የትግራይ ዋንጫ የምድብ ድልድል ይፋ ሆኗል

የትግራይ ክልል ዋንጫ የምድብ ዕጣ የማውጣት ሥነ-ስርዓት ዛሬ ተካሂዷል።

በኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታዎች ምክንያት እንዲራዘም የተደረገው የትግራይ ዋንጫ የፊታችን ቅዳሜ መስከረም 26 ቀን እንደሚጀምር ይጠበቃል። በሽቶ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን እና የትግራይ ክልል እግር ኳስ ፌደሬሽን በጣምራ ለመጀመርያ ግዜ  ለሚዘጋጀው ለዚህ ውድድር ዛሬ 9፡00 ላይ በትግራይ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፅህፈት ቤት የዕጣ ማውጣት ስነ-ስርአት ተካሂዷል። በዚህም መሰረት መቀመጫቸውን በክልሉ ያደረጉት አራት የፕሪምየር ሊግ ክለቦች እና የከፍተኛ ሊጉ አክሱም ከተማ እንዲሁም ተጋባዡ ድሬዳዋ ከተማ ሶስት ክለቦችን በያዙ ሁለት ምድቦች እንዲከፈሉ ተደርጓል።

በወጣው ዕጣ መሰረትም በምድብ አንድ ወልዋሎ ዓ.ዩ ፣ ደደቢት እና ሽረ እንደስላሴ ሲደለደሉ ምድብ ለ ደግሞ መቐለ ከተማ ፣ ድሬዳዋ ከተማ እና አክሱም ከተማን አካቷል። በውድድሩ የመክፈቻ ዕለትም 08፡00 ላይ ከምድብ አንድ ወልዋሎ ዓ.ዩ ከደደቢት ሲገናኙ 10፡00 ላይ ደግሞ በምድብ ሁለት  መቐለ ከተማ ከድሬዳዋ ከተማ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ይሆናል።