ዋልያዎቹ በባህርዳር ለጨዋታው ዝግጁ ሆነዋል

ነገ ረቡዕ 10:00 በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ሶስተኛ የምድብ ጨዋታውን የሚያደርገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በባህርዳር የነበረውን ቆይታ እና የመጨረሻ ልምምድ በጭሩ ሲቃኝ።

በ2019 በካሜሮን አስተናጋጅነት በሚደረገው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ተሳታፊ ለመሆን ከ2009 ጀምሮ ሲደረግ የነበረው የማጣሪያ ውድድር ሶስተኛ የምድብ ጨዋታዎች በዚህ ሳምንት መደረግ ይጀምራሉ። ከጋና ፣ ሴራሊዮን እና ኬንያ ጋር የተደለደለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በመጀመሪያው ማጣሪያ ከሜዳው ውጪ በጋና በሰፊ የግብ ልዩነት ከተሸነፈ በኃላ በሀዋሳ አለም አቀፍ ስታዲየም ደግሞ ሴራሊዮንን በጌታነህ ከበደ ብቸኛ የፍፁም ቅጣት ምት ግብ ረትቶ በእኩል ሶስት ነጥቦች ከሌሎቹ የምድቡ ቡድኖች ጋር በነጥብ ተስተካሎ በግብ ክፍያ ተበልጦ መጨረሻ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ከሴራሊዮኑ ጨዋታ በኋላ ለተወሰኑ ቀናት ተበትነው የቆዩት ዋልያዎቹ የኢትዮጵያ ዋንጫ ውድድር ከተጠናቀቀ በኋላ ለኬንያው ጨዋታ ከመስከረም 21 ጀምሮ ለዘጠኝ ተከታታይ ቀናት ልምምዳቸውን አድርገዋል። ለ26 ተጨዋቾች ጥሪ ያቀረቡት አሰልጣኝ አብርሀምም ሽመክት ጉግሳን በአዲስ መልክ ወደ ቡድናቸው ሲቀላቅሉ ጉዳት ላይ የነበረው ተመስገን ካስትሮን እና ወደ ሰርቢያ ለሙከራ አቅንቶ የነበረው ከንዓን ማርክነህንም አካተዋል። ሆኖም የመስመር አጥቂው በሀይሉ አሰፋ እና ተከላካዩ ሳላሀዲን ባርጊቾ በጉዳት ከስብስቡ ውጪ ሲሆኑ አስቻለው ታመነ ደግሞ በኢትዮጵያ ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ ባስተናገደው ጉዳት ምክንያት ዘግየት ብሎ ቡድኑን በመቀላቀል ለጨዋታው ዝግጁ ሆኗል። ከሀገር ውጪ ባሉ ሊጎች ከሚጫወቱ ተጨዋቾች መካከል ደግሞ የፔትሮጀቱ ሽመልስ በቀለቀደም ብሎ የመጣ ሲሆን ቢኒያም በላይ ፣ ጋቶች ፓቶም እና ኡመድ ዑኩሪ ግን ሰኞ የመጀመሪያ ልምምዳቸውን በማድረግ ከቀሪው ስብስብ ጋር ተቀላቅለዋል።


መስከረም 21 ከአዲስ አበባ ወደ ባህርዳር በማቅናት በብሉ ናይል ሆቴል እና ሪዞርት (አቫንቲ) በማረፍ ዝግጅታቸውን የጀመሩት ዋልያዎቹ የመጀመሪያ ልምምዳቸውን በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታድየም የመለማመጃ ሜዳ ላይ የሰራ ሲሆን በመቀጠልም ወደ ዋናው የስታድየሙ የመጫወቻ ሜዳ በመዞር ዝግጅቱን ሲያደርግ ቆይቷል። በዝግጅቱም አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ እና ረዳቶቹ የኬንያ እና የጋናንን ጨዋታ የሚያሳይ የቪዲዮ ምሥል እንደ ግብዓትነት በመጠቀም ተጨዋቾች በሜዳ ላይ ምን ማድረግ እንደሚገባቸው በተግባራዊ ልምምድ ሲያሰሩ ቆይተዋል።

ብሔራዊ ቡድኑ ዛሬ ከረፋዱ 4 ሰዓት ላይ በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የመጨረሻ ልምምዱን ሲያደርግም የቦታ አያያዝን እና ኳስን መሰረት ያደረጉ ቀለል ያሉ የሜዳ ላይ ስራዎች የልምምዱ ዋነኛ ትኩረቶች ነበሩ። የፍፁም ቅጣት ምት የመምታት እንዲሁም አጥቂዎች እና ተከላካዮች ላይ ትኩረት ያደረጉ ስራዎችም በዝግጅቱ ተካተው ነበር። የዛሬው የመጨረሻ የልምምድ መርሀ ግብር ለአንድ ሰዓት ያህል የቆየ ሲሆን የብሔራዊ ቡድኑ ስብስብ ከጉዳት ነፃ ሆኖ በመልካም ጤንነት የነገውን ጨዋታ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል።