ካሜሩን 2019 | የኬንያ ብሔራዊ ቡድን የመጨረሻ ልምምዱን ሰርቷል

በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከጋና ሴራሊዮን እና ዋልያወቹ ጋር የተደለደለው እና ሶስተኛ የምድብ ማጣሪያውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ነገ 10:00 በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የሚገጥመው የኬንያ ብሔራዊ ቡድን የመጨረሻ ልምምዱን በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም አከናውኗል።

32 የልዑካን ቡድን አባላትን በመያዝ ትላንት (ሰኞ) ማለዳ ባህርዳር በመግባት በዲላኖ ሆቴል ማረፊያውን ያደረገው ቡድኑ ከሰዓት 10:00 ላይ በባህር ዳር ስታዲየም ውስጥ በሚገኝ አነስተኛ ሜዳ የመጀመሪያ ልምምዱን የሰራ ሲሆን ዛሬ የመጨረሻ ልምምዱን በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ሰርቷል። ለአንድ ሰአት ተኩል ያህል በቆየው ልምምድ ፈረንሳዊው አሰልጣኝ ሴባስቲያን ሚኜ እና ረዳቶቻቸው የመስመር ላይ ተሻጋሪ ኳሶች ላይ ያተኮረ እንዲሁም በዲፓርትመንት የተከፋፈለ የማጥቃት እና የመከላከል ትኩረትን መሰረት ያደረጉ ስራዎችን ሲያሰሩ ተመልክተናል። ቡድኑ በሁለት ተከፍሎ ጨዋታም አድርጓል። 

ጋናን ከረቱበት ስብስብ ውጭ የነበረው የቶትነሀሙ አማካይ ቪሴንት ዋኒያማ በቡድኑ ስብስብ ውስጥ መካተቱ ቡድኑን ያጠናክራል ተብሎ ሲጠበቅ ለጃፓኑ ካሺማ ሬሰርስ የሚጫወተው አጥቂው ሚሼል ኦሉንጋም ተጠባቂ የቡድኑ ተጫዋች ሆኗል፡፡

ነገ 10:00 በባህር ዳር የሚደረገውን ወሳኝ ጨዋታ ጋንቢያዊው ባካሪ ፓፓ ጋሳማ እና የሀገሩ ዜጎች የሆኑት ረዳት ዳኞቹ ሱሌይማን ሶሴ እና አብዱላሊዝ ጃውል ሲመሩት ኮሚሽነሩ ከዩጋንዳ ገምጋሚ (አሰሰር) ከግብፅ ናቸው፡፡