“ኬንያ ላይ የሚደረገውን ጨዋታ እንደ ፍፃሜ ነው የምናየው” አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ

በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ምድብ ስድስት ባህር ዳር ላይ ኬንያን ያስተናገደችው ኢትዮጵያ ጨዋታውን ያለ ግብ አጠናቃ ደረጃዋን የማሻሻል እድሏን ሳትጠቀምበት ቀርታለች። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የዋልያዎቹ አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ለጋዜጠኞች የሰጡትን አስተያየት እንዲህ አቅርበነዋል።

ስለ ጨዋታው

በዛሬ ከኬንያ ጋር ባደረግነው ጨዋታ ተጫዋቾቼ ባሳዩት እንቅስቃሴ ደስተኛ ነኝ። ጥሩ ቡድን እንዳለን ለማየት ችያለሁ። በመጀመሪያ አርባ አምስት የነበረውን የታክቲክ እና የትኩረት ማጣት ችግር በመቅረፍ በሁለተኛው አጋማሽ ላይ ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ተጭነን ለመጫወት ሞክረናል። የኬንያ ቡድን ደግሞ በየቦታው የሚጫወቱ ተጫዋቾች ጥሩ ልምድ ያላቸው ናቸው። በተለይ ደግሞ በታክቲኩ የተሻለ ልምድ ያላቸው ናቸው የነበሩት። በመከላከል እና በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ባደረጉት ጥረት የሚፈልጉትን አሳክተው ወጥተዋል።

በሜዳቸው ላይ ይህን አጨዋወት ይጫወታሉ ብለን አንጠብቅም። ስለዚህ የነበሩትን ጥቃቅን ስህተቶች አርመን ከሜዳችን ውጭ የምናደርገውንም ጨዋታ ዛሬ ባሳየነው ብቃትና ከዛም በተሻለ መልኩ ተንቀሳቅሰን የተሻለ ውጤት ይዘን ለመመለስ ጥረት እናደርጋለን።

የኬንያው አሰልጣኝ ውጤቱ ተገቢ ነው ብለዋል። ለአንተ ውጤቱ ተገቢ ነው ?

ለኛ ውጤቱ ተገቢ አይደለም፤ ይህ ውጤት ለኛ መሆን ነበረበት። እንደጨወታ ብልጫችን ውጤቱን ይዘን መውጣት ነበረብን። በእርግጥ እነሱ ከሜዳቸው ውጭ ስለተጫወቱ አንድ ነጥብ ተነሳሽነታቸውን ከመጨመር አንፃር ሊጠቅማቸው ይችላል። ያም ሆነ ይህ ቡድናችን ላይ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ እና በተጫዋቾቻችን ላይ ቀጣዩንም ጨዋታ በተሻለ ስነልቦና መጫወት እንዲችሉ ያስቻሉ ናቸው። መልበሻ ክፍል ከገባንም በኃላ ተጫዋቾቼ ላይ ያየሁት የቁጭት ስሜት በመልሱ ጨዋታ የተሻለ ነገር ለመስራት መምጣታቸው እና ይህ በራሱ አንድ ጥሩ መገለጫ ነው ብዬ አስባለሁ። 

በሴራሊዮን ጨዋታ ላይ በማጥቃቱ ረገድ ከፍተኛ ክፍተቶች ነበሩ። ዛሬም በተመሳሳይ ያ ተስተውሏል…?

ገና አልተሰራም፤ ግልፅ ነው። ቀደም ብዬ ባለፈው መግለጫ እንዳልኩት ማጥቃታችን ላይ ጥሩ ነን። በተደጋጋሚ ስርአት ባለው እና በተጠና መልኩ ወደ ግብ ክልል ውስጥ በተደጋጋሚ ገብተናል። አሁንም ወደ ግብ የመቀየሩና የአጨራረስ ብቃታችንን ማረም እና ማስተካከል አለብን። ይሄ ደግሞ በአንድ ጊዜ የሚመጣ አይደለም፤ በየጊዜው እየሰራን የተለያዩ ጨዋታዎችን እያደረግን እያዳበርነው የምንሄደው ነገር ነው። ትልቁ ነገር ግን ቡድኑ እንደ ቡድን የምፈልገውን አጨዋወት እና ማድረግ ያለባቸውን ነገሮች በሙሉ በሜዳ ውስጥ ምንም ሳይቆጥቡ ተጫዋቾቼ ሁሉንም ነገር አድርገዋል። በአጠቃላይ ተጫዋቾቼ በጣም ጥሩ ነበሩ። ያ ነው ትልቁ ነገር ለኔ። ያ ደግሞ በሚቀጥለው ጥሩ ነገር እንድንሰራ ያደርገናል። ባለፉትን ዘጠኝ ቀናት ሰርተናል፤ አሁንም እንቀጥላለን።

የኬንያው አሰልጣኝ ሴባስቲዬን ሚኜ ቀጣዩ ጨዋታ እንደፍፃሜ ነው ብለዋል …

የኛም ሀሳብ የኬንያው አሰልጣኝ ካሉት ውጭ አይደለም። የሚቀጥለውን ጨዋታ እኛም እንደፍፃሜ ነው የምናየው። ምክንያቱም ወሳኝ ነው። የሴራሊዮን መቀጣት አለመቀጣት ገና አለየለትም፤ ስለዚህ ከሶስት ቀናት በኃላ እዛ የምናደርገው ጨዋታ ለኛ እጅግ በጣም ወሳኝ ነው። ስለዚህ የምንሄደው እንዳይገባብን መከላከሉ ላይ በጥንቃቄ ሰርተን ለማሸነፍ ደግሞ ማግባት ላይ ጥሩ ነገር ለማድረግ የሚችል ቡድን መገንባት ነው አላማችን። 

ስለ ደጋፊዎቹ…

ደጋፊዎችን በተመለከተ እኔ በጣም ቃላት ያጥረኛል። ምክንያቱም የባህር ዳር እና አካባቢዋ ስፖርት አፍቃሪ፣ ከብዙ ቦታ ቡድናችንን ለመደገፍ የመጡ ተመልካቾች የቡድኑ አስራ ሁለተኛ ተጫዋች ነበሩ። ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ድረስ ቡድናችንን ደግፈዋል። የቡድናችንን የመነሳሳት ብቃት ይበልጥ አዳብረዋል እና ሁሉንም በስታዲየሙ የተገኘውን በሙሉ እግዜር ያክብርልኝ። ለሰጣችሁን ድጋፍ እጅግ እጅግ በጣም አድርገን እናመሰግናለን ለማለት እፈልጋለሁ። በቡድኔ ተጫዋቾች እና በቡድኑ አባላትም ስም በስቴዲየሙ ተገኝቶ ላበረታቱን ጨዋ ደጋፊዎቻችን እጅ እነሳለሁ፡፡