ከኢትዮጵያ እና ኬንያ ጨዋታ ከፍተኛ ገቢ ተገኝቷል

በ2019 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ሶስተኛ የምድብ ጨዋታ መስከረም 30 ባህር ዳር ዓለም አቀም ስታድየም ኬንያን ያስተናገደው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ያለ ግብ በአቻ ውጤት ማጠናቀቁ ይታወሳል። በስራ ቀን እና ሰዓት በተካሄደው ጨዋታ የታደመው እጅግ ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ ተመልካች እና የነበረው ደማቅ ድባብም በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሀንን ጭምር ያነጋጋረ መሆኑ ይታወቃል።

ሶከር ኢትዮጵያ አጨዋታው ጋር በተያያዘ ከኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ባገኘችው መረጃ በነፃ መግቢያ የገቡትን አካላት እና በመግቢያ አካባቢ በተፈጠረ ግርግር ትኬት ሳይቆርጡ የገቡትን ሳይጨምር ከ70 ሺህ በላይ ተመልካች ጨዋታውን እንደተከታተለ ተገልጿል። በገንዘብ ደረጃም ከ1.5 ሚልየን ብር በላይ ገቢ እንደተገኘ ሰምተናል። ይህም ከዚህ ቀደም ከተገኙት ገቢዎች የተሻለው እንደሆነ ተነግሮናል።


የረቡዕ ጨዋታን ፍፃሜ ተከትሎ የኬንያው አሰልጣኝ ሰባስቲየን ሚኜ ”  ከአስራ ሁለት ተጫዋቾች ጋር ነበር የተጫወት ነው። የማወራው ስለ ዳኛው ሳይሆን ስለ ደጋፊዎች ነው። የነበረው የደጋፊ ድባብ ለኛ ከባድ ነበር።” በማለት የድጋፍ ሁኔታውን በአግርሞት ሲገልፁ አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱም ” ደጋፊዎችን በተመለከተ እኔ በጣም ቃላት ያጥረኛል። ምክንያቱም የባህር ዳር እና አካባቢዋ ስፖርት አፍቃሪ፣ ከብዙ ቦታ ቡድናችንን ለመደገፍ የመጡ ተመልካቾች የቡድኑ አስራ ሁለተኛ ተጫዋች ነበሩ።” ሲሉ አስተያየት መስጠታቸው ይታወሳል። 

ፎቶ ከላይ – ኤቢ አድቨርታይዚንግ እና ኤቨንት