ሶከር መፅሀፍት | ኢንቨርቲንግ ዘ ፒራሚድ (ምዕራፍ አንድ – ክፍል አንድ)

በእንግሊዛዊው እውቅ ጸኃፊ ጆናታን ዊልሰን የተደረሰውና የእግርኳስ ታክቲክ ታሪክ ላይ ያለኮረው Inverting the pyramid መፅሀፍን በትርጉም ካለፈው ሳምንት ጀምሮ እያቀረብንላችሁ እንገኛለን። በዛሬው ክፍል ሁለት መሰናዷችን የመፅሀፉ ምዕራፍ አንድን በከፊል አቅርበንላችኋል።


|| የመፅሀፉን መቀድም ለማንበብ ይህን ይጫኑመቅድም


ምዕራፍ አንድ

ከመሰረቱ ወደ ፒራሚዱ ቅርጽ

እግርኳስ መሰረታዊ ቅርጽ ሳይዝ ምስቅልቅል ባለ አቀራረብ መካሄድ ጀመረ፡፡ ቆይቶም በንግስት ቪክቶሪያ ዘመን የነበሩ ሰዎች መጡና ህግና ስርዓት አበጁለት፡፡ በኋላም ኅልዮታውያኑ ጥልቅ ትንታኔ ያደርጉለት ያዙ፡፡ እስከ 1920ዎቹ መጨረሻ ድረስ ታክቲክ በዘመናዊ እግርኳስ ግብዓትነት እውቅና አላገኘም፤ በውይይት ደረጃም ቦታ አልተሰጠውም፡፡ ይሁን እንጂ በ1870ዎቹ መጀመሪያ ተጫዋቾች በሜዳ ውስጥ የሚኖራቸው የአደራደር መዋቅር በጨዋታው የአቀራረብ ስልት ላይ ትልቅ ልዩነት እንደሚያስከትል ይታወቅ ነበር፡፡ ነገር ግን በጨዋታው ህልውና መነሻ ዓመታት እግርኳሱ ይህን መሰል ውስብስብ ሀሳብ ፈፅሞ የሚያውቀው አይደለም፡፡

በተለያዩ ባህሎች ውስጥ ኳስ መምታትን የሚያካትቱ ጨዋታዎች እንደነበሩ ቀደምት መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ሮም፣ ግሪክ፣ ግብጽ፣ ካሪቢያኖች፣ ሜክሲኮ፣ ቻይና እና ጃፓንን የመሳሰሉ ሀገራት እግርኳስ ጨዋታን የጀመሩ ስለመሆናቸው በርካታ አቤቱታዎችን ያቀርባሉ፡፡ ሆኖም ስፖርቱ የተሻለ መልክ ይዞ የታየው በመካከለኛው ዘመን የብሪታንያ ዜጎች እንዲሁ ተሰባስበው እና ቡድናዊ ቅርጽ ሳይኖራቸው በሚጫወቱበት ጊዜ እንደነበር ይነገራል፡፡ በዚያ ዘመን የነበሩ የጨዋታ ደንቦች ከቦታ ቦታ የመለያየት አዝማሚያ አሳይተዋል፡፡ ይሁን እንጂ በመሰረታዊነት ሁለት ቡድኖች እያንዳንቸው ለክብነት የቀረበ ቁስን እየገፉ ግምታዊ ስፋት ባለው ሜዳ ላይ በሚገኙ ተቃራኒ አቅጣጫዎች የሚቆሙ ኢላማዎች ጋር ለማድረስ ይጥሩ ነበር፡፡ ጨዋታው የጋለ ስሜት የሚንጸባረቅበት፣ ከስርዓት ውጪ የሆነ፣ ግርግር የበዛበትና ህጋዊ አካሄድን የማይከተል ይዘትም ታይቶበታል፡፡ በአስራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን አስተምህሮዎቻቸውን በጠንካራ ክርስቲያናዊ ስርዓቶች ላይ የመሰረቱ የህዝብ ትምህርት ቤቶች ስፖርት የተማሪዎቻቸውን ሞራላዊ እሴት ከፍ ሊያደርግላቸው እንደሚችል በማሰብ ለእግርኳስ የቀረበ ስፖርት ማዘወተር ጀመሩ፡፡ ታክቲካዊ እሳቤዎች ከመፈጠራቸው በፊት የህገ-ደንቦች ውህደትና ስብስብ ዋነኛ ትኩረትን የሚሻ ጉዳይ ሆነ፡፡

በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መባቻ አካባቢ ቀደም ያሉት ተጫዋቾች በሜዳ ላይ የነበራቸውን አደራደር የሚወክሉ ቅርጾች በግልጽ መታየት ሲጀምሩ እንኳ ይሰጣቸው የነበረው ዋጋ ያን ያህልም አልነበረም፡፡ በእግርኳስ የጅማሮ ጊዜያት በታክቲክ ላይ የተመረኮዙ ረቂቅ ሐሳቦች፣ ቀስቶችና ተቋራጭ መስመሮችን የያዙ ስዕላዊ መግለጫዎች ፍጹም ሊታሰቡ የማይችሉ ናቸው፡፡ በእርግጥ እግርኳስዊ አመለካከትን በማሳየት ረገድ የጨዋታው ዝግመታዊ የታክቲክ እድገት ትምህርት ሰጪ ቢሆንም ዘወትር ዋጋው የማይታይና ቦታ ያልተሰጠው ሆኖ ቆይቷል፡፡ በብሪታኒያውያኑ አዕምሮ ዘንድ የሰረጸው “ተፈጥሮአዊው የአጨዋወት መንገድ” አስተሳሰብ ደግሞ ለእነዚህ ሒደቶች ጋሬጣ ሆኖባቸዋል፡፡ (ህግና ደንቦች ከረቀቁ በኋላ በነበሩት ከአርባ በላይ አመታት እንኳ <ከእንግሊዛውያኑ የእግር ኳስ አጨዋወት መንገድ> ውጪ ምንም የተለየ ለውጥ አልታየም፡፡)

ዳቪድ ዊነር ስለእንግሊዝ እግርኳስ ታሪክ በጻፈበት <ዞስ ፊት> የተሰኘ መጽሃፍ ላይ ሁኔታውን ወደ ኋላ መለስ ብሎ ለመቃኘትና ለመገንዘብ መሞከር ግራ አጋቢ ቢመስልም የእንግሊዞች እግርኳስ አረዳድ “የአገሪቱ ግዛታዊ ልዕልና በመውደቅ ሒደት ውስጥ እንደሚገኝ የማሰብ ሞራላዊ ድክመት የሚወገዝ ሊሆን ይገባል፡፡” ከሚል ስር የሰደደ ሐሳብ የመጣና በንግስት ቪክቶሪያ የአገዛዝ ዘመን የመጀመሪያዎቹ ዓመታት የተንሰራፋ እንደሆነ ያብራራልናል፡፡

ቡድናዊ ይዘት ያላቸው የስፖርት አይነቶች “ለመኖር ራስን ብቻ በጥልቀት ማወቅ በቂ ነው፡፡” የሚል የፍልስፍና መርህን ስለሚቃረኑ ትኩረት አግኝተው ይበረታቱ ጀመር፡፡ ይህ አይነቱ ፍልስፍናዊ አስተሳሰብ ወሲባዊ ፍላጎትን ለማርካት በግል የሚወሰዱ መፍትሄዎችን መስፋፋት ይፈቅድ ነበር፡፡ በጊዜው ወደ ሞራላዊ መቀመቅ የሚጥል ከዚህ የከፋ ተግባር አልታየም፡፡ ለምሳሌ ያህልም የአፒንግሀም ትምህርት ቤቶች ርዕሰ መምህር የነበረው ሪፈረንድ ኤድዋርድ ትሪንግ “ድርጊቱ በአጭር ወደ መቀጨትና ከንቱ ህልፈት ይዳርጋል፡፡” እያለ በስብከት መልክ ይወተውት ነበር፡፡ እግርኳስም ይህን እኩይ ተግባር ማርከሻ ተደርጎ ተወሰደ፡፡ <ዘ ቦይስ ቻምፒዮን ስቶሪ ፔፐር> በተባለ መፅሔት ላይ በ1901 ኢ.ኤ.ሲ.ቶምሰን ” የእግር ኳስን ያህል የጀግኖች ስፖርት የለም፡፡ ጨዋታው ቁርጠኝነት፣ ጥንካሬ፣ ጽናት፣ ብርታትና እርጋታን የሚሻ ልዩና የተለመደው እንግሊዛዊ ጀብዱ የታከለበት ነው፡፡” ሲል ጽፏል፡፡ ለሁኔታው መገጣጠም እጅጉን ጥሩ ማስረጃ የሚሆኑ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አመክንዮዎች አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል የእንግሊዝ እግርኳስ የሃገሪቱን ግዛታዊ እድገት ለማገዝ ጥቅም ላይ ከዋለ በኋላ ብሪታኒያ በንጉሰ ነገስታዊ አገዛዝ የነበራት ግዙፍ ተጽዕኖ ውድቀት ሲጀምር ሃገሪቱ የደረሰችበት የእግርኳስ ልዕለ ኃያልነትም አብሮ መዳከሙ የግጥጥሞሹ ማሳያ ግልጽ ምልክት ነው፡፡

በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በመጀመሪያው አጋማሽ ኣመታት እግርኳስ ተወዳጅነቱ አሻቅቦ በከፍተኛ ደረጃ ተስፋፋ፡፡ ሆኖም በጅማሮዎቹ ጊዜያት በበርካታ ትምህርት ቤቶች የሚተገበሩ የጨዋታ ህጎች ልዩነቶች ይታይባቸው ነበር፡፡ በቼልተንሐምና ራግቢ በሚገኙ ሰፊና ክፍት ሜዳዎች ላይ ይካሄዱ የነበሩት ጨዋታዎች በግብስብሱ ከሚደረጉት በጥቂቱም ቢሆን የተለዩ መሆናቸው ለናሙናነት መቅረብ የሚችል ነው፡፡ አንድ ተጫዋች በራሱ አልያም በተጋጣሚ ተጫዋቾች ጥፋት ተሰርቶበት መሬት ላይ ሊወድቅ ይችላል፡፡ ሆኖም ግን ከወደቀበት ጭቃ ላይ ሳይጎዳ ሊነሳ የሚችልበት አጋጣሚም ነበር፡፡ በተጻራሪው በቻርተር ሐውስ እና በዌስት ሚኒስትር ገዳማት አካባቢ ባሉ ሜዳዎች ላይ እንዲህ አይነቶቹ ግብግቦች ለአጥንት ስብራት ይዳርጋሉ፡፡ ስለዚህም በዚያ አካባቢ የድሪብሊንግ ዘዴ (ኳስን ለተወሰነ ርቀትና ጊዜ እግር ስር ይዞ የመጫወት ሒደት) በዚያ አካባቢ ተጀመረ፡፡ አዲሱ አጨዋወት ኳስን በእጅ የመያዝ እንቅስቃሴን ከደንብ ውጪ የሆነና ያልተፈቀደ ቢያደርገውም ጨዋታው ዘመነኛ መልክ ሊይዝ ስላልቻለ ሙሉ በሙሉ ከዚህኛው ዘመን እግር ኳስ የተለየ ነበር፡፡ ማንም ስለፎርሜሽኖች ግንዛቤ አልነበረውም፡፡ የጨዋታ ጊዜ ርዝመት እና በየቡድኑ የሚኖሩ የተሳታፊ ተጫዋቾች ቁጥርም ገና ውሳኔ አላገኘም ነበር፡፡ በእርግጥ በትምህርት ቤቶች ውስጥ የክፍል አለቆችና አንጋፎቹ ተማሪዎች ኳስን በእግሮቻቸው ስር አድርገው ሲሮጡ ምናልባት በተጋጣሚያቸው ተጫዋቾች “ታክል” ተደርገው ኳሱን ከተቀሙ በሚል የቡድን አጋሮቻቸው ከኋላ ሆነው ሲከተሏቸው (ከለላ ሲሰጧቸው) የተቃራኒ ቡድን ተጫዋቾች (በተወሰኑ ት/ቤቶች ውስጥ በእድሜያቸው አነስ ያሉና አዘወትረው የትልልቆቹን አድካሚና አሰልቺ ስራ የሚሰሩ አገልጋይ ተማሪዎች) ደግሞ የትልልቆቹን እንቅስቃሴ ለማቆም ይጥራሉ፡፡

በፊት መስመር ተሰላፊዎች መካከል የነበረው የእርስ በርስ መግባባት በቅጡ ያላደገና ጅምር ቁመና የያዘ ነበር፡፡ ከዚያ እንጭጭነት ደረጃ ተነስቶም የመጀመሪያው የእንግሊዝ እግር ኳስ ስርዓት ላይ የጨመረው ውስን መሰረታዊ ገጽታ ነው፡፡ ጨዋታው ባብዛኛው <ድሪብሊንግ>ን የሚያካትት ሲሆን ቅብብሎች፣ ውህደትና መከላከል የበታችነት ተደርገው ይታሰቡ ነበር፡፡ ከዚህ ውስጥ በመጠኑም ቢሆን ኳስን በግንባር ወደ ታች መግጨት እንግሊዛውያን በአጠቃላይ ለህይወት ላላቸው አመለካከት የተሻለውና ተመራጩ የእግርኳስ መገለጫ ሊሆን እንደሚችል አንዳንድ ሰዎች ይናገራሉ፡፡ በህዝብ ት/ቤቶች የነበረው አመለካከትም ይህን የጨዋታ አቀራረብ የመናቅ አዝማሚያ አሳይቷል፡፡ (ታዋቂው ሃንጋሪያዊ የወግ ጸኃፊ ጆርጅ ማይክስ በ1946 ለመጀመሪያ ጊዜ የብሪታንያን ምድር ሲረግጥ አንዲት እንግሊዛዊት እንስት “ጎበዝ” ብላ ስታደንቀው ቃሉ ያየዘውን ክብደትና ያለመታመን አዝማሚያ ሲለሚረዳ በጊዜው ስለተሰማው ከፍተኛ ኩራት በስላቅ መልክ ጽፏል፡፡)

በየቦታው የአተገባበር ልዩነት ይታይባቸው የነበሩት የጨዋታ ህግና ደንቦች በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ እግር ኳስን ለማስፋፋት አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ፈጥረዋል፡፡ በደቡብ ምስራቅ እንግሊዟ ሱሬይ ክልል በሚገኘው የጎዳልሚንግ ኮሌጅ መምህር የነበረው ኤች.ሲ.ማልደን በ1848 በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ካሉት ክፍሎቹ በአንዱ የሐሮው፣ ኤተን፣ ረግቢ፣ ዊንቼስተርና ሽሪውበሪ ት/ቤት ተወካዮችን እንዲሁም በሚያስገርም ሁኔታ ሁለት የትምህርት ተቋማት የማይወክሉ ወጣቶችን ጉባኤ ጠርቶ በብዙዎች ዘንድ ምናልባትም “የመጀመሪያ ነው፡፡” ተብሎ የሚገመተውን የጨዋታ ህጎች ጥንቅር እንዲያረቁ አደረገ፡፡ ማልደንም ” አዲሱን የጨዋታ ህጎች ስብስብ <የካምብሪጅ ህጎች> በሚል መጠሪያ ለህትመት አበቃነው፡፡ በከተማዋ እምብርት ሰፊ መናፈሻ ላይ በሚገኘው <ፓርከርስ ፒስ> የተሰኘ ስፍራ ህግና ደንቦቹ እየተባዙ ተሰራጩ፡፡ በአመርቂ ሁኔታም ስኬታማ ሆኑ፡፡ ጥሩ አመኔታና ተቀባይነት አግኝተውም ተግባር ላይ መዋል ጀመሩ፡፡ የትኛውም የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪ ህግና ደንቦቹን ሳያከብርና ሳይወድ ስለመጫወቱ በጭራሽ ሰምቼ አላውቅም፡፡” ሲል ጻፈ፡፡


ስለ ደራሲው 

ጆናታን ዊልሰን ዝነኛ እንግሊዛዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ሲሆን በተለያዩ ጋዜጦች፣ መጽሄቶች እና ድረገጾች ላይ ታክቲካዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው የእግርኳስ ትንታኔዎችን የሚያቀርብ ጉምቱ ጸኃፊ ነው፡፡  ባለፉት አስራ ሁለት ዓመታትም የሚከተሉትን ዘጠኝ መጻህፍት ለህትመት አብቅቷል፡፡

-Behind The Curtain: Travels in Eastern European Football (2006)

-SunderlandA Club Transformed (2007)

-Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics (2008)

-The Anatomy of England (2010)

-Brian Clough: Nobody Ever Says Thank You: The Biography (2011)

-The OutsiderA History of the Goalkeeper (2012)

-The Anatomy of Liverpool (2013)

-Angels With Dirty Faces: The Footballing History of Argentina (2016)

-The Barcelona Legacy: Guardiola, Mourinho and the Fight For Football’s Soul (2018)