የደቡብ ካስቴል ዋንጫ ዛሬ ተጀምሯል

በደቡብ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት እንዲሁም በካስቴል ቢራ ስፖንሰር አድራጊነት ለ7ኛ ጊዜ የሚደረገው የደቡብ ካስቴል ዋንጫ በዛሬው ዕለት ተጀምሯል። በሶስት ክለቦች መካከል ከጥቅምት 4-10 በሀዋሳ የሚካሄደው ይህ ውድድር ከዚህ ቀደም ከስድስት በላይ ክለቦችን እያሳተፈ ቢዘልቅም ዘንድሮ ወደ ሶስት ቀንሷል።

ዛሬ በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ ላይ በ09:00 ሀዋሳ ከተማን ከደቡብ ፖሊስ ያገናኘው ጨዋታ በሀዋሳ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። አቶ ገልገሎ ገዛኸኝ (የደቡብ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ም/ሀላፊ) እና የክልሉ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ደመላሽ ይትባረክ ባስጀመሩት በዚህ ጨዋታ የተቀዛቀዘ እንቅስቃሴ የቸመለከትንበት ነበር። በመጀመሪያው አጋማሽ በአንፃራዊነት አዲስ አዳጊው ደቡብ ፖሊስ በተሻለ መልኩ መንቀሳቀስ የቻለ ሲሆን ሀዋሳ ከተማ ደግሞ በርካታ ወጣት ተጫዋቾችን ተጠቅሟል። በ42ኛው ደቂቃ የሀዋሳ ከተማ የተከላካይ ስፍራ ተጫዋቾች በሳጥን ውስጥ በሰሩት ጥፋት የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት በክለቡ የሙከራ ጊዜ እያሳለፈ የሚገኘው የቀድሞ ሀዋሳ፣ ሲዳማ፣ ደደቢት እና አርባምንጭ አጥቂ አሸናፊ አደም ወደ ግብነት ለውጧት በደቡብ ፖሊስ 1-0 መሪነት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡


በሁለተኛው አጋማሽ አዳነ ግርማን ጨምሮ በርካታ ተጫዋቾችን ቀይሮ ያስገባው ሀዋሳ ከተማ ፍፁም ብልጫ ያሳየበትን እንቅስቃሴ ማድረግ ችሏል። በተለይ አዳነ ግርማ በርካታ የግብ አጋጣሚዎች ከመሀል ሜዳ እየተነሳ ሲፈጥር አስተውለናል። 57ኛው ደቂቃ ላይ የሙከራ ጊዜን እያሳለፈ የሚገኘው የወልቂጤ ከተማው አጥቂ ብሩክ በየነ እንዲሁም ወጣቱ አጥቂ ቸርነት አውሽ በ61 ደቂቃ ባስቆጠሯቸው ግቦች ሀዋሳ ከተማ 2-1 በሆነ ውጤት አሸንፎ ጨዋታው ተጠናቋል።
ውድድሩ የፊታችን ማክሰኞ ደቡብ ፖሊስ ከሲዳማ ቡና በሚያደርጉት ጨዋታ የሚቀጥል ይሆናል፡፡