ደቡብ ፖሊስ ስምንት ተጫዋቾችን አስፈረመ

ከበርካታ ነባር ተጫዋቾቹ ጋር የተለያየው አዲሱ የፕሪምየር ሊግ ክለብ ደቡብ ፖሊስ ስምንት ተጫዋቾችን ወደ ቡድኑ ቀላቅሏል።

ከስምንት ዓመታት በኃላ ወደ ፕሪምየር ሊጉ የከፍተኛ ሊግ ሻምፒዮን በመሆን ያደገው ደቡብ ፖሊስ ራሱን አጠናክሮ በሊጉ ተፎካካሪ ለመሆን በርካታ ለውጦች እያደረገ ይገኛል። አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራውን ከረጅም ጊዜ በኋላ ዳግም ከቀጠረ ጊዜ ጀምሮም ከሃያ የሚበልጡ ነባር ተጫዋቾችን በኮንትራት ማለቅ እና በአሰልጣኙ ፍላጎት አሰናብቷል። በለቀቁት ምትክም አዳዲስ ልምድ ያላቸው እና ወጣት ተጫዋቾችን እያመጣ ሲገኝ አሁን ደግሞ ስምንት የሚደርሱ ተጫዋቾችን በሙከራ እና በቀጥተኛ ፊርማ የቡድኑ አካል አድርጓል፡፡

ከፈራሚዎቹ አንዱ የሆነው የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ ብሩክ አየለ በኤሌክትሪክ ፣ ሀዋሳ ፣ ሲዳማ ቡና እና ወልዲያ ያሳለፈ ሲሆን ከወራት በፊት በገጠመው ጉዳት ከሜዳ ርቆ ቆይቶ ካገገመ በኋላ ወደ ፖሊስ አምርቷል። ሌላኛው አማካይ ወንድሜነህ ዘሪሁን በመከላከያ ፣ አዳማ ፣ ኤሌክትሪክ ፣ ሀዋሳ እና አርባምንጭ የእግር ኳስ ህይወቱን አሳልፏል። ያለፉትን ስድስት ወራት አርባምንጭን ለቆ በሲዳማ ቡና እምብዛም ስኬታማ ጊዜን ሳያሳለፍ ለአዲስ አዳጊው ክለብ ፈርሟል።

አንጋፋው አጥቂ ኄኖክ አየለም ዳግም የፖሊስ ተጫዋች ሆኗል። ኄኖክ ከዚህ ቀደም በደቡብ ፖሊስ ነበር እግር ኳስን የጀመረው። ወደ አዳማ ከተማ ካመራ በኋላ ያለፈውን የውድድር ዓመት በዲላ ከተማ ቆይቶ ወደ ቀድሞው አሰልጣኙ እና ክለቡ ተመልሷል። በተጨማሪም ብሩክ ተሾመ (ተከላካይ ከጅማ አባጅፋር) ፣ አሸናፊ ባልቻ (የግራ ተከላካይ ከካፋ ቡና) ፣ ዳኜ ዳንኤል (አጥቂ በባንክ ተስፋ ቡድን የነበረ) ፣ አረጋኸኝ ማሩ (ተከላካይ ከነጌሌ ከተማ) እና ዘነበ ኃይሌ (ተከላካይ ከካፋ ቡና) ክለቡን የተቀላቀሉ አዳዲስ ተጫዋቾች ናቸው፡፡

እስከ አሁን ከ16 በላይ የሚደርሱ ተጫዋቾችን ያመጣው ክለቡ አሰልጣኝ ዘላለም ከመምጣታቸው በፊት ፈርመው የነበሩት አሳምነው አንጀሎን እና ናትናኤል ጌታሁንን በተለያዩ ምክንያቶች ያሰናበተ ሲሆን እስከ አሁን አምና ከነበሩት ተጫዋቾቹ ሰባቱን ብቻ አስቀርቷል።