የኢትዮጵያ ዋንጫ ፍፃሜ – መከላከያ ከ ሀዋሳ ከነማ

የ2007 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ዋንጫ ነገ ፍፃሜውን ያገኛል፡፡ ባለፈው ማክሰኞ ተጋጣሚያቸውን አሸንፈው ወደ ፍፃሜው ያለፉት መከላከያ እና ሀዋሳ ከነማም የፍፃሜውን ጨዋታ አሸንፈው በ2016 ኮንፌድሬሽን ዋንጫ ለመካፈል ይፋለማሉ፡፡

መከላከያ ማክሰኞ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ባደረገው ጨዋታ 2-1 አሸንፎ ወደ ፍፃሜው አልፏል፡፡ በጨዋታው ጦሩ ከመመራት ተነስቶ አዲሱ ተስፋዬ እና በኃይሉ ግርማ በግንባር ባስቆጠሯቸው ግቦች ታግዞ አሸንፏል፡፡ በመጀመርያው አጋማሽ የተወሰደበትን ብልጫ ቀልብሶ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት በመውሰድ ጨዋታውን በበላይነት ለማጠናቀቅም ችሏል፡፡

አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ የሀዋሳን ጥንካሬ በማስታወስ ቡድናቸው በግማሽ ፍፃሜው የታዩበትን ድክመቶች አስተካክሎ እንደሚገባ ተስፋ አድርገዋል፡፡

‹‹ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ባደረግነው ጨዋታ በመጀመርያው አጋማሽ በተለይም የመጀመርያዎቹ 20 ደቂቃዎች ያሳየነውን ድክመት ከተጫዋቾቼ ጋር ተነጋግረን ለማስተካከል ጥረት አድርገናል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ማሸነፋችን በራሱ የተነሳሽነት እና የአሸናፊነት መንፈስ እንዲኖረን አድርጓል፡፡ በክረምቱ ስንዘጋጅ የነበረው ለፕሪሚየር ሊጉ ቢሆንም ጥሎ ማለፉን ማሸነፍም ግባችን ነው፡፡ አንዱን (የግማሽ ፍፃሜውን) ተወጥተናል፡፡ የሚቀረን የፍፃሜው ጨዋታ ነው፡፡ ሀዋሳ ከነማ ከአምናው ተሻሽሎ መጥቷል፡፡ በቡድኑ ላይ የቅርፅ ለውጥ ተመልክቻለሁ፡፡ ነገር ግን አላማችን ማሸነፍ በመሆኑ ጨዋታውን እናሸንፋለን፡፡ ›› ብለዋል፡፡

በጦሩ በኩል በግማሽ ፍፃሜው ያልተሰለፈው ግብ ጠባቂው ጀማል ጣሰው የመሰለፉ ጉዳይ አጠራጣሪ ሲሆን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በተደረገው ጨዋታ በእጁ ላይ በደረሰበት ጉዳት ተቀይሮ ከሜዳ የወጣው ተከላካዩ ቴዎድሮስ በቀለ እረፍት እንደሚያስፈልገው የተነገረው በመሆኑ በነገው ጨዋታ አይሰለፍም፡፡ ከጉዳቱ በማገገም ላይ የሚገኘው መሃመድ ናስርም የበአል እረፍት የተሰጠው በመሆኑ ለጨዋታው አይደርስም ተብሏል፡፡

ሀዋሳ ከነማ በ10 አመት ውስጥ የመጀመርያ የጥሎ ማለፍ ድል ለማሳካት ተስፋ በማድረግ ወደ ሜዳ ይገባል፡፡ ሀዋሳ ከነማ ከወላይታ ድቻ ጋር ባደረገው ጨዋታ ኳስ መስርቶ በዝግታ ወደ ተቃራኒ ቡድን መግባት እና ኳስን የሚቆጣጠር ቡድን ሆኖ ቀርቧል፡፡ የጨዋታ አቀጣጣይ ታፈሰ ሰለሞን እና ዋነኛ ግብ አግቢያቸው ተመስገን ተክሌ በጨዋታው አለመሰለፋቸው ቡድኑ በማጥቃትወረዳው ላይ ያለው አስፈሪነት ቢቀንሰውም ጠንካራ ቡድን ነው፡፡ ሌላኛው ኳስ በመቆጣጠር ከሚታወቀው መከላከያ ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ ምን መልክ ሊኖረው እንደሚችል መመልከትም ያጓጓል፡፡

አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት ቡድኑ ከወላይታድቻ ጋር ከነበረው አጨዋወት ለውጦች ይዞ ሊገባ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
‹‹ ሁሉንም ጨዋታዎች በአንድ አይነት ሲስተም አንጫወትም፡፡ እንደየቡድኖቹ ባህርይ የሚለዋወጥ እቅድ ይዘን ወደ ሜዳ እገባለን፡፡ መከላከያ ቅዱስ ጊዮርጊስን አሸንፎ የመጣ ጠንካራ ቡድን በመሆኑ በወላይታ ድቻ አይን ማየት አንችልም፡፡ ስለዚህ ለነሱ የሚሆን ቡድን ይዘን እንቀርባለን፡፡ ከዚህ ውጪ በአሰላለፍ ላይ የጎላ የሚባል ለውጥ አይኖርም፡፡ ›› ብለዋል፡፡ ውበቱ አክለውም ለረጅም ጊዜ ወደራቁበት የአፍሪካ ውድድር ለመመለስ በቡድኑ ውስጥ ያለው ተነሳሽነት ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

‹‹ ጨዋታው የፍፃሜ እንደመሆኑ መጠን ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተናል፡፡ በቡድኑ ላይ ያለውም ተነሳሽነት ጥሩ ነው፡፡ ክለቡ በአፍሪካ መድረክ ከተሳተፈ ረጅም ጊዜ አስቆጥሯል፡፡ እኛም ይህንን ለመቀየር ነው የምንጫወተው፡፡ ›› ሲሉ አስተያየታቸውን አጠቃለዋል፡፡

ሀዋሳ ከነማ ለወሳኙ የፍፃሜ ፍልሚያ የኮከቦቹን ተመስገን ተክሌ እና ታፈሰ ሰለሞንን ግልጋሎት አያገኝም፡፡ በድቻው ጨዋታ በጉዳት ምክንያት ያልተሰለፉት ሁለቱ ተጫዋቾች አሁንም ከጉዳት አላገገሙም፡፡

በቅጣት ምክንያት የድቻው ጨዋታ ያመለጠው አዲስ አለም ተስፋዬ ቅጣቱን ጨርሶ ለነገው ጨዋታ መሰለፍ የሚችል ሲሆን ባለፈው ማክሰኞ ለክለቡ የመጀመርያ የነጥብ ጨዋታውን ያደረገው ኤፍሬም ዘካርያስ በጉዳት ምክንያት ለነገው ጨዋታ የመሰለፉ ጉዳይ አጠራጣሪ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *