ሀዋሳ ከተማ የትጥቅ ድጋፍ ተደረገለት

የፕሪምየር ሊጉ ክለብ ሀዋሳ ከተማ ግምቱ ከመቶ አስር ሺህ ብር በላይ ወጪ የተደረገበት የትጥቅ ድጋፍ አገኘ።

በኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ የ2011 የውድድር ዘመን የመጀመርያ ሳምንት ጨዋታውን በሜዳው ወልዋሎን በፍፁም የበላይነት 3-0 በመርታት ዓመቱን በድል የጀመረው ሀዋሳ በከተማው በሚገኘው ባለ ሦስት ኮከቡ ሴንትራል ሀዋሳ ሆቴል ግምቱ ከመቶ አስር ሺህ ብር በላይ ወጪ የወጣበት ከእንግሊዝ የመጣ ሁለት ዓይነት (በሜዳው እና ከሜዳው ውጭ የሚለበስ) የማልያ ትጥቅ ተበርክቶለታል። ሀዋሳ ትላንት በመጀመርያው ጨዋታው አንደኛውን ማልያ በመልበስ ወደ ሜዳ እንደገባ መመልከት የተቻለ ሲሆን በቀጣይም መሰል የሆኑ ድጋፎች የሀዋሳ ሴንትራል ሆቴል እንደሚያደርግ ተነግሯል።

በሌላ ዜና የፈረሰኞቹ እና የብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች የሆኑት ጌታነህ ከበደ እና አብዱልከሪም መሐመድ ለቀድሞ ክለባቸው ደቡብ ፖሊስ ከግብፅ በሽመልስ በቀለ አማካኝነት ትጥቅ በማስመጣት ድጋፍ ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ለማወቅ ችለናል።