የአሰልጣኞች አስተያየት | ደቡብ ፖሊስ 1-2 መከላከያ

የኢትዮጵያ ዋንጫ እና አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን በማንሳት ዓመቱን የጀመረው መከላከያ ፕሪምየር ሊጉንም ከሜዳው ውጪ ደቡብ ፖሊስን በማሸነፍ በድል ጀምሯል። ሀዋሳ ላይ ከተደረገው ጨዋታ በኋላ የሁለቱን ቡድኖች አስተያየት እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

“ውጤቱ ቢያስደስተኝም ያሳየነው እንቅስቃሴ ግን ደካማ ነበር” ሥዩም ከበደ – መከላከያ

“ዛሬ ውጤቱ ቢያስደስተኝም ያሳየነው እንቅስቃሴ ግን ደካማ ነበር። የተጋጣሚያችንን እንቅስቃሴ ስላላወቅነው በተገቢ መልኩ መንቀሳቀስ አልቻልንም። እንደመጀመሪያ ጨዋታ እንደመሆኑ ከብዶናል፤ በቀጣይ ይስተካከላል። እኛ ከጫና ውስጥ ነበር የመጣነው ( ከጥሎ ማለፍ እና ከአሸናፊ አሸናፊዎች ዋንጫ ነው የመጣነው) ይህ ሁሉ እንድንዳከም ቢያደርገንም በውጤቱ ግን ኮርቻለሁ።

“የመርሐ ግብር አወጣጡ ፈታኝ ነው። ቀጣይ የምንጫወተው ከጅማ አባጅፋር ጋር ነው፤ ከዛ ደግሞ ከሬንጀርስ እንጫወታለን። በጅማው እና ሬንጀርሱ ጨዋታ መሀል ያለው ልዩነት የአምስት ቀን ልዩነት ነው። የመጀመሪያ ጨዋታችን ከሜዳ ውጭ መሆኑ ጥሩ ቢሆንም የመርሀ ግብሩ መደራረብ ግን ከባድ ነው። ”


“የልምድ ማነስ እንጂ ጥሩ ተንቀሳቅሰናል” ዘላለም ሽፈራው – ደቡብ ፖሊስ

“ጨዋታው ጥሩ ነበር ጥሩ ተንቀሳቅሰናል። ከመጀመሪያው አጋማሽ ይልቅ በሁለተኛው አጋማሽ ተቆጣጥሮ ለመውጣት ጥረት አድርገናል። በተለይ በብሩክ በኩል በርካታ ያለቀላቸውን ኳሶች ፈጥረናል። ያን ወደ ግብነት መለወጥ አልቻልንም። አብዛኛው የቡድኔ ስብስስብ ከከፍተኛ ሊግ የመጡ ናቸው። ዛሬ እንደክፍተት የልምድ ማነስ እንጂ ጥሩ ተንቀሳቅሰናል። ከኛ በተሻለ መልኩ እነሱ በቡድናቸው ልምድ ያላቸው ተጫዋቾችን ያካተተ ነው። እኛ እንደጅምር ጥሩ ነን፤ በቀጣይ ጨዋታ አዳሙ፣ አበባው እና ሌሎች የሚቀላቀሉም ስላሉ እነሱን ከጨመርን ጥሩ እንሆናለን ብዬ አስባለው።