ከፍተኛ ሊግ | የካ ክፍለ ከተማ 13 ተጫዋቾች አስፈርሟል

የ10 ተጫዋቾቹን ውል ያራዘመው የካ 13 አዳዲስ ተጫዋቾችንም ወደ ቡድኑ ቀላቅሏል።

በ2010 የውድድር ዓመት ወደ ከፍተኛ ሊግ ማደግ የቻለው የካ ክፍለ ከተማ ወጣ ገባ አቋም በማሳየት ነበር ዓመቱን ያጠናቀቀው። የካ ዘንድሮ በማዕከላዊ እና ደቡብ ምስራቅ ምድብ የተመደበ ሲሆን አስር ሦስት ተጫዋቾችን ለአንድ ዓመት በሚቆይ ውል ሲያስፈርም የአስር ተጫዋቾቹን ውል ደግሞ አራዝሟል። በሌላ ዜና ደግሞ የክለቡ ዋና አሰልጣኝ ባንተይርጋ ጌታቸው ከ2005 ጀምሮ ቡድኑን በማስልጠን የቆዩ ሲሆን በ2010 ያበቃ የነበረው ውላቸው ለአንድ ዓመት እንዲራዘም ተደርጓል።

የክለቡ አዳዲስ ፈራሚዎች ሮቤል ዳንኤል (ከዲላ ከተማ ተከላካይ) ፣ አንተነህ ከተማ (ከደደቢት ተስፋ ተከላካይ) ፣ ኤፍሬም ማሞ (ከደደቢት ተስፋ አጥቂ) ፣ ማሀሪ ዮሴፍ (ከአርባምንጭ ከተማ ተከላካይ) ፣ ናትናኤል ተፈራ (ከአዲስ አበባ ከተማ ግብ ጠባቂ) ፣ ኢብራሂም ባዱ (ከአራዳ ክፍለ ከተማ አማካይ) ፣ ካሳሁን ገብረሚካኤል (ከወልቂጤ ከተማ ተከላካይ) ፣ ታረቀኝ ታደሰ (ከድሬዳዋ ፖሊስ ተከላካይ) ፣ ነቢል ኢብራሂም (ከአዲስ ከተማ አማካይ) ፣ ብሩክ ብርሃኑ (ከደደቢት ተስፋ አጥቂ) ፣ ዘውዱ ሀብታሙ (ተከላካይ) ፣ ኃይማኖት ሰይፉ (ከነጌሌ ከተማ ተከላካይ) እና ታደሰ ያለው (ከንፋስ ስልክ ከተማ ግብ ጠባቂ) ናቸው።

ከመስከረም 20 ጀምሮ ዝግጅቱን በአዲስ አበባ የጀመረው የካ ክፍለ ከተማ በቀጣይ ቀናት ወደ ሆሳዕና በማቅናት ዝግጅቱን እንደሚቀጥል ታውቋል። በተጨማሪም ክለቡ በ2011 የውድድር ዓመት የሚጠቀመው የኦሜድላን ሜዳ መሆኑም ታውቋል።