ጌታነህ ከበደ ለጋናው ጨዋታ አይደርስም

ለ2019 የካሜሩን አፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ የምድብ አምስተኛ ጨዋታውን ከጋና ጋር ለመጫወት ዝግጅት እያደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በጉዳት ምክንያት ጌታነህ ከበደን አይጠቀምም።

የፊታችን እሁድ ጋናን በአዲስ አበባ ስታድየም የሚያስተናግደው ብሔራዊ ቡድኑ ከጥቅምት 27 ጀምሮ ዝግጅቱን እያደረገ ይገኛል። የቡድኑ አምበል ጌታነህ ከበደ ብሔራዊ ቡድኑን ከተቀላቀለበት ጊዜ ጀምሮ ባጋጠመው መጠነኛ ጉዳት በህክምና ባለሙያው በይስሀቅ ሽፈራው በሚሰጠው ሙያዊ ድጋፍ ከቡድኑ አባላት ተነጥሎ ያለፉትን ቀናት ልምምድ ሲሰራ መቆየቱ ይታወሳል።

ጌታነህ ምንም እንኳ ከጉዳቱ ያገገመ ቢሆንም ለጨዋታው ብቁ የሚያደርገውን የተሟላ ልምምድ አለመስራቱን ተከትሎ ከእሁድ የጋና ጨዋታ ውጭ መሆኑን ለማረጋገጥ ችለናል።