ሶከር መፅሀፍት | ኢንቨርቲንግ ዘ ፒራሚድ (ምዕራፍ ሁለት – ክፍል አንድ)

በዝነኛው እንግሊዛዊ የእግርኳስ ፀኃፊ ጆናታን ዊልሰን የተደረሰውና በእግርኳስ ታክቲክ ዝግመታዊ የሒደት ለውጦች ላይ የሚያተኩረው Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics የተሰኘውን መጽሃፍ በትርጉም እያቀረብንላችሁ እንገኛለን። ባለፉት አራት ተከታታይ ክፍሎች የመጽሀፉን ምዕራፍ አንድ ማቅረባችን የሚታወስ ሲሆን ከዚህ መሰናዶ ጀምሮ የምዕራፍ ሁለት ጽሁፎችን በተከታታይ እናቀርብላችኋለን፡፡ መልካም ንባብ!


|| የመፅሀፉን ክፍል አራት ለማንበብ ይህን ይጫኑ ምዕራፍ አንድ- ክፍል አራት

ምዕራፍ ሁለት

ክፍል አንድ: ዋልዝና ታንጎ

እግርኳስ የያዘውን ኃያል የጽንወት አቅም ለመቋቋም የተሳናት እንግሊዝ ብቻ አልነበረችም፡፡ የሃገሪቱ ዜጎች የንግድና ማህበራዊ እሴቶች ልውውጥ ለማከናወን በሚሄዱባቸው ሌሎች መዳረሻዎች በሙሉ ጨዋታውን የማስተዋወቅ እድል ፈጥረዋል፡፡ ይህ ሒደት ደግሞ በሃገሪቱ ንጉሰ ነገስታዊ ግዛት ውስጥ ብቻ አልተገደበም፡፡ በወቅቱ እንግሊዝ መዳብን ከቺሊ ወደ ሌሎች ሃገራት በመላክ ከሚገኘው ግዙፍ ምጣኔ ሀብት ተቋዳሽ  ነበረች፡፡ ለማዳበሪያነት የሚያገለግል የአዕዋፋት ኩስ- ከፔሩ፥ ስጋ፣ሱፍና ቆዳ- ከአርጀንቲና እና ኡሯጓይ፥ ቡና ከብራዚል እና ኮሎምቢያ ወደ ተቀረው አለም እየወሰደች በመሸጥ ትርፋማ ሆነች፡፡ ይህንን መጠነ ሰፊ የገንዘብ ዝውውር ለመቆጣጠር እንዲያስችላትም በየቦታው ባንኮችን ከፈተች፡፡ በ1880ዎቹ ሃያ በመቶ የሚሆነው የብሪታንያ የውጭ መዋዕለ ንዋይ ፍሰት ለደቡብ አሜሪካ የተመደበ ነበር፡፡ በ1890 በአርጀንቲናዋ ርዕሰ-መዲና ብዌኖስ አይረስና አካባቢዋ የሚኖሩ ወደ አርባ አምስት ሺህ የሚጠጉ ብሪታኒያውያን የነበሩ ሲሆን ከእነዚህ በተጨማሪ ቁጥራቸው አነስተኛ ቢሆንም በሳኦፓውሎ፣ ሪዮዲጂኔይሮ፣ ሞንቴቪዲዮ፣ ሊማና ሳንቲያጎ የከተሙት እንግሊዛውያን እግርኳሳዊ ተጽዕኖዋቸው ቀላል አልነበረም፡፡ እነዚህ ዜጎች መደበኛ ስራቸውን እየከወኑ ጋዜጦች፣ ስፖርት ማዘውተሪያዎች፣ የእግርኳስ ቡድኖች፣ ትምህርት ቤቶችና የህክምና ተቋማትን መመስረት ጀመሩ፡፡ ቀስ በቀስም የደቡብ አሜሪካን ተፈጥሮአዊ ሀብቶች በዝብዘው በምትኩ እግርኳስን አስፋፉ፡፡

በአውሮፓም ታሪኩ ተመሳሳይ ይዘት አሳይቷል፡፡ አንድ ቦታ ላይ በዲፕሎማሲ፣ ባንኪንግ፣ ንግድና የምህንድስና ስራዎች የተሰማሩ ማናቸውም የብሪታንያ ዜግነት ያላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ካሉ ያለጥርጥር እግርኳስ አብሯቸው ይኖራል፡፡ የመጀመሪያው የቡዳፔስት ክለብ <ኧጅፔስት> በ1885 ጂምናዚየም ውስጥ ከተቋቋመ ጥቂት ጊዜያት በኋላ <ኤም.ቲ.ኬ.> እና <ፌሬንክቫሮስ> ተመሰረቱ፡፡ በመሀለኛው የአውሮፓ ክፍል ደግሞ የብሪታንያ መዳረሻ ማዕከል ቪየና ሆና ነበር፡፡ በቆንጽላዎች፣ ባንኮችና ግንባታው ዘርፍ ያሉ ድርጅቶች ውስጥ የሚሰሩ ባለሙያዎችና ንግድ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ጨዋታውን በማስፋፋት ረገድ የቀዳሚነት ሚና ያዙ፡፡ በህዳር 15-1894 በኦስትሪያ የመጀመሪያው እግርኳስ ግጥሚያ በቪየናው የክሪኬት ክለብና ከ<ባሮን ሮዝቺልድ> ግዛት በመጡ አትክልተኞች መካከል ተደረገ፡፡ በከተሞች ውስጥ የታየው እግርኳሳዊ ፍላጎት ከፍ እያለ ሲሄድም በ1911 ይህ የክሪኬት ክለብ <ዌይነር አማተር> ወደ ተሰኘ የእግርኳስ ቡድንነት ተቀየረ፡፡ በቼክ በሁሉም እድሜ ክልል የሚገኙ ስፖርቶኞችን የሚያሳትፍ፣ በሰውነት መተጣጠፍና መገለባበጥ ላይ የሚያተኩርና የ<ተርኒን-ጂምናስቲክ> አካል የሆነ <ሶኮል> ተብሎ የሚታወቅ እንቅስቃሴ ነበር፡፡ እግርኳስ እንግዲህ ከዚህ በጀርመንም ዝነኛ ከነበረው ብሄርተኛ ስፖርታዊ ንቅናቄ ጋር ተቀባይነት የማግኘት ፍልሚያ ማድረግ ተጠበቀበት፡፡ ሆኖም ከርዕሰ መዲናዋ ፕራግ  ወደ ለንደንና ቪየና ከተሞች የሚያቀኑ ወጣት ምሁራን ቁጥር እያደገ በመምጣቱ በሃገሪቱ የእግርኳስ ጨዋታ ወዲያውኑ ስር መስደድ ቻለ፡፡ በ1897 ከ<ሃብስበርግ> ግዛት የሚመጡ ቡድኖች በሙሉ ተሳታፊ የሚሆኑበት የ<ደር ቻሌንጅ ዋንጫ> መጀመር በሰዎች ዘንድ የነበረውን ከፍ ያለ የእግርኳስ ፍላጎት ይበልጡን ወደ ላቀ ደረጃ አሻገረው፡፡

እንግሊዛዊነትን የሚያቀነቅኑ ዴንማርካውያን፣ ደቾችና ሲውዲኖች ጨዋታውን በአግባቡ ተቀብለው በፍጥነት ሊላመዱት ቻሉ፡፡ ዴንማርኮች  እንዲያውም በ1908ቱ ኦሎምፒክ የብር ሜዳሊያ በመውሰድ በስፖርቱ ዘርፍ የነበራቸውን ብቃት ሊያሳዩ በቁ፡፡ ሆኖም ግን ሃገራቱ የብሪታኒያን እግርኳስ አጨዋወት መንገድ ከመከተል ባለፈ የተለየ ታክቲካዊም ሆነ ሌላ የአቀራረብ ስልትን የሚያስቃኝ ምንም አይነት ሙከራ አላደረጉም፡፡  በአስራ ዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ በደች የነበሩ የስፖርት ክለቦችን ምስሎች ስንመለከት በንግስት ቪክቶሪያ ዘመን የታየውን  እንግሊዝ-ነክ የሆኑ ጥበባዊ ስራዎች መለያ ግልባጭ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በፎቶግራፎቹ ላይ በተጫዋቾቹ ችላ የተባለና በግዴለሽነት የተያዘ ዥርግግ ያለ የከንፈር ጺም ይታያል፡፡ ማርቲን ቫን ቦተንበርግና ቤቨርሊ ጃክሰን የተባሉ ተሳታፊዎችን በመጥቀስ <ግሎባል ጌምስ> የተሰኘው መጽሄት እንዳስቀመጠው ሐሳብ ከሆነ የስፖርቱ አላማ ”በውቡ የደች መሬት ላይ በእንግሊዛውያኑ ልማድና እቅድ መሰረት ልክ እንደ እነርሱ (እንግሊዞቹ) መጫወት ነበር፡፡” ይህ ደግሞ አስመስሎ መቅረብን የሚወክል እንጂ ለግኝትና ፈጠራ ቦታ የሚሰጥ የእግርኳስ ወቅት እንዳልነበር ማሳያ ነው፡፡

በማዕከላዊ አውሮፓና በደቡብ አሜሪካ የእንግሊዞች አጨዋወት ስልት ላይ ጥርጣሬን የማሳደር አዝማሚያ ይታይ ስለነበር በእግርኳስ ሒደታዊ የእድገት ለውጥ መታየት ጀመረ፡፡ 2-3-5 ፎርሜሽን ጥቅም ላይ የመዋሉ ነገር ተጠናክሮ ቢቀጥልም እንቅስቃሴያዊ የተጫዋቾች አደራደር መዋቅርን ከማመልከት ያለፈ ፋይዳው እምብዛም በመሆኑ የአጨዋወት ዘይቤም የራሱ የሆነ ድርሻ ኖረው፡፡ ሌሎች ሃገራት ብልሀታዊና ጥበባዊ የእግርኳስ ጨዋታ አቀራረብ አማራጮችን ሲያዳብሩ ረጃጅም ቅብብሎች ላይ ጥገኛ የሆነ ስልትን በመቀበልና 2-3-5 ፎርሜሽንን በማስፋፋት ረገድ ከፍ ያለ ሚና የነበራት ብሪታንያ የተክለሰውነት ጥንካሬ ላይ ያመዘነውን የአጨዋወት ዘዴ የሙጥኝ ብላ ቀጠለች፡፡

በማዕከላዊው የአውሮፓ ክፍል የነበረውን እግርኳስ ከሌሎች ለየት እንዲል ያደረገው በከተሞች ውስጥ ይኖር በነበረው የሰራተኛው መደብ ያገኘው ፈጣን ተቀባይነት ነበር፡፡ ምንም እንኳ የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ፣ ሳውዝአምፕተን፣ ኮረንቲያንስ፣ቶተንሐምና ኤቨርተንን የመሳሰሉ ክለቦች ያደረጓቸው ጉዞዎች እንዲሁም የተለያዩ አሰልጣኞች ወደ አህጉሪቱ መሃል ሃገራት መድረስ የብሪታንያን እግርኳሳዊ ተጽዕኖ ዘላቂ እንዲሆን ቢረዳውም በእንግሊዝ ህዝብ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የተንሰራፋው የእግርኳስ አስተምህሮ በመሀል አውሮፓ ጨዋታውን ያዘወትሩ በነበሩ ሰዎች ዘንድ የሰረጸ አልነበረም፡፡ ይህም ከአካባቢው የተገኙትን ተጫዋቾች “ትክክለኛው የአጨዋወት መንገድ” በሚል ቅድመ ግንዛቤ ያልተያዙ እንዲሆኑ አግዟቸዋል፡፡

በመሃለኛው የአህጉሪቱ ክፍል የሚገኙ ሃገራትን የበለጠ እድለኛ የሚያሰኛቸው ስኮትላንዳውያን ትልቅ እግርኳሳዊ አሻራ ስላሳረፉባቸው ነው ፡፡ የጨዋታቸውን የትኩረት ማዕከል ፈጣንና አጫጭር ቅብብሎች ላይ የሚያጠነጥን እንዲሆን ለማድረጋቸውም አርአያ ሆነዋቸዋል፡፡ ለምሳሌ ያህል በፕራግ ከተማ ጂም ክሬይግ <ኤ ላየን ሉክስ ባክ> መጽሄት ላይ የእርሱ ዘመን “ባለ ብዙ ክህሎት የኳስ ጥበበኛ!” ሲል የገለፀው የቀድሞው የሴልቲክ የግራ መስመር አጥቂ ጆን ማደን በ1905 እና በ1938 መካከል በነበሩት አመታት ስላቪያ የተባለውን የመዲናዋን ክለብ አሰልጥኗል፡፡ በአንድ ወቅት ለኤርድሮኒያንስና አርሰናል የተጫወተው ሌላኛው የአገሩ ልጅ ጆን ዳይክ ደግሞ በ1919 እና 1933 መካከል ለሁለት ጊዜያት ያህል ስፓርታን መምራት ችሏል፡በኦስትሪያም ቀደም ብሎ በ1905 የተለያዩ ጉዞዎች ሲፈጽም የነበረውን የሬንጀርስ የእግርኳስ አቀራረብ ዘይቤ ለማስመሰል አልያም ለመውሰድ ሆን ተብሎ የሚደረግ ጥረት ነበር፡፡

ይቀጥላል…


ስለ ደራሲው 

ጆናታን ዊልሰን ዝነኛ እንግሊዛዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ሲሆን በተለያዩ ጋዜጦች፣ መጽሄቶች እና ድረገጾች ላይ ታክቲካዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው የእግርኳስ ትንታኔዎችን የሚያቀርብ ጉምቱ ጸኃፊ ነው፡፡  ባለፉት አስራ ሁለት ዓመታትም የሚከተሉትን ዘጠኝ መጻህፍት ለህትመት አብቅቷል፡፡

-Behind The Curtain: Travels in Eastern European Football (2006)

-Sunderland: A Club Transformed (2007)

-Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics (2008)

-The Anatomy of England (2010)

-Brian Clough: Nobody Ever Says Thank You: The Biography (2011)

-The Outsider: A History of the Goalkeeper (2012)

-The Anatomy of Liverpool (2013)

-Angels With Dirty Faces: The Footballing History of Argentina (2016)

-The Barcelona Legacy: Guardiola, Mourinho and the Fight For Football’s Soul (2018)

ቀደምት ምዕራፎች
መቅድም LINK
ምዕራፍ 1 – ክፍል አንድ LINK
ምዕራፍ 1 – ክፍል ሁለት LINK
ምዕራፍ 1 – ክፍል ሶስት LINK
ምዕራፍ 1 – ክፍል አራት LINK