ኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል የመሃል ተከላካይ ዋሊድ አታ ክለቡ ጊንኪልቢርጊ በቱርክ ሱፐር ሊግ ጨዋታ ካይሰርሪስፖርን በሙስጠፋ ኤል ካቢር 2 ግቦች ታግዞ ባሸነፈበት ጨዋታ ሳይሰለፍ ቀርቷል፡፡ ዋሊድ ከቡድኑ ውጪ ሆኖ ጨዋታውን ተከታትሏል፡፡ ጊንኪልቢርጊ በቱርክ ሱፐር ሊግ በሰባት ጨዋታ 7 ነጥብ በመያዝ 13 ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
በህንድ ሂሮ ሱፐር ሊግ የአዲሱን የውድድር ዘመን የመክፈቻ ጨዋታ ላይ ለቼኔይን ተሰልፎ የተጫወተው ፍቅሩ ተፈራ ብድኑ ሳይሳካለት በአምናው የሊጉ ሻምፒዮን አትሌቲኮ ደ ኮልካታ 3-2 በሆነ ውጤት ተሸንፏል፡፡ ፍቅሩ በጨዋታው ላይ ግብ ማስቆጠር አልቻለም፡፡ ለአትሌቲኮ ደ ኮልኮታ የማሸነፊያ ግቦቹን ፓርቹጋላዊው የቀድሞ የስፓርቲንግ ሊዝበን እና ቫሌንሲያ አጥቂ ሄልደር ፓስቲጋ እና ስፔናዊው ቫልዶ አስቆጥረዋል፡፡ ለቼኔይን ብራዚልያዊው ኤላኖ እና ጄጄ ላፔክሉሃ ሁለቱን ግቦች አስቆጥረዋል፡፡ ፍቅሩ የመጀመሪያውን የህንድ ሂሮ ሱፐር ሊግ ግብ ያስቆጠረ ተጫዋች መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡ በመጀመሪያው የህንድ ሂሮ ሱፐር ሊግ ውድድር ዓመትም ከምዕራብ ቤንጋሉ ክለብ አትሌቲኮ ደ ኮልካታ ጋር የሊጉ ሻምፒዮን ነበር፡፡
ጌታነህ ከበደ ከደቡብ አፍሪካው ኪክኦፍ ጋዜጣ ጋር ባደረገው ቆይታ ለአማተክስ 10 ግቦችን ለማስቆጠር ማለሙን ተናግሯል፡፡ ጌታነህ ለተክስ በ4 ጨዋታዎች ላይ ተጫውቶ ግብ ማስቆጠር አልቻለም፡፡ አንድ ለግብ የሚሆን ኳስ ግን አመቻችቶ አቀብሏል፡፡ አማተክስ በዚህ ሳምንት በቴሌኮም ካፕ ከኦርላንዶ ፓይሬትስ ሊያደርግ የነበረው ጨዋታ ለሌላ ጊዜ ተላልፏል፡፡ ፓይሬትስ ከግብፁ አል አሃሊ ጋር ባለበት የካፍ ኮንፌድሬሽን ካፕ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ለቴሌኮም ካፕ ጨዋታው መራዘም ምክንያት ነው፡፡