ሶከር መፅሀፍት | ኢንቨርቲንግ ዘ ፒራሚድ (ምዕራፍ ሁለት – ክፍል ሦስት)

በዝነኛው እንግሊዛዊ የእግርኳስ ፀኃፊ ጆናታን ዊልሰን የተደረሰውና በእግርኳስ ታክቲክ ዝግመታዊ የሒደት ለውጦች ላይ የሚያተኩረው Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics የተሰኘውን መጽሃፍ በትርጉም እያቀረብንላችሁ እንገኛለን። በዚህ ሳምንትም የምዕራፍ ሁለትን ሦስተኛ ክፍል ይዘን ቀርበናል፡፡


|| ያለፈውን ሳምንት ለማንበብ ይህን ይጫኑ ምዕራፍ ምዕራፍ ሁለት – ክፍል ሁለት

የእንግሊዝ እግርኳስ ማህበር ሲጠቀምባቸው የነበሩ የጨዋታ ህግጋት በ1867 ወደ አርጀንቲና ተዛመቱ፡፡ በእንግሊዘኛ ቋንቋ በሚታተመው <ዘ-ስታንዳርድ> የተሰኘ ጋዜጣ ላይም መውጣት ጀመሩ፡፡ በዚያው ዓመት መጨረሻ ለዋና ከተማው  የክሪኬት ክለብ ቅርንጫፍ ሆኖ ለማገልገል የብዌኖስ አይረስ እግርኳስ ክለብ ተመሰረተ፡፡ ሆኖም የተዘራው ዘር የማያፈራ መሬት ላይ የተበተነ ይመስል ከስድስት ዓመታት ቆይታ በኋላ እግርኳስ ክለቡ ወደ ራግቢ ቡድንነት ተቀየረ፡፡  ከኤደንብራ ዩኒቨርሲቲ ተመርቆ ወደ ሃገሪቱ በመምጣት በቅዱስ አንድሪያስ የስኮትላንዳውያን ትምህርት ቤት መምህር ለነበረው አሌክሳንደር ዋትሰን ሃተን ምስጋና ይግባና በ1880ዎቹ መነሻ እግርኳስ በድጋሚ በአርጀንቲና ማቆጥቆጥ ጀመረ፡፡ ሃተን የሚሰራበት ትምህርት ቤት የመጫወቻ ሜዳውን የማስፋፋት እቅድ እንደሌለው ባወቀ ጊዜም የስራ መልቀቂያ ደብዳቤ አስገባ፡፡ ከዚያም በ1884 የእንግሊዞች ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን አቋቋመና በእግርኳስ ስልጠና የበቁ ባለሙያዎች መቅጠሩን ተያያዘው፡፡ በ1893 የአርጀንቲና እግርኳስ ማህበር ሊግ ቀድሞ በነበረው አሰራር ላይ አዳዲስ ማሻሻያዎችን አድርጎ እንደገና ሲመሰረት ሃተን ዋና ተዋናይ መሆን ቻለ፡፡ ቀስ በቀስ ከእንግሊዛውያኑ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተሰባሰቡ ተለቅ-ተለቅ ያሉ ወጣቶች <አሉሚኒ> የተባለ ቡድን መስርተው በአንደኛ ዲቪዚዮን መወዳደር ጀመሩና በሃያኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ የነበሩትን አመታት በውጤታማነታቸው ዘለቁ፡፡ በነዚህ ጊዜያት ትምህርት ቤቶቹን የወከለው ቡድን እንኳ የሚወዳደረው በታችኛው የሊግ እርከን ላይ ነበር፡፡ በሒደት ለእግርኳስ አጽንዖት ሰጥተው የሚፎካከሩ የትምህርት ቤት ቡድኖች እነርሱ ብቻ መሆናቸው ቀርቶ ከመጀመሪያዎቹ ሰባት ተከታታይ የውድድር አመታት ስድስቱ በክቡር ሎማስ ዲ ዛሞራ አዳሪ ትምህርት ቤት ዙሪያ በተመሰረቱ ሌሎች ቡድኖች አሸናፊነት የተጠናቀቀ ሆነ፡፡

በዩሯጓይ ሪቨርፕሌት ዙሪያ የነበረውም ታሪክ ተመሳሳይ ሁኔታን አሳይቷል፡፡ በሌላ የስራ መስክ የተሰማሩ ወጣት ብሪታኒያውያን የክሪኬትና ጀልባ ቀዘፋ ውድድሮች ላይ የሚካፈሉ ክለቦችን አቋቋሙ፡፡ በዚህ ወቅት የእንግሊዝ ትምህርት ቤቶች ከእነዚህ ስፖርቶች ጎን ለጎን እግርኳሱ ቦታ እንዲያገኝ ግፊት አሳደሩ፡፡ ይህም ሁኔታ ጨዋታው እድገት የሚያሳይበትን መንገድ አመቻቸ፡፡  የእንግሊዛውያን ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት መምህር የነበረው ዊሊያም ሌዝሊ ፑል በሞንቴቪዲዮ ከተማ እግርኳስን በማስፋፋት ረገድ የጎላ ሚና ተጫወተ፡፡ ፑል በግንቦት 1891 የአልቢዮን ክሪኬት ክለብን ካቋቋመ በኋላ በስሩ የእግርኳስ ቡድን መስርቶ ከብዌኖስ አይረስ ከሚመጡ ሌሎች ቡድኖች ጋር ግጥሚያዎችን እንዲያከናውን አደረገ ፡፡

በእነዚያን ቀደምት ዓመታት የነበሩ እግርኳስ ቡድኖች ውስጥ የተጫዋቾች አሰላለፍ የሰፈረባቸውን ሰነዶች በወፍ በረር ቃኘት ብናደርግ ተጫዋቾቹ በአብዛኛው እንግሊዛውያን አልያም ደግሞ እንግሊዝኛ-ተናጋሪ አርጀንቲናውያን ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ይህም እንግዲህ የወቅቱ  እግርኳስ መለያ ባህል ሆነ፡፡ በአርጀንቲና ስለነበረው አማተር እግርኳስ ታሪክ ባወሳበት መጽሃፉ ሆርጌ ኢዋንዡክ አላማው “ጥልቅ ባልሆነ ስሜትም ቢሆን ጥሩ መጫወትና ስፖርታዊ ጨዋነትን ማስፈን ነበር፡፡” ሲል ይናገራል፡፡ በአንድ ወቅት አሉሚኒዎች ከኢስቱዲያንቴስ ጋር ባደረጉት ጨዋታ ያገኙት ፍጹም ቅጣት ምት ያገኛሉ፡፡ ነገር ግን “ተገቢ ያልሆነ ውሳኔ ተወስኗል!” ብለው በመሟገታቸው ለመምታት አመነቱ፡፡ በጊዜው የሁሉም ትኩረት ነገሮች <በትክክለኛ አቅጣጫቸው> እንዲጓዙ የመሻት ስነምግባርን ማስፈን ላይ ነበር፡፡ ይህ እምነትና አስተሳሰብ ታክቲካዊ በሆኑ ጉዳዮች ውስጥም ሰርፆ ተቀመጠ፡፡ 2-3-5 ፎርሜሽንም አለምአቀፋዊ የተጫዋቾች የሜዳ ላይ አደራደር ቀኖና ተደርጎ ተወሰደ፡፡ በ1904 <ዘ-ብዌኖስ አይረስ ሄራልድ> የብሪታንያ ተጓዥ ቡድን የነበረው ሳውዛምፕተን በአርጀንቲና ምድር ባደረገው የመጀመሪያ ጨዋታ በአልሙኒ ላይ የተቀዳጀውን የ3-0 ድል አስመልክቶ በሰራው ሰፊ ዘገባ የህዝብ ትምህርት ቤቶች እግርኳሳዊ ተጽዕኖ ከፍተኛ መሆኑን ግልጽ አድርጎ አልፏል፡፡ “ብሪታንያ ከሁሉ የተሻለች ሆና የመገኘቷ ምስጢር ዜጎቿ አብሯቸው የተፈጠረ  ነገሮችን በጀብደኝነት የመከወን ፍቅር ስላላቸው ነው፡፡” ብሏል የጋዜጣው ርዕሰ አንቀጽ፡፡

ይሁን እንጂ ቀስ በቀስ የእንግሊዝ የበላይነት እየተዳከመ ሄደ፡፡ የአርጀንቲና እግርኳስ ማህበር-አፋ(AFA) በ1903 የስራ ቋንቋውን ስፔንኛ አደረገ፡፡ ከሁለት አመት በኋላም የዩሯጓይ እግርኳስ ማህበር ተመሳሳዩን ዱካ ተከተለ፡፡ አሉሙኒዎችም በ1911 ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ወደቁ፡፡ በቀጣዩ አመትም አፋ <አሶሲዮን ዴል ፉትቦል አርጀንቲና> በሚል የስፓኝ ቋንቋ ስያሜውን ቀየረ፡፡ እስከ 1934 ድረስ የእንግሊዘኛው ፉትቦል (Football) አጻጻፍ እንደነበረ ሰንብቶ በዚሁ አመት መጨረሻ በስፓኝ ቋንቋ ቅላጼ ፉዝቦል (futbal) ወደሚል ቃል ተለወጠ፡፡ ዩሯጓውያንና አርጀንቲናውያን እንግሊዞቹ አካላዊ ኃይል ወይም ጉልበት ላይ የሚያሳዩትን ጥብቅ እምነት በፍጹማዊ ሐሳብነት የመመልከት ተፅእኖ ሳያርፍባቸው፣ “አካላዊ ብልጫ የሞራል ልዕልና መገለጫ ነው!” የሚል ስሜት ሳይገዛቸውእና ለቴክኒካዊ ብልሃት አመኔታ ሳያጡ የራሳቸውን እግርኳሳዊ አቋም አንጸባረቁ፡፡ ሁሉም የሚጠቀሙበት የተጫዋቾች የሜዳ ላይ አደራደር ቅርጽ ተመሳሳይ ቢሆን እንኳ ዘይቤ ግን የሚቻለውን ያህል የተለያየ መልክ ሊኖረው ግድ ሆነ፡፡ የማህበራዊ ሳይንስ ተመራማሪው ኤድዋርድ አርቼቲ ” የስፔንና ጣልያን ስደተኞች ተጽዕኖ ፈጣሪነት እያደገ ስለመምጣቱ መታሰብ ሲጀመር ኃይልና ጥብቅ ስርዓት ተዘንግተው ማራኪ አቀራረብና ክህሎት ቦታ ተሰጣቸው፡፡ ይህም በተለያዩ አስተምህሮዎች ላይ የሚታይ መደበኛ ልማድ ነበር፡፡” ሲል ይወተውታል፡፡

ዩሯጓዊው ገጣሚና ጋዜጠኛ ኤድዋርዶ ጋሊያኖ ደግሞ ” እንደ አዝናኙና አስደሳቹ የጭፈራ አይነት ታንጎ፥ እግርኳስም በጭርንቁስ መንደሮች ማበብ ቻለ፡፡” በማለት ጻፈ፡፡የተለያዩ ሁኔታዎች ጉራማይሌ የእግርኳስ አቀራረብ ዘይቤዎች እንዲገኙ ሰበብ ሆነዋል፡፡ በእነዚያ የገዳማት አመቺና ሰፋፊ ሜዳዎች የሚከናወኑ ጨዋታዎች በእንግሊዝ የህዝብ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ባሉ ሜዳዎች ከሚደረጉት አንጻር ልዩነቶች ተስተዋሉባቸው፡፡ በተጻራሪው በብዌኖስ አይረስና ሞንቴቪዲዮ ድሃ ሰፈሮች ባልተስተካከሉትና ሻካራ በሆኑት ውስን ቦታዎች ላይ በሚገኙ መጫወቻ ስፍራዎች የተለየና የላቀ ክህሎት ዳበረ፡፡ አዲስ ዘይቤም ተፈጠረ፡፡ “ሚሎንጋ በተባሉት የምሽት ክበቦች እንደተገኙት ሃገራዊ የጭፈራ አይነቶች ሁሉ ሃገር-በቀል የእግርኳስ አጨዋወት መንገዶችም  ተፈጠሩ፡፡” በማለት ጋሊያኖ ያወጋል፡፡ “ዳንኪረኞች አራት ማዕዘን ቅርጽ ባለው የሸክላ ንጣፍ በተለበጠ ወለል በሚገኝ ውስን ስፍራ ላይ በከበረ ድንጋይ የሚሰራ ረቂቅ ጌጥ ይስላሉ፡፡ እግርኳሰኞችም እግራቸውን ሌጦ እንደሚጎነጉኑ እጆች ተጠቅመው በዚያች ውስን ቦታ ኳሷን በርቀት ከመምታት ይልቅ ራሳቸው ጋር ሲይዙ አልያም የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ሲኖራቸው ጥሩ መግባባት ላይ ይደርሳሉ፡፡ ጥዑም የሙዚቃ ድምፅ ለመፍጠር የጊታር ክሮች ላይ የተመጠነ ቅኝት እንደሚደረግባቸው ሁሉ ኳሱም በዚያ ስልት የራሱ ለዛ እንዲኖረው አዳዲስ ዘይቤዎች ተወለዱ፡፡ አጫጭርና ፈጣን ቅብብሎች የኳስ ንክኪዎችን ማራኪ ይዘት አላበሳቸው፡፡” ሲልም ያክላል፡፡

ለተለያዩ ባህሪያት ቅድሚያ ከመስጠት አንጻር ሁለቱ ስልቶች ተጣጥመው አብረው ሊጓዙ አልቻሉም፡፡ አዲስና ነባር ሐሳቦ ሲገናኙም ግጭቶች መፈጠራቸው የማይቀር ሆነ፡፡ ይህም በ1905 መነሻ ላይ በግልጽ ታየ፡፡ በወቅቱ ኖቲንግሐም ፎሬስቶች በተለያዩ ሃገራት እየተዘዋወሩ በሚያደርጉት ግጥሚያ በስድስተኛ ጨዋታቸው እንግሊዝኛ ተናጋሪ አርጀንቲናውያንን ከወከለው ምርጥ አስራ አንድ የተጫዋቾች ስብስብ ጋር ተገናኙ፡፡ ፎሬስቶች አካላዊ ጉሽሚያ ላይ ባተኮረው አጨዋወታቸው የበላይነት ለመውሰድ ያደረጉት ጥረት የበዛ ጥላቻ እንዲያተርፉ አስገደዳቸው፡፡ በብሪታኒያ ደጋፊነት የሚታወቀው የጊዜው <ሄራልድ> የተሰኘ ጋዜጣም የፎሬስትን እግርኳስ አቀራረብ ዘይቤ ለመተቸት “የደፈሩት” አካላት ላይ በከፍተኛ ሁኔታ አስገራሚ ዘለፋውን አቀረበ፡፡ ” በተለይ ብርታትን ለማሳደግ የሚረዱ እና ወጣቶች አምራችና ባተሌ በሚሆኑበት እድሜያቸው ላይ ጥንካሬን እንዲላበሱ ለማድረግ የሚያግዙ ጨዋታዎች የግድ ሰዎችን የሚያዝናኑ ወይም የሚያፍታቱ መሆን አይጠበቅባቸውም፡፡” ሲልም ጋዜጣዊ ግሳጼ ይዞ ብቅ አለ፡፡

የኖቲንግሃም ፎሬስት ቀጣይ ጉዞዎች ገጽታ በምሬትና ቁጣ የታጀበ መሆኑን ቀጠለ፡፡ “የትከሻ ጉሽሚያ የጨዋታው አካል መሆን ይኖርበታል!” የሚለው ሐሳብ መሰረታዊ ያለመግባባት መንስኤ ሆኖ የሚያስመርር ክርክር ውስጥ ተገባ፡፡ በሌላ በኩል ከሁሉም ክለቦች የበለጠ የ1912ቱ የሲውንደን ታውኖች ጉዞ አንጻራዊ ተቀባይነትን አገኘ፡፡ ይህ ሁኔታ ምናልባት ብሪታኒያውያን የሆነ “ሊማሩት የሚገባ ነገር” እንዳለ የሚያረጋግጥ እውነታን ፈጠረ፡፡ የሲውንደኑ አሰልጣኝ ሳሙኤል አለን በጥቅሉ በአማተር ቡድኖች መሀል የተሻለ እግርኳስ እንደሌለ አረጋገጠ፡፡ “የሃገሪቱ ተጫዋቾች ግላዊ ክህሎትን እንደዋነኛ ጉዳይ ይመለከታሉ፤ ‘ሁልጊዜም በተናጠል ጥሩ ነገር የማበርከትና ያንንም የማሳየት እድል አለ፡፡’ ብለውም ያስባሉ፡፡” ሲል ስጋቱን ገለጸ፡፡ በአርጀንቲና የነበሩ የወቅቱ ወግ አጥባቂዎች የጨዋታውን አቀራረብ ስልት በመበረዝ ጉዳይ አውሮፓውያኑን ተጠራጣሪዎች ነበሩ፡፡ እንግሊዛዊ የዘር ሐረግ ያለው የአሉሚኒ ቡድን የቀድሞ ተጫዋች ሆርጌ ብራውን በ1920ዎቹ መነሻ ” አዲሱ የአጨዋወት ዘይቤ የተጋጣሚ ቡድን የግብ ክልል ላይ በሚደረጉና ከመጠን ያለፈ ቁጥር ባላቸው ቅብብሎች እየተዳከመ መጥቷል፡፡ ወኔ-ቢስና ለስለስ ያለ  የጨዋታ ስልት ነው፡፡ ምናልባት የተሻለ ጥበብ የሚታይበት ሊሆን ይችላል፤ የበለጠ ብልሃት የሚስተዋልበት መሆኑንም አስመስክሯል፡፡ ሆኖም ግን ቀዳሚ የጋለ ስሜቱን አጥቷል፡፡” በማለት ተቃውሞውን ይገልጽ ነበር፡፡ ይህ የተለመደ ትችት እየተስፋፋ የሚሄድበት ሁኔታ ተፈጥሮ ቆየ፡፡ በ1953 ሃንጋሪ በዌምብሌይ ወሳኝ በሆነ መልኩ የጦፈውን ክርክር እስካረገበችበት ጊዜ ድረስ ብሪታኒያ “ቀሪው የእግርኳስ አለም ከተጋጣሚ ቡድን ግብ ፊት በ<ቀጥተኝነት/ስልነት ችግር> ሲጠቃ ኖሯል፡፡” በሚል ከንቱና አሳሳች እምነት ስታምጥ ከረመች፡፡

በ1924 ኦሎምፒክ የዩሯጓይን ቡድን ያየ ማንም ሰው ግራ ሊጋባ ይችላል፡፡ ውድድሩ ሲካሄድ አርጀንቲና በሀገሯ መሰንበትን መረጠች፡፡ ዩሯጓይ ግን ወደ ፓሪስ አቅንታ በጥንት ዘመን እግርኳስ ከታዩ ታታላቅ ታሪኮች መካካል አንዱን ልትጽፍ ቻለች፡፡ ጋሊያኖ ሁነቱን የማግነን አዝማሚያ  ቢታይበትም አገሩ የወርቅ ሜዳይ አሸናፊ በመሆኗ ያደረበት ከወገንተኝነት የመነጨ ደስታ ቅር የሚያሰኝ አይሆንም፡፡ ለድሉ ግዝፈት በዋነኝነት የሚጠቀሰው ምክን ቡድኑ በሌላ የሙያ ዘርፍ የተሰማሩ ሰርቶ አደሮችን ያሰባሰበ በመሆኑ ነው፡፡ ስጋ አሻጊ፣ እብነ በረድ ቀራጭ፣ የምግብ ግብዓቶች ነጋዴ፣ በረዶ ሻጭና ሌሎችንም የእለት ጉርሳቸውን በመሰል ስራዎች የሚያሟሉ ሰራተኞን አሰባስቦ ወደ ውድድሩ ያቀና ቡድን ነበር፡፡ ሲነሱ በርካሹ የመርከብ ጉዞ ወደ አውሮፓ አመሩ፤ ፈረንሳይ ከመድረሳቸው በፊት የምግብና መኝታ ወጪያቸውን ለመሸፈን በስፔን ዘጠኝ የወዳጅነት ጨዋታዎችን አደረጉ፤ ሁሉንም ጨዋታዎች ደግሞ አሸነፉ፡፡ ከላቲን አሜሪካ ሃገራት በአውሮፓ የእግርኳስ ግጥሚያዎችን የማድረግ ጉዞ በመጀመር ቀዳሚዋ ዩሯጓይ ነች፡፡ ይሁን እንጂ ትኩረት በመሰብሰብ ረገድ ግን እድለቢስ ስለነበረች የጥቂቶችን ይሁንታ ብቻ በማግኘት ተቸገረች፡፡ በኦሎምፒኩ መክፈቻ ጨዋታ ዩጎስላቪያን አቅም አሳጥታ 7-0 ስትረታ የተመልካቹ ቁጥር ከሁለት ሺህ ያልበለጠ ነበር፡፡

“አሰልጣኞችን ሳንይዝ፣ የአካል ብቃት ዝግጅት ሳናደርግ፣ የስፓርት ህክምና ቡድን አባላትን ሳናሟላ እና በአጠቃላይ ብቁ ባለሙያዎች ሳይኖሩን የዩሯጓያውያንን እግርኳስ ትምህርት ቤት መሰረት ጣልን፡፡ በሃገሪቱ ሜዳዎች  ከማለዳ እስከ ቀትር ከዚያም ደግሞ አመሻሽተን በደማቋ የጨረቃ ብርሐን መውጫ ሰዓት ብቻችን ሆነን ያን የቆዳ ኳስ ስናባርር እንውላለን፡፡  እግርኳስ ተጫዋች ለመሆን፣ እግርኳስ ተጫዋች ምን አይነት ባህሪ ሊኖረው እንደሚገባ ለማሳየት- በኳሱ ፍጹም የላቀ ብልሃትን ለማምጣት፣ ኳስን በቁጥጥር ስር ለማድረግ፣ ያለ ተገቢ ምክንም ላለመልቀቅ እና ሌሎችንም እየተገበርን ለሃያ አመታት ተጫወትን፡፡ ጨዋታችን ያልተገራ ባህሪ ነበረው፡፡ ልማዳዊና በተግባር የተፈተነ፣ በራሳችን ጥረት የተማርነው እንዲሁም አገርኛ ይዘትና ዘይቤ የሚስተዋልበት ነበር፡፡ እግርኳሱ በቀደመው ዘመን በሚተዳደርበት ህግና ደንብ ጥላ ውስጥ ያልወደቀ ነገርግን ብዙም ከዚያ ያላፈነገጠ ቁመና ያዘ፡፡ እንግዲህ እግርኳሳችን ይህን መሰል መልክ ነበረው፡፡ እኛም የአጨዋወት አስተምህሮአችንንና ስልታችንን በዚሁ መንገድ ቀረጽነው፡፡ በአዲሱ አለም በመላው የደቡብ አሜሪካ አህጉርም የአጨዋወት ዘይቤውና ትምህርቱ ተስፋፋ፡፡” በማለት ብሄራዊ ቡድኑን በአሰልጣኝነት ወደ ፓሪስ ይዞ የተጓዘው ኡንዲያኖ ቪየራ ለየት ባለና ከጋሊያኖ ባነሰ ውበት ያለው አገላለፅ ሁኔታውን ያስታውሰዋል፡፡

በፓሪስ ቡድኑ ወዲያው እውቅና አገኘ፡፡” ከጨዋታ ጨዋታ ተመልካቹ እነዚያን በእግርኳስ ቼዝ የሚጫወቱና እንደ ሽኮኮ የማይያዙ አብዶኛ ተጫዋቾችን ለማየት ተጋፍቶ መግባት ጀመረ፡፡ በጊዜው የእንግሊዝ ቡድን በረጅምና የከፍታ ኳስ አጨዋወት የተካነ ነበር፡፡ ሆኖም እነዚህ ከሩቁ የአሜሪካ ደቡባዊ ክፍል የመጡና የትኛውንም አይነት የአጨዋወት ስልት ውርስ ያላገኙ ልጆች የአባቶቻቸውን ዱካ መከተል አልመረጡም፡፡ በቀጥታ የቡድን አጋሮቻቸው እግር ስር የሚያርፉ፣ ፈጣን ልውውጦች የሚስተዋልባቸው፣ መደበኛ ድግግሞሽ ያላቸው፣ በከፍተኛ ፍጥነት የሚታገዙና ድሪብሊንግ የሚያካትቱ የቅርብ ርቀት ቅብብሎችን ለመፈልሰፍ ፈለጉ፡፡” ሲል ጋሊያኖ በፓሪስ ብሄራዊ ቡድኑ ስለነበረው ፈጣን ተቀባይነት ጽፏል፡፡

ቼዝ-በኳስ? ቻርለስ አልኮክ የሰጠው ዋጋ ያን ያህልም የተጋነነ ላይሆን ይችላል፡፡ ምንም እንኳ የመሀል አጥቂው ፔድሮ ፔትሮኔ በከፍተኛ ተኩረት የሚይዘው ጸጉሩ እንዳይበታተንበት ካለበት ስጋት አንጻር ኳስን በጭንቅላት የመምታት ፍላጎት ባያሳይም ግቦች የማስቆጠር ችሎታውን ግን አድንቆለታል፡፡ ዩሯጓይ በውድድሩ ብቃቷን ይዛ ስትቀጥል እዚያ የነበሩ ሰዎች ቦርቀዋል፡፡ሲውዘርላንድን በፍጻሜው 3-0 ከመርታቷ በፊት ባደረገቻቸው አራት ጨዋታዎች አስራ ሰባት ግቦችን አስቆጥራና ሁለት ተቆጥሮባት በጥሩ ብቃት ዘልቃለች፡፡ በዚህ የዪሯጓይ ስኬት የፈረንሳዊው ረጅም ልብ-ወለድ ደራሲና የስነጽሁፍ ሰው ሄንሪ ዲሞንዘርላት አስተያየት የተለየ ነበር፡፡ “ታላቅ ክስተት ነው! አሁን የትክክለኛው እግርኳስ አጨዋወት ኖረን፡፡ እስካሁን ድረስ የምናውቀውና የተጫወትነው ለንጽጽር ቢቀርብ ትምህርት ቤት ውስጥ ተማሪዎች ትርፍ ጊዜያቸውን ለማሳለፍ ከሚያዘወትሩት ጨዋታ የተሻለ ሆኖ አናገኘውም፡፡” የሚል ታላቅ አድናቆት ቸረ፡፡

የተሳካ የተጫዋችነት ዘመኑ መገባደጃ ላይ በ<ለኪፕ> ጋዜጣ አርታኢነት ያገለግል የነበረው ጋብሬል ሃኖት ደግሞ ” ዩሯጓይ በልዩ ተፈጥሮአዊ ክህሎት የሚገኝ ግሩም ኳስን የመቀበል፣ የመቆጣጠርና የመጠቀም ቴክኒካዊ ችሎታ አሳይታለች፡፡ ተጫዋቾቿ ውበት ያለው እግርኳስን ፈጥረዋል፡፡ ማራኪ- የዛኑ ያህልም በአይነቱ የተለየ፣ ፈጣን፣ ጥንካሬን የተላበሰና ስኬታማ ዘይቤን አግኝተዋል፡፡” በማለት ምክንያታዊና በመጠኑ ከስሜታዊነት የራቀ አስተያየቱን አስፍሯል፡፡ ያም ቢሆን ” የብሪታንያ እግርኳስ የበላይነቱን እንደያዘ ነው፡፡” የሚለውን ክርክር በመቃረንም ” ሐሳቡ በአረቢያ ምድር ብቻ የሚገኙ ባለግርማ ሞገስ ብልህ የግልቢያ ፈረሶችን ከልግመኞቹ የእርሻ ስራ ፈረሶች ጋር እንደማነጻጸር ነው፡፡” በማለት የእንግሊዝ አጨዋወት ከዩሯጓያኖቹ ጋር ፍጹም ሊነጻጸር እንደማይገባ ገለፀ፡፡

ከውድድሩ መልስ ዩሯጓይ ወደ አገሯ ተመልሳ ብዙም ሳትቆይ ከአርጀንቲና ጋር ፈታኝ ጨዋታ አደረገች፡፡ በደጋፊዎች ሁከት ተቋርጦ በነበረው የብዌኖስ አይረሱ የእነዚህ ባላንጦች የሁለተኛ ዙር ጨዋታ አርጀንቲና በሜዳዋ ያገኘችው የ2-1 ድል በጃትና የተከታታዩ የሜዳና ከሜዳ ውጪ ጨዋታዎች የ3-2 ድምር ውጤት ባለድል እንድትሆን አስቻላት፡፡ ይህም ቡድኑ ቀደም ሲል ወደ ኦሎምፒኩ ተጉዞ ቢሆን ኖሮ የውድድሩ አሸናፊ ይሆን እንደነበር ማሳያ ስለመሆኑ ብዙዎች በእጅጉ እንዲወተውቱ ዳረጋቸው፡፡ ሆኖም ጉዳዩ በ”ምናልባትነት” ከመታየት ያለፈ ሊሆን አልቻለም፡፡ ይሁን እንጂ የርዕሰ መዲናዋ ክለብ ቦካ ጁኒየርስ በ1925 በአውሮፓ ባደረጋቸው ጉዞዎች ካካሄዳቸው አስራ ዘጠኝ ጨዋታዎች ሶስቱን ብቻ በመረታት ትልቅ ግርምትን ፈጥሮ አለፈ፡፡

ይቀጥላል…


ስለ ደራሲው 

ጆናታን ዊልሰን ዝነኛ እንግሊዛዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ሲሆን በተለያዩ ጋዜጦች፣ መጽሄቶች እና ድረገጾች ላይ ታክቲካዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው የእግርኳስ ትንታኔዎችን የሚያቀርብ ጉምቱ ጸኃፊ ነው፡፡  ባለፉት አስራ ሁለት ዓመታትም የሚከተሉትን ዘጠኝ መጻህፍት ለህትመት አብቅቷል፡፡

-Behind The Curtain: Travels in Eastern European Football (2006)

-Sunderland: A Club Transformed (2007)

-Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics (2008)

-The Anatomy of England (2010)

-Brian Clough: Nobody Ever Says Thank You: The Biography (2011)

-The Outsider: A History of the Goalkeeper (2012)

-The Anatomy of Liverpool (2013)

-Angels With Dirty Faces: The Footballing History of Argentina (2016)

-The Barcelona Legacy: Guardiola, Mourinho and the Fight For Football’s Soul (2018)


 

ቀደምት ምዕራፎች
መቅድም LINK
ምዕራፍ 1 – ክፍል አንድ LINK
ምዕራፍ 1 – ክፍል ሁለት LINK
ምዕራፍ 1 – ክፍል ሶስት LINK
ምዕራፍ 1 – ክፍል አራት LINK
ምዕራፍ 2 – ክፍል አንድ LINK
ምዕራፍ 2 – ክፍል ሁለት LINK