የፌዴሬሽኑ የጥናት ኮሚቴ ስራውን አገባደደ

ለወራት ሲካሄድ የቆየው የፌዴሬሽኑን የአሰራር እና አደረጃጀት ችግሮችን እና የመፍትሄ ቅጣጫዎችን ሲያጠና የቆየው ኮሚቴ የጥናት ስራውን በማገባደድ የመጨረሻ የሰነድ ርክክቡን ነገ ያደርጋል።

የፌዴሬሽኑን የአሰራር እና አደረጃጀት ችግሮችን የሚፈትሽ እና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በጥናት በተደገፈ ሙያዊ ሀሳብ እንዲያመጡ በማሰብ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አመራሮች በእግርኳሱ የረጅም ጊዜ ልምድ እና ተመኩሮ ያላቸውን ግለሰቦችን በማሰባሰብ በባሳለፍነው ዓመት ሰኔ ወር ላይ አንድ ኮሚቴ ማዋቀሩ ይታወቃል።

ኮሚቴው ያለፉትን ወራት በተለያዩ መንገዶች የእግርኳሱ አደረጃጀት እና አወቃቀር ችግር ምን እንደሚመስል እና መፍትሄው ምን መሆን እንደሚገባ በራሱ መንገድ እና የተለያዩ ባለ ድርሻ አካላት የተሳተፉበት የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት በርካታ ጠቃሚ ግባቶችን በመውሰድ ሲሰራ ቆይቷል። ከፍተኛ ገንዘብ ፣ እውቀት እና ጊዜ ወጥቶበት ለወራት ሲካሄድ የቆየው ይህ ጥናት በመጨረሻም የደረሰበትን የመፍትሄ ሀሳብ እና ድምዳሜ አጠናቆ የጨረሰ ሲሆን ነገ ከ10:00 ጀምሮ በካፒታል ሆቴል የፌዴሬሽኑ አመራሮች እና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የሰነድ እርክብ የሚያደርግ ይሆናል።

ለዘመናት የሚነሱትን የፌዴሬሽኑን የተዝረከረከ ልማዳዊ አሰራርን ስር ነቀል በሆነ መልኩ መፍትሄ ያመጣል ተብሎ በታሰበው በዚህ ጥናት ፌዴሬሽኑ ሰነዱን ተረክቦ ወደ ትግበራ መግባት ትልቁ የቤት ስራው ይሆናል።