ፌዴሬሽኑ በአክሊሉ አያናው እና ኢትዮጵያ ቡና ውዝግብ ዙርያ ውሳኔ ሰጠ

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዲሲፕሊን ኮሚቴ በአክሊሉ አያናው እና በኢትዮጵያ ቡና መካከል የተፈጠረውን ውዝግብ በተመለከተ ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ባደረገው ስብሰባ ውሳኔ ሰጥቷል።

በአምና የውድድር ዘመን ነበር ተከላካዩ አክሊሉ አያናው ከደደቢት ወደ ኢትዮጵያ ቡናን የተቀላቀለው። በጉዳት ምክንያት በተወሰኑ ጨዋታዎች ካልሆነ በቀር አብዛኛውን የውድድር ጊዜ ያሳለፈው በጨዋታ አልነበረም። ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ በሚፈለገው ደረጃ ከተጫዋቹ የሚፈለገውን አገልግሎት ባለማግኘቱ ከቡድኑ ቀንሶታል። ይህ ውሳኔ ያላስደሰተው አክሊሉ ቅሬታውን በመያዝ ወደ ፌዴሬሽኑ ዲሲፕሊን ኮሚቴ ደብዳቤ ያስገባ ሲሆን ጉዳዮዩን ሲመለከተው የቆየው ኮሚቴም በመጨረሻም ተጫዋቹ ወደ ቡድኑ እንዲመለስ ይህም ካልሆነ የውል ዘመኑ እስኪፈፀም ሙሉ ደሞዙን ከፍሎ እንዲሸኘው እና ለህክምና ያወጣውን ወጪ ተጫዋቹ በሚያቀርበው ሰነድ አማካኝነት ኢትዮጵያ ቡና እንዲሸፍን ወስኗል።

ኢትዮጵያ ቡና ይህን ተከትሎ ውሳኔውን ይቀበል አልያም ይግባኝ ይጠይቅ ከክለቡ የተገኘ መረጃ ያላገኘን ቢሆንም ምላሽ ካለ የምናስተናግድ መሆኑን እንገልፃለን።

አክሊሉ አያናው ወደ ኢትዮጵያ ቡና ያደረገው ዝውውር ተገቢ አይደለም በማለት ፋሲል ከነማ በወቅቱ ክስ መስርቶ እንደነበር ይታወሳል።