ለአሰልጣኞች እና ዳኞች ሲሰጥ የቆየው ስልጠና ዛሬ ተጠናቀቀ

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አትሌት ኢን አክሽን ከተባለ ተቋም ጋር በመተባበር ከዩናይትድ ስቴትስ በመጡ ባለሙያዎች አማካኝነት በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ለ52 የአንደኛ ሊግ ክለቦች አሰልጣኞች እና ለ32 ጀማሪ እና 1ኛ ደረጃ የእግር ኳስ ዳኞች የሙያ ማሻሻያ ስልጠና ሲሰጥ ቆይቶ በዛሬው እለት ተጠናቋል። 

የፌዴሬሽኑ የቴክኒክ ዳይሬክተር አቶ መኮንን ኩሩ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት ተቋሙ አምናም በተመሳሳይ  ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ተመሳሳይ ስልጠና እንደሰጠ ገልፀው የዘንድሮውም በተሳካ ሁኔታ መከናወኑን ተናግረዋል። 

” የዘንድሮን ለየት የሚያደርገው የስልጠናውን እድል የሰጠነው ለ62 አንደኛ ሊግ ክለቦች አሰልጣኞች የነበረ ሲሆን 52 አሰልጣኞች ተሳትፈውበታል። ከዚህ በተጨማሪ ለ32 ለጀማሪ፣ 1ኛ ደረጃ እና 2ኛ ደረጃ ወጣት የእግር ኳስ ዳኞች የሙያ ማሻሻያ ስልጠና ተስጥቷል። የዳኞቹ በአዲስ አበባ እና ዙርያዋ ያሉትን ብቻ ያካተተ ስለሆነ በቀጣይ ለሁሉም የምናዳርስ ይሆናል። 

“ስልጠናው በአጠቃላይ የተሳካ ነበር ማለት ይቻላል። አሜሪካኖቹ በራሳቸው መንገድ የክፍል ውስጥ እና የሜዳ ላይ ስልጠና ሰጥተዋል። በእኛ በኩል ደግሞ በስፖርት ፊዚዮሎጂ፣ አናቶሚ እና በፊትነስ እንዲሁም የእግርኳስ ዶፒንግ ላይ ባሉን ኢንስትራክተሮች መስጠት ችለናል። በቀጣይም ከሌሎች ሀገራት ጋር በመተባበር የእግርኳሱን ደረጃ ከፍ የሚያደርጉ ስልጠናዎች ይከናወናሉ።”