ሀዋሳ ከተማዎች በመመለስ ላይ ናቸው

ትናንት በደጋፊዎች ግጭት ምክንያት ሳይደረግ የቀረው ጨዋታ ዛሬ እንደሚከናወን ቢገለፅም የሀዋሳ ቡድን አባላት በአሁኑ ሰዓት ጉዞ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

የትናንቱ የስድስተኛ ሳምንት መርሀ ግብር በቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሀዋሳ ከተማ መካከል ከመደረጉ አስቀድሞ በደጋፊዎች መካከል የተነሳው ግጭት ጨዋታው እንዳይካሄድ ምክንያት መሆኑ ይታወሳል። በመሆኑም ዛሬ 9፡00 ላይ ጨዋታው በአዲስ አበባ ስታድየም በዝግ ይካሄዳል ተብሎ ቢጠበቅም ሀዋሳ ከተማዎች ዛሬ ማለዳ ወደ መቀመጫ ከተማቸው ሀዋሳ ጉዞ መጀመራቸው ታውቋል።

ሶከር ኢትዮጵያ ጉዳዩን አስመልክቶ ከክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ጠሀ አህመድ ጋር ባደረገችው ቆይታም ተከታዩን ምላሽ አግኝታለች። ” ጨዋታውን ማካሄድ አንችልም ፤ በኛ በኩል ከ20 በላይ ደጋፈዎቻችን ተጎድተውብናል። በአጋጣሚም ቢሆን ወደ ስድስት የሚጠጉ ተጫዋቾቻችን ጉዳት ገጥሟቸዋል። በዚህ ሁኔታ ላይ ደግሞ ተጫወቱ ማለት እጅጉን ይከብዳል። እኛ አስቀድመን እንግዳ ቡድን ስለሆንን የቀኙን ጥላ ፎቅ ስጡን ስንል የሰጡን ያልሆነ ቦታ ነው። ያ ቢሆን ይህ ሁሉ አይነሳም ነበር። በዚህ ነገር ደስተኛም አልነበርንም። ሁኔታውም ቀስ በቀስ ወደ አስፈሪ ድርጊት ሄዷል። ስለዚህ በዚህ መንፈስ ውስጥ ሆነን ለመጫወት የሚያስችል ሞራል ላይ አይደለንም። ”

በሌላ በኩል ባገኘነው መረጃ የሊግ ኮሚቴው በትናንቱ ውሳኔ መሰረት ጨዋታው ዛሬ እንደሚካሄድ በመጠበቅ ላይ ሳለ ሀዋሳዎች መሄድ በመጀመራቸው ሀሳባቸውን ቀይረው ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ በስልክ ግንኙነት ለማድረግ ጥረት ላይ ቢሆንም እስካሁን እንዳልተሳካለትና ሀዋሳዎችም ጉዟቸውን እንደቀጠሉ ታውቋል።

በዚህ ጉዳይ ላይ የሚኖር ተጨማሪ መረጃ ካለ ይዘን የምንመለስ ይሆናል