ሴቶች 1ኛ ዲቪዝዮን | ቅዱስ ጊዮርጊስ መጀመርያ ድል ሲያመዘግብ ሀዋሳ ከአአ ከተማ ነጥብ ተጋርቷል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ 1ኛ ዲቪዚዮን አራተኛ ሳምንት ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች ተደርገው ቅዱስ ጊዮርጊስ የዓመቱን የመጀመርያ ድል ሲያስመዘግብ ቅዱስ ሀዋሳ ከተማ በሜዳው ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር ነጥብ ተጋርቷል።
አሰላ ላይ ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ ቅዱስ ጊዮርጊስን ጋብዞ 1-0 በሆነ ጠባብ ውጤት  ሽንፈት ገጥሞታል። የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ ጨዋታ በመኖሩ ምክንያት ለ20 ደቂቃዎች ዘግይቶ በተጀመረው ጨዋታ እንስቶቹ ፈረሰኞች ገና ከጅማሮው ነበር አሸናፊ የሆኑበትን ግብ ያገኙት። አይናለም ዓለማየሁ ከግራ በኩል የሰጠቻትን ኳስ ተጠቅማ ፋና ዘነበ በ2ኛው ደቂቃ አስቆጥራ የጊዮርጊስን አሸናፊነት አረጋግጣለች። 

ሀዋሳ ላይ ሀዋሳ ከተማ አዲስ አበባ ከተማን አስተናግዶ ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል። በእለቱ የነበረው ከባድ ፀሐይ በተጫዋቾች ላይ የፈጠረባቸው ተፅዕኖ በሙሉ የጨዋታው ክፍለ ጊዜ የታየ ሲሆን የሚቆራረጡ ኳሶች የበዙበት ነበር። በመጀመሪያወቹ 20 ደቂቃዎች አዲስ አበባ ከተማዎች የእንቅስቃሴ የበላይነት የነበራቸው ሲሆን በ12ኛው ደቂቃ ፍቅርተ ብርሀኑ ያገኘችውን መልካም አጋጣሚ ሳትጠቀምበት የቀረችበት አስቆጪ ሙከራ ተጠቃሽ ነበረች። በቀሪው የመጀመርያ አጋማሽ ደቂቃዎች የምርቃት ፈለቀን በቅጣት ያለመሰለፍ ተከትሎ በፊት መስመር ላይ ተሰልፋ የነበረችው ነፃነት መና በርካታ የግብ አጋጣሚዎችን ብታገኝም በቀላሉ ስታባክናቸው በአዲስ አበባ ከተማዎች በኩል ታዳጊዋ አጥቂ ፎዚያ መሐመድ በግሏ ያደረገችው እንቅስቃሴ መልካም ነበር። 

በሁለተኛው አጋማሽ የተጫዋች ለውጥ ያደረጉት ሀዋሳ ከተማዎች የተሻለ መንቀሳቀስ የቻሉበት እንዲሁም አዲስ አበባ ከተማዎች በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ጥረት ያደረጉበት ነበር። ከ75ተኛው ደቂቃ በኃላ በግራ መስመር በኩል ተቀይራ የገባችሁ ርብቃ ጣሰው በርካታ አጋጣሚዎችን ብትፈጥርም ሳሳሁልሽ አምክናባታለች። 78ኛው ደቂቃ ላይ ስንታየው ማቲዎስ ከግብ ጠባቂዋ ጋር ተገናኝታ የተመለሰባት እና ከሁለት ደቂቃዎች በኃላ ነፃነት መና ከርብቃ  ያገኘችውን ኳስ ሞክራ ወደ ውጪ የወጣባት ሙከራዎች በሀካሳ በኩል የሚጠቀሱ ነበሩ። በ81ኛው ደቂቃ ኤደን ሽፈራው ከግራ መስመር ያሻገረችውን ኳስ ፎዚያ መሐመድ በቄንጠኛ መልኩ ወደ ግብ መትታ ወደ ውጭ በቀላሉ የወጣባት ደግሞ በእንግዳው ቡድን በኩል የሚጠቀስ ነው።