አሰልጣኝ ዘማርያም ወደ መደበኛ ስራቸው ተመለሱ

ከግብፁ የቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታ መልስ ያለፉትን ሁለት ቀናት የአምስት ወር ደሞዝ አልተከፈለኝም በማለት ልምምድ ሳያሰሩ የቆዩት የጅማ አባ ጅፋሩ አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ ወደ ኃላፊነታቸው ተመልሰዋል።

የጅማ አባ ጅፋሩ አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ የአምስት ወር ደሞዝ አልተከፈለኝም በሚል መነሻ ያለፉትን ሁለት ቀናት ቡድኑን ልምምድ ሳያሰሩ መቅረታቸውን በትናንቱ ዘገባችን መግለፃችን ይታወቃል። በአሰልጣኙ እና በክለቡ መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት የተረዱት የክለቡ የበላይ ኃላፊዎች ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት እና ከአሰልጣኙ ጋር ባደረጉት ውይይት ያልተከፈለ ደሞዛቸው በፍጥነት እንደሚፈፀምላቸው ከስምምነት ላይ በመድረሳቸው አሰልጣኙ ዛሬ 10:00 ሲ ኤም ሲ በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሜዳ በመገኘት ረዘም ላለ ደቂቃ ከተጫዋቾቻቸው ጋር ውይይት ካደረጉ በኃላ መደበኛ ስራቸውን ሲያሰሩ መመልከት ችለናል።

አሰልጣኝ ዘማርያም ስለጉዳዩ ሲናገሩ ” የክለቡን የበላይ ኃላፊዎች ማመስገን እፈልጋለው። ጥያቄው ትክክለኛ እንደሆነ በማመን ተገቢውን አፋጣኝ ምላሽ እንደሚሰጡኝ ቃል ስለገቡልኝ ወደ ስራዬ ተመልሻለው አሁን ሙሉ የቡድኑ አባላት እና የደጋፊዎቻችን ትኩረት የሚሆነው የፊታችን እሁዱ ላለብን ወሳኝ የመልስ ጨዋታ ዝግጅት ማድረግ ላይ ይሆናል” ብለዋል።

ከግብ ጠባቂው ዘሪሁን ታደለ በስተቀር የተቀሩት የቡድኑ አባላት በዛሬው ልምምድ ላይ የተገኙ ሲሆን በጥሩ መንፈስ ልምምዶቻቸውን ሰርተው አጠናቀዋል።