የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ቡሩንዲን 3-0 በመርታት በድምር ውጤት 3-2 አሸንፎ በሩዋንዳ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው ቻን ውድድር አልፏል፡፡ ቡድኑ በቡጁምቡራ 2-0 የተሸነፈበትን ውጤት ለመቀልበስም በጥሩ እንቅስቃሴ የታጀበ ውጤት አስመዝግበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የመጀመርያ የግብ እድል የተፈጠረው በ8ኛው ደቂቃ ነበር፡፡ አስቻለው ግርማ ከቀኝ መስመር ከራምኬል ሎክ የተሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ወደ ግብ የሞከረውን ኳስ የቡሩንዲ ተከላካዮች አውጥተውታል፡፡ በ28ኛው ደቂቃ ደግሞ ኤልያስ ማሞ ከፍፁም ቅጣት ምት ግራ ጠርዝ ወደ ግብ የሞከረውን ኳስ ግብ ጠባቂው ማክ አርተር አድኖታል፡፡
በ36ኛው ደቂቃ ጋቶች በረጅሙ ወደ ግብ የመታውን ኳስ የቡሩንዲ ተካከዮች በአግባቡ ባለማራቃቸው ራምኬል ቢያገኘውም ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡
በ37ኛው ደቂቃ ስዩም ተስፋዬ በግራ መስመር በተገኘ የቅጣት ምት ከኤልያስ ማሞ የተሸገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ኢትዮጵያን ቀዳሚ ያደረገች ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡ የድምር ውጤቱም ቡሩንዲ 2-1 ኢትዮጵያ ሆኗል፡፡ የቀኝ መስመር ተከላካዩ ስዩም ባለፉት 5 የአለም እና የአፍሪካ ፣ የቻን እና የወዳጅነት ጨዋታዎች 4ኛ ግቡን ከመረብ አሳርፏል፡፡
ቡሩንዲዎች በመጀመርያው አጋማሽ ይህ ነው ተብሎ የሚጠቀስ የግብ እድል መፍጠር ያልቻሉ ሲሆን ናሂማና ሻሲኪ ከግራ መስመር የተገኘውን ቅጣት ምት በቀጥታ ወደ ግብ ከሞከረው ውጪም አስደንጋጭ የሚባል ሙከራ አላደረጉም፡፡
በ2ኛው አጋማሽ የመጀመርያዎቹ 5 ደቂዎች ቡሩንዲዎች ተጭነው ለመጫወት ሲሞክሩ በ47ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው ሙስጣፋ ፍራንሲስ የመታውን ቅጣት ምት ታሪክ ጌትነት መልሶታል፡፡
በ52ኛው ደቂቃ በመሃመድ ናስር ተቀይሮ የገባው ምንይሉ ወንድሙ ከቀኝ መስመር የተሸገረውን ኳስ በግንባሩ በመግጨት ወደ ግብ የሞከረው ኳስ ወደ ውጪ ወጥቷል፡፡
በ73ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታው ድንቅ እንቅስቃሴ ሲያሳይ የዋለው ኤልያስ ማሞ ያሻገረውን የቅጣት ምት ኳስ ጋቶች ፓኖም በግንባሩ በመግጨት ኢትዮጵያን 2-0 መሪ ሲያደርግ በድምር ውጤትም አቻ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡
ከ2ኛው ግብ በኋላ ብዙ ሳይቆይ በ78ኛው ደቂቃ ኤልያስ ማሞ በግሩም ሁኔታ ለአስቻለው ግርማ ያሳለፈለትን ኳስ አስቻለው ግብ ጠባቂውን ለማለፍ ሲሞክር በተሰራበት ጥፋት ኢትዮጵያ የፍፁም ቅጣት ምት አግኝታለች፡፡ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ጋቶች በቀላሉ ወደ ግብነት ቀይሮ የኢትዮጵያን መሪነት ወደ አስተማማኝነት ቀይሮታል፡፡
በመጨረሻዎቹ ደቂዎች ወደ ቻን ውድድር ለማለፍ 1 ግብ ብቻ ያስፈለጋቸው ቡሩንዲዎች መጠነኛ ጫና ለመፍጠር ቢሞክሩም የተሳካ የግብ እድል ሳይፈጥሩ ጨዋታው በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
ኢትዮጵያ ለ2ኛ ተከታታይ ጊዜ የሀገር ውስጥ ሊግ ብቻ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ለሚካፈሉበት ውድድር ማለፍ ችላለች፡፡ የቻን ውድድር በጃንዋሪ 2016 በሩዋንዳ አስተናጋጅነት ይካሄዳል፡፡