ከ20 አመት ሴቶች ብሄራዊ ቡድን በሜዳቸው አቻ ተለያዩ

በፓፓ ኒው ጊኒ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የ2016 የአለም ከ20 አመት በታች ሴቶች ዋንጫ ለማለፍ ከመጨረሻው ምእራፍ ላይ የደረሰው የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ከጋና አቻው ጋር 2-2 ተለያይቷል፡፡

ጋናዎች በ4ኛው ደቂቃ ከማእዘን የተሸገረችን ኳስ ተጠቅመው ቀዳሚ መሆን ችለዋል፡፡ ከግቧ በኋላ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በተደጋጋሚ ወደ ግብ የደረሰ ሲሆን በ6ኛው ደቂቃ አዲስ ንጉሴ ፣ በ7ኛው ደቂቃ ደግሞ በሎዛ አበራ አማካኝነት የግብ ሙከራ ማድረግ ችለዋል፡፡

በ15ኛው ደቂቃ አምበሏ ሎዛ አበራ ከፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውጪ በግሩም ሁኔታ ከመረብ በማሳረፍ ኢትየጵያን አቻ ማድረግ ስትችል ከ5 ደቂቃ በኋላ ደግሞ ለራሷ እና ለቡድኗ 2ኛ ግብ በማስቆጠር ኢትዮጵያ 2-1 መሪ እንድትሆን አስችላለች፡፡ ሎዛ በኢትዮጵያ የአለም ዋንጫ ማጣርያ ጉዞ የተቆጠሩትን 6 ግቦች በሙሉ በስሟ ማስመዝገብ ችላለች፡፡

በ36ኛው ደቂቃ ሎዛ አበራ ከተከላካዮች አምልጣ በመውጣት ለኢትዮጵያ 3ኛ ሊሆን የሚችል የግብ እድል ብትፈጥርም በግብ ጠባቂዋ ቪክቶርያ አንትዊ ተጨርፎ ወደ ውጭ ወጥቷል፡፡

በ43ኛው ደቂቃ አዲስ ንጉሴ ግብ መሆን የሚችል እድል ብታገኝም ሳትጠቀምበት ቀርታለች፡፡ የመጀመርያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜም በኢትዮጵያ 2-1 መሪነት ተጠናቋል፡፡

ከእረፍት መልስ ኢትዮጵያ ከመጀመርያው አጋማሽ የደከመ እንቅስቃሴ ያሳየች ሲሆን በተቃራኒው ጋናዎች የተሻለ ተንቀሳቅሰዋል፡፡ የኢትዮጵያ የአማካይ ክፍል መሳሳትን ተከትሎ ጋናዎች ኳስን ቶሎ ቶሎ ለማግኘትና በረጃጅም ኳሶች የግብ እድል ለመፍጠር ሞክረዋል፡፡

በ80ኛው ደቂቃ ከመስመር የተሻገረውን ኳስ ተቀይራ የገባችው ራፊያ አል ሃሰን ወደ ግብነት ቀይራ ጋናን አቻ ማድረግ ችላለች፡፡ ጨዋታውም 2-2 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የጋና ተጫዋቾች የአየር ሁኔታውን መቋቋም የተሳናቸው ሲሆን ሁለት ተጫዋቾችም በአምቡላንስ ታግዘው ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል፡፡

IMG_7951

ከጨዋታው በኋላ አስተያየታቸውን የሰጡት የኢትዮጵያ አሰልጣኝ አስራት አባተ ጨዋታው እንዳልተጠናቀቀና በመልሱ ጨዋታ ግቦችን አስቆጥሮ ማጣርያውን ለማለፍ ጥረት እንደሚያደርጉና ያሉባቸውን ክፍተቶች ባላቸው ጊዜ አርመው ለመልሱ ጨዋታ እንደሚዘጋጁ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ እና የጋና ከ20 አመት በታች ሴቶች የመልስ ጨዋታ ከ2 ሳምንት በኋላ በጋና ይካሄዳል፡፡ በደርሶ መልስ የሚያሸንፈው ቡድንም ፓፓ ኒው ጊኒ ለምታዘጋጀው የአለም ከ20 አመት በታች ሴቶች ዋንጫ አፍሪካን ከሚወክሉ 2 ቡድኖች አንዱ ይሆናል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *