የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ታሪክ ለመስራት 120 ደቂዎች ብቻ ቀርተውታል፡፡ ካሜሩንን እና ቡርኪናፋሶን በማሸነፍ ለመጨረሻው ማጣያ ያለፉት ወጣቶቹ ሉሲዎች ነገ ሌላዋ የምእራብ አፍሪካ ሃገር ጋናን አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ይገጥማሉ፡፡
ብሄራዊ ቡድናችን ከነገው ወሳኝ ጨዋታ በፊት ዛሬ ጠዋት ከ1፡00 – 2፡00 ድረስ የመጨረሻ ልምምዳቸውን በአዲስ አበባ ስታየም ያከናወነ ሲሆን ቡድኑ ለጨዋታው ዝግጅት እንዳደረገ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየታቸውን የሰጡት አሰልጣኝ አስራት አባተ ገልፀዋል፡፡
‹‹ ለጨዋታው ያደረግነው ዝግጅት ጥሩ ነው፡፡ የነገው ጨዋታ በ13 ቀን ውስጥ 3ኛ ጨዋታችን እንደመሆኑ መጠን ክብደት አለው፡፡ ተጫዋቾቼ የዚህ አይነት ልምድ ስለሌላቸው አስቸጋሪ ሊሆንብን ይችላል፡፡ በተጨማሪም ትዕግስት ያደታ የአባቷ ህልፈት እንዳለ ሆኖ ልምምዷን ረቡዕ ጀምራ የነበረ ቢሆንም በ2 ቢጫ ጨዋታውን የማታደርግ በመሆኑ ቡድናችን ላይ ክፍተት ይፈጥራል፡፡ ያም ሆኖ የቡድኑ ስነ ልቡና ጥሩ በመሆኑ በቀላሉ አንላቀቅም፡፡ ያላቸው የቡድን መንፈስ ጥሩ ነው፡፡ ተጫዋቾቼ ጨዋታውን እዚሁ ጨርሰው ለመሄድም ተዘጋጅተዋል፡፡ ›› ብለዋል፡፡
አሰልጣኝ አስራት የተጋጣሚያቸው ጋናን ብቃት አንስተው ቡድናቸው ጨዋታውን እዚሁ ለመጨረስ ስላደረገው ዝግጅት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
‹‹ ጋና ከሌሎች ቡድኖች የሚለየው በቀላሉ የማይጠቃ እና በቀላሉ ለማጥቃት የማይቸገር ነው፡፡ ይህም የነሱ ጠንካራ ጎን ነው፡፡ ቡድኑ ከ15 እና 17 አመት በታች የአለም ዋንጫ ላይ ተካፍሎ የሚያውቅ በመሆኑ የውድድር ልምድ አለው፡፡ ይህንን ቡድን በሜዳም ሆነ ከሜዳ ውጪ ስንገጥም ከፍተኛ ጥንቀቃቄ ማድረግ አለብን፡፡ በተለይም በሜዳችን አንድ ግብ ማስተናገድ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ስለዚህ በማጥቃቱም ሆነ በመከላከሉ ሚዛናዊ ቡድን ይዘን እንገባለን፡፡ ተጫዋቾችም ለዚህ ተዘጋጅተዋል፡፡ እዚህ የምናስበውን ውጤት ባናሳካ እንኳን ተጫዋቾቻችን ከሜዳ ውጪ የማሸነፍ የአእምሮ ጥንካሬ በመያዛቸው እስከ መጨረሻው እንታገላለን፡፡ ›› ሲሉ በተጫዋቾቻቸው እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
ነገ ጋናን በሚገጥመው ቡድን ውስጥ ምንም አይነት የተጫዋቾች ጉዳት የሌለ ሲሆን በአማካይ ስፍራ የምትጫወተው ትዕግስት ያደታ በሁለት ቢጫ ምክንያት አትሰለፍም፡፡
የጋና ብሄራዊ ቡድን ትላንት ማታ አዲስ አበባ የገባ ሲሆን ቦሌ አካባቢ በሚገኘው ጎልደን ቱሊፕ ተቀምጧል፡፡ በዚህም ሰአት ልምምዱን በአዲስ አበባ ስታየም በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡
ጨዋታው ነገ 10፡00 በአዲስ አበባ ስታድየም የሚደረግ ሲሆን ዩጋንዳዊያን ዳኞች እና ኬንያዊ ኮሚሽነር ጨዋታውን ይመሩታል፡፡