የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፣ ኮካኮላ እና የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ በመተባበር እድሜያቸው ከ15 አመት በታች የሆኑ ታዳጊዎችን በመመልመል በአካዳሚው ስልጠና እንደሚሰጡ ትላንት በአካዳሚው አዳራሽ በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ተገልጧል፡፡
በእለቱ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽንን በመወከል ፕሬዝዳንቱ አቶ ጁነይዲ ባሻ ፣ የኢትዮጵያ ወጣቶች አካዳሚ ዳይሬክተር ሲራክ ኃ/ማርያም (ዶ/ር) እንዲሁም የኮካኮላ ተወካይ ኪንግ ኦሪ ማቻርያ ተገኝተዋል፡፡
በመግለጫው ላይ እንደተብራራው ምርጫው ከሁሉም ክልል እና ሁለቱ የከተማ መስተዳድሮች የተደረገ ሲሆን ምርጫው የተደረገውም ከአካዳሚው እና ፌዴሬሽኑ በተውጣጡ ባለሙያዎች መሆኑ ተገልጧል፡፡ በመጀመርያው ዙር ከተመለመሉት 88 ታዳጊዎች መካከል 62 ታዳጊዎች ወደ አካዳሚው ገብተዋል፡፡ ከ62 ታዳጊዎች 39 ወንዶች እና 23 ሴቶች ናቸውም ተብሏል፡፡
ታዳጊዎቹ በአካዳሚው የሚኖራቸውን ቆይታ ወጪ የሚሸፍነው ኮካኮላ ሲሆን ለሁለት አመት አስፈላጊውን ወጪ ይሸፍናል፡፡ የፌዴሬሽኑፕሬዝዳንት አቶ ጁነይዲ ባደረጉት ንግግር 2 አመት በቂ ባይሆንም ፌዴሬሽኑ ጠንክሮ በመስራት ከኮካኮላ ጋር ያለውን አጋርነት ለተጨማሪ አመታት እንዲዘልቅ የማድረግ አላማ እንዳለው ተናግረዋል፡፡
በአዳራሹ የተገኙት የአካዳሚው ሰልጣኞች ስለ ወደፊት ራእያቸውና የትኛውን ተጫዋች መሆን እንደሚፈልጉ መድረክ ላይ በመውጣት ተናግረዋል፡፡
የኮካኮላ ኩባንያ ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር በ2007 የውድድር አመት ከ15 አመት በታች ውድድር መካሄዱ የሚታወስ ነው፡፡