ኢትዮጵያ ቡና ጠቅላላ ጉባዔውን ዛሬ አካሄደ

የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ 8ኛ መደበኛ እና ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባዔውን ተሳታፊ አባላት እና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት ዛሬ በኔክሴስ ኢንተርናሽናል ሆቴል አከናውኗል።

የጠቅላላ ጉባዔው ሰብሳቢ አቶ ድንቁ ስለሺ፣ የክለቡ የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ እና ስራ አስኪያጅ አቶ ስንታየሁ በቀለ በመሩት በዚህ ጠቅላላው ጉባዔ ድምፅ ከሚሰጡ አርባ አንድ የጉባዔው አባላት ሃያ ሁለቱ ሲገኙ በተጋባዥ እንግድነት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽንን በመወከል ም/ፕሬዝዳንቱ ኮሎኔል ዐወል አብዱራሂም፣ የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት ኃይለኢየሱስ ፍስሀ (ኢንጂነር) እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።


ምላዕተ ጉባዔው መሟላቱ ከተረጋገጠ በኋላ በተያዘው አጀንዳ መሰረት የክለቡ የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ የ2010 የአፈፃፀም ሪፖርት በማቅረብ በጀመረው ጉባኤ የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ የተቋቋመበትን ዓላማ ለማሳካት ጠንክሮ እየሰራ ሲገኝ በዚህ የሪፖርት መነሻነት ጠንካራ እና ደካማ ጎኖቹን በመገምገም የተሻለ እቅድ ለመንደፍ ሪፖርቱ እንደሚከተለው አቀርበውታል።

የሰው ኃይል አስተደደርን በተመለከተ የተሰሩ የሰራተኛ ቅጥር እና የተወሰዱ የዲሲፕሊን እርምጃዎች፣ በክለቡ ስር የሚገኙ ቡድኖች የቅድመ ዝግጅት ጊዜ እና የተመዘገቡ ውጤቶች ፣ የክለቡ የቴሌቪዥን እና የራዲዮ ፕሮግራሞች ትምህርት ሰጪ እና አዝናኝ አስተማሪ እንዲሆን ማድረግ መቻሉን እንዲሁም የፋይናስ አቅሙ በ2010 ከስፖንሰር ሺፕ ከማልያ ሽያጭ፣ ከቡና ላኪዎች እና ከሌሎች የተገኘ አጠቃላይ ገቢ 47,801,399,41 ብር እንደሆነ፤ ለተለያዩ ተግባራት ወጪ 53, 024, 90 ብር እንደሆነ እና 4,898,201.00 ብር ያልተከፈለ እዳ እንዳለበት ገልፀዋል።

በ2010 ያጋጠሙ ዋና ዋና ችግሮችን መቶ አለቃ ፍቃደ ሲናገሩ የትራንስፖርት፣ የተጫዋች ትጥቅ፣ ጠንካራ ተጫዋቾችን በክፍያ ምክንያት ወደ ክለቡ አለመምጣት እና የእግርኳስ ሜዳ ላይ ያጋጠሙ ችግሮች እንደሆኑ በመናገር የ2011 የበጀት ዓመት ሊሰሩ የታሰቡት የስራ እና የወጪ ዝርዝሮችን አቅርበዋል። በ2011 ከአምናው በተሻለ ከፍተኛ ገቢ በተለያዩ ተግባራት ለመሰብሰብ ማቀዳቸውን አስታውቀዋል።

ክለቡ ለመንግስት ከ2006 – 2010 ጀምሮ 66, 144, 700, 83 ሚሊየን ብር ግብር መክፈሉን ክለቡ ምንያህል ህዝባዊ እንደሆነ እንደሚያሳይ ያብራሩት መቶ አለቃ ፈቃደ በቀጣይ ራሱን ወደ ዘመናዊነት ለመለወጥ የሚያደርገው ጥረት የሚያበረታታ ሲሆን ያሉበትን መሰናክሎች በማለፍ የታለመለት ግብ ላይ ይደርሰል ብለዋል። እስካሁን ላለው ስኬት ክለቡ ደጋፊዎቹን ከልብ ያመሰግናል ሲሉም አክለዋል። 


በመቀጠል በቀረበው ሪፖርት ከተሳታፊዎች ሀሳብ ቀርቧል። በተለያየ ጊዜ የክለቡ ስራ አስኪያጅ መቀያየር፣ ከፌዴሬሽኑ ጋር ያለው ግኑኝነት፣ የቴሌቭዥን ፕሮግራም አስመልክቶ እና ሌሎች ጥያቄ የቀረቡ ሲሆን በምላሹ መቶ አለቃ ፈቃደ የስራ አስኪያጅ መቀያየር በክለቡ የቦርድ አመራር ላይ ጫና እየፈጠረ መሆኑን እና በአሁኑ ወቅት የተረጋጋ ስራ አስኪያጅ ተቀጥሮ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል። “ከፌዴሬሽኑ ጋር ያለው ነገር ጥሩ ነው። እንዲያውም ዘንድሮ የጠየቅናቸውን ጥያቄዎች እየመለሱ ነው። ሆኖም የ2010 ገቢ ምንም አልተከፈለንም። ገንዘቡን ለማግኘት እየተነጋገርን ነው። ” ያሉት የቦርድ ሰብሳቢ የቴሌቪዥን ጣቢያን በተመለከተ ክለቡ ከጄ ቲቪ በመውጣት ከአርትስ ቲቪ ጋር ለመስራት ቅድመ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ገልፀው የተጫዋች ዝውውር ሂደት በጣም መስተካከል እንዳለበት ምላሽ ሰጥተዋል።


ጠቅላላ ጉባዔው ከሻይ እረፍት በኋላ ቀጥሎ በክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ስንታየው በቀለ አማካኝነት የ2011 እቅድ ሲቀርብ  ክለቡ የተለመዱ ዓመታዊ ክንውኖች እንዳሉ ሆነው በተለይ የስታዲየም ግንባታው ደረጃ በደረጃ የሚሰራ ቢሆንም መጫወቻ ሜዳውን ለልምምድ መስሪያ ለማድረስ መታቀዱን እና ስራ መጀመሩን እንዲሁም በታዳጊዎች ላይ ትኩረት በመስጠት ከፍተኛ ስራ እንደሚከናወን ገልፀዋል። ከጉባዔው አባላት በእቅድ ዙሪያ ጠቃሚ የሆኑ ገንቢ ሀሳቦች ከተሳታፊዎች ቀርቦ የጠቅላላ ጉባዔው የመጨረሻ አጀንዳ ወደ ሆነው ጉዳይ አምርቷል። 

በዚህም መሰረት የክለቡ የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፍቃደ ያቀረቡት የክለቡ የጠቅላላ ጉባኤ አባላት ከ41 ወደ 46 ከፍ እንዲል እንዲሁም የቦርድ አባላት ከ13 ወደ 15 ከፍ ብሎ ሁለቱ ተጨማሪ የቦርድ አባላት ከደጋፊ ማኅበሩ እንዲገቡ ለጉባዔው ሀሳብ አቅርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል። የአባላቱ ቁጥር በጥናት ላይ የተመሰረተ ይሁን፤ አሁን ባይጨመር፣ ሀሳቡ ጥሩ ነው ይፅደቅ የሚል እና የአባላቱ ቁጥር ከዚህ በላይም መጨመር አለበት የሚሉ ክርክሮች ከተካሄዱ በኋላ የመጀመርያው ሀሳብ ማለትም የጠቅላላ ጉባዔ አባላት ከ41 ወደ 46፤ የቦርድ አባላት ከ13 ወደ 15 እንዲጨምር ተስማምተው ውሳኔ አግኝቷል። በተጨማሪም የስታዲየም ግንባታ የኮሚቴ ማዋቀር ላይ ውይይት ተደርጓል። 


የጠቅላላ ጉባዔው ፍፃሜ ላይ የክብር እንግዳው ኮሎኔል ዐወል ንግግር ሲያደርጉ ” በኢትዮጵያ ውስጥ አንጋፋ ቡድን ከሆኑት እና በሚሊዮን የሚቆጠር ደጋፊዎች ባለቤት በሆነው የኢትዮጵያ ቡና ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በመገኘቴ ታላቅ ደስታ ይሰማኛል። ” በማለት ክለቡ ለሀገሪቷ እግርኳስ የሚጠቅም ሀሳቦች በጉባኤው ማንሳቱ ጠቃሚ መሆኑን ገልፀው ንግራቸውን ሲፈፅሙ የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት ኃይለየሱስ ፍስሀ በበኩላቸው ” ከክለቦች ጋር ተቀራርቦ የመስራት ችግር ቢኖርብንም አሁን አብረናቹ ለመስራት ተዘጋጅተናል። እናተም ቅረቡን” በማለት ተናግረው የጠቅላላ ጉባዔው ተጠናቋል።