ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ወላይታ ድቻ ከ ድሬዳዋ ከተማ

ቀጣዩ የስምንተኛ ሳምንት ቅድመ ዳሰሳችን ትኩረት ሶዶ ላይ ወላይታ ድቻ እና ድሬዳዋ ከተማን የሚያገናኘው ጨዋታ ይሆናል።

በሰባተኛ ሳምንት የሊጉ መርሀ ግብር ድል ያልቀናቸው ወላይታ ድቻ እና ድሬዳዋ ከተማ ነገ 09፡00 ላይ እርስ በርስ ይገናኛሉ። ባለሜዳዎቹ ወላይታድ ድቻዎች በሰንጠረዡ አጋማሽ ላይ የተቀመጡ ቢሆንም ሳምንት በጥሩ ሁኔታ ጀምረውት መሪ ከሆኑ በኋላ በመከላከያ የተረቱበት ጨዋታ እስከ አምስተኛ ደረጃ ከፍ የሚሉበትን ዕድል አሳልፈው የሰጡበት ነበር። የመጨረሻ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ደደቢትን ካሸነፈበት ጨዋታ ውጪ ድል ላልቀናው ድሬዳዋ ከተማም ያሳለፍነው ሳምንት መልካም የሚባል አልነበረም። ቡድኑ በሜዳው ደካማ አጀማመር እያደረገ ከሚገኘው ደቡብ ፖሊስ ጋር አቻ መለያየቱም ያልተጠበቀ ነበር። ዛሬ በተሰማው ዜና መሰረትም የቡድኑ አሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ መልቀቂያ በማስገባታቸው ነገ ምክትል አሰልጣኙ ስምዖን አባይ ድሬን እየመሩ ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይጠበቃል። ጨዋታውን ለሁለቱም ቡድኖች የሳምንት ውጤታቸውን የሚያስረሳ ድል ለማግኘት የሚያልሙበት ይሆናል።

ወላይታ ድቻ ጉዳት ላይ ይገኙ የነበሩት ኃይማኖት ወርቁ እና እርቅይሁን ተስፋዬን ቢያገኝም በነገው ጨዋታ ላይ ግን እንደማይጠቅምባቸው ታውቋል። በተመሳሳይ ሁለቱ ተጫዋቾቹን ራምኬል ሎክ እና ወሰኑ ማዜን በጉዳት ያጣው ደሬዳዋ ከተማ የነገውም ስብስቡ ውስጥ ሁለቱ ተጫዋቾች አልተካተቱም።

ማጥቃትን መሰረት ያደረገ አቀረረብ ያለው ወላይታ ድቻ ጨዋታው በሜዳው የሚደረግ እንደመሆኑም መጠን ተጋጣሚውን ተጭኖ እንደሚጫወት ይጠበቃል። በዋነኝነትም የመስመር አማካዮቹ ከድሬዳዋ የመስመር አማካዮች እና ተከላካዮች ጋር የሚያደርጉት ፍልሚያ ለፊት አጥቅው ባዬ ገዛኸኝ የግብ ዕድሎችን እንደሚፈጥሩ ይታሰባል። በተለይም የቡድኑ የግራ ወገን ተመራጩ የማጥቃት አቅጣጫ የመሆን ዕድል ይኖረዋል። በተመሳሳይ የድሬዎችም ማጥቃት በአመዛኙ ከመስመር የሚነሳ መሆኑ ጨዋታው በሁለቱ ኮሪደሮች በሚኖሩት ፍልሚያዎች የመወሰኑን ነገር ከፍ ያደርገዋል። በምክትል አሰልጣኙ እንደሚመራ በሚጠበቀው ድሬዳዋ በኩል ጥንቃቄ አዘል አቀራረብ ሊኖረው ቢችልም አምና አሰልጣኙ በያዙት ወቅት ከሜዳ ውጪም በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ወደፊት ገፍተው መጫወትን ይመርጡ የነበረ በመሆኑ ቡድኑ ነገ የአሰላለፍ ለውጥ ባያደርግም ሙሉ ለሙሉ በራሱ ሜዳ ላይ አፈግፍጎ ላይጫወት የሚችልበት ዕድል የሰፋ ነው።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ቡድኖቹ እስካሁን በተገናኙባቸው ስድስት ጨዋታዎች ወላይታ ድቻ ድል ቀንቶት አያውቅም።

– ሦስቱ ጨዋታዎች በድሬዳዋ አሸናፊነት ሲጠናቀቁ ቀሪዎቹ የአቻ ውጤት ተመዝግቦባቸዋል። በጨዋታዎቹ ድሬዎች ስድስት ግቦችን ሲያስቆጥሩ ድቻዎች ደግሞ አንድ ግብ ብቻ ቀንቷቸዋል።

– በወላይታ ድቻ ሜዳ ከተደረጉት ጨዋታዎች ውስጥ ሁለቱ በአቻ ሲጠናቀቁ አንዱን ድሬዳዋዎች አሸንፈዋል።

– ወላይታ ድቻ ዘንድሮ በሜዳው ሁለት ጨዋታዎችን አድርጎ ሁለቱንም በድል ሲወጣ በተመሳሳይ በሁለት አጋጣሚዎች ከሜዳቸው የወጡት ድሬዎች አንድ ነጥብ ብቻ አሳክተዋል።

ዳኛ

– ጨዋታው እያሱ ፈንቴ አራት የቢጫ ካርዶች እና አንድ የቀይ ካርድ ከመዘዘበት የአራተኛው ሳምንት የአዳማ ከተማ እና ሲዳማ ቡና ጨዋታ በኃላ የሚመራው ሁለተኛ ጨዋታው ይሆናል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ወላይታ ድቻ (4-1-4-1)

ታሪክ ጌትነት

እሸቱ መና – ዐወል አብደላ – ውብሸት ዓለማየሁ – ያሬድ ዳዊት

በረከት ወልዴ

ቸርነት ጉግሳ – አብዱልሰመድ ዓሊ – ኄኖክ ኢሳያስ – እዮብ ዓለማየሁ

ባዬ ገዛኸኝ


ድሬዳዋ ከተማ (4-4-2)

ሳምሶን አሰፋ

ገናናው ረጋሳ – አንተነህ ተስፋዬ – ፍቃዱ ደነቀ – ሳሙኤል ዮሃንስ

ሚኪያስ ግርማ – ፍሬድ ሙሺንዲ – ምንያህል ይመር – ሲላ አብዱላሂ

ኢታሙና ኬይሙኒ – ኃይሌ እሸቱ