ኢትዮጵያ 3-0 ብሩንዲ ፡ የጨዋታ ዳሰሳ


 

በዮናታን ሙሉጌታ


 

በ2016 በሩዋንዳ ለሚካሄደው የቻን የአፍሪካ ዋንጫ የመጨረሻ ማጣሪያ የብሩንዲ አቻውን 3ለ2 በሆነ አጠቃላይ ውጤት ያሸነፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ ውድድሩ በቀጥታ ማለፉን አረጋግጧል፡፡በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄደውና ቡድኑ 3ለ0 ባሸነፈበት ጨዋታ ላይ የታዩ አንዳንድ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ነጥቦችን እንደሚከተለው ቃኝተናቸዋል፡፡

 

ከሜዳ ውጪ የተደረገው ጨዋታ በብሩንዲ ብሔራዊ ቡድን 2ለ0 አሸናፊነት እንደመገባደዱ መጠን እንግዳው ቡድን በመከላከሉ ላይ ማዘንበሉ እንደማይቀር ከጨዋታው በፊትም የሚገመት ነበር፡፡በመሆኑም አብዛኛውን የጨዋታ ጊዜ ብሩንዲዎች ውጤታቸውን ለማስጠበቅ ከራሳቸው የሜዳ ክፍል ውጪ በቁጥር ኣንድ ወይም ሁለት ተጨዋቾችን ብቻ በመተው የተቀሩት በራሳቸው ሜዳ አጋማሽ ላይ በመሆን ተጋጣሚያቸው የመጫወቻ ክፈተትን እና የመጨረሻ ኳስ ማቀበያ ቀዳዳዎችን እንዳያገኝ በተቻለው መጠን በጥንቃቄ ተጫውተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በኩል የጐል እድሎችን በብዛት በመፍጠር እና በማስቆጠር ማሸነፍ እንዲሁም በጨዋታው ጐል ሳይቆጠርበት መውጣት መተኪያ የሌለው የጨዋታ እቅድ ነበር፡፡ የዮሐንስ ሣህሌ ብሔራዊ ቡድን መለያ እየተደረገ የሚሰወደው የ4-4-2 አጨዋወት በብሩንዲ ጨዋታ ላይ ቀዳሚው የጨዋታ ሲስተም ሆኖ ይታይ ነበር፡፡ በዚህም በተከላካይ መስመር ሥዩም ተስፋዬ ፣ አስቻለው ታመነ ፣ሳላዲን በርጌቾና ነጂብ ሳኒ በአማካይ ቦታ ላይ ጋቶች ፓኖም ፣ አስቻለው ግርማ ፣ ኤልያስ ማሞንና በረከት ይስሀቅን እንዲሁም ከፊት ራምኬል ሎክ እና መሐመድ ናስር የአጥቂውን መስመር በማስያዝ ነበር ቡድኑ ጨዋታውን የጀመረው፡፡ነገር ግን በአንዳንድ የጨዋታ አጋጣሚዎች እንዲሁም በተጨዋቾችም ስሜታዊ የሆነ ድንገተኛ የቦታ ለውጥ የቡድኑ አጨዋወት ወደ 4-3-3 የተለወጠ የሚመስሉባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡

በመቀጠል በእለቱ የነበረውን ጨዋታ ከማሳካት አኳያ የቡድኑየተከላካይ፣የአማካይ እና የአጥቂ ተሰላፊዎች የነበራቸውን ሚና ጠቅለል ባለመንገድ ለማየት እንሞክራለን፡፡

 

የተከላካይ መስመር

በጨዋታው የነበሩት የኋላ መስመር ተሰላፊዎቻችን ወደራሳቸው ግብ ተጠግተው እንዲከላከሉ የሚያደርግ ጥቃት ከተጋጣሚው ቡድን ያልነበረ በመሆኑ አብዛኛውን ሰዓት ወደሜዳው አጋማሽ በመጠጋት ተጫውተዋል፡፡ሁለቱ የመስመር ተከላካዮች ሥዩም እና ነጂብ ከሁለቱ የመሀል ተከላካዮች በአቋቋም ነጠል ብለው ከፊታቸው የሚገኙ አማካዮች ጋር በመቀራረብ እንደ አንድ የማጥቃት አማራጭ አገልግለዋል፡፡

1
ምስል 1 ፡ ከመሀል ተከላካዮቻችን ይጀመሩ ከነበሩ የማጥቃት ምሥረታ ኳሶች መካከል በአንዱ ላይ ሁለቱ የመስመር ተከላካዮቻችን ነጠል ብለው ቆመው ኳሱን በመቀበል በማጥቃት ላይ ለመሳተፍ ሲዘጋጁ

 

እንዲሁም ወደመሀል ሜዳው የቀረቡት ሁለቱ የመሀል ተከላካዮቻችን የማጥቃት እንቅስቃሴን ለማስጀመር የሚሆን ክፍተት በሚያጡባቸው አጋጣሚዎች ላይ ወደሁለቱ የመስመር ተከላካዮች ኳስን የመላክ አማራጭ እንዲኖራቸውም የሥዩምና ነጂብ የማጥቃት ተሳትፎ ጠቅሟል፡፡ሳላዲን እና አስቻለው በጨዋታው በመከላከሉም ሆነ ኳሶችን በማስጀመር ጥሩ የተንቀሳቀሱ ቢሆንም በተለይ ተገጣሚው ቡድን ድንገተኛ የማጥቃት እድሎች ሲፈጥር በግራና በቀኝ በኩል የሁለቱ የመስመር ተከላካዮች የሚተውትን ክፍት ቦታዎችን መሸፈኑ ላይ ከጋቶች ፓኖም ሽፋን ባላገኙባቸው አጋጣሚዎች ላይ ተቸግረው ታይተዋል፡፡ይህ ዓይነቱ አጋጣሚ በከባድ ተጋጣሚዎች ዘንድ በቀላሉ የግብ አጋጣሚዎችን ይፈጥራል፡፡በመሆኑም የመስመር ተከላካዮች የማጥቃት ተሳትፎ በሚፈለግበት ሰዓት እና የመሀል ተከላካዮቹ ወደ መሀል ሜዳ በሚቀርቡበት አጋጣሚ የተከላካይ አማካዩ የጋቾች ፓኖም ከቦታው ሳይርቅ ክፍተቶችን ለይቶ በቶሎ የመሸፈን ብቃቱ እጅጉን መሻሻል አለበት፡፡ይህም የመሀል ተከላካዮቹ ላይ የሚፈጥረውን ጫና ለመቀነስም ሆነ በተከላካዩና በአማካዩ መካከል የሚኖረውን ክፍተት ለማጥበብ በጣሙን ወሳኝ ነው፡፡

2
ምስል 2፡ በማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ ከነበረው ሥዩም ተስፋዬ የተቀማውን ኳስ ብሩንዲዎች ሦስት ለ ሦስት በሆነ አጋጣሚ ወደጐል ለመቀየር ሲሞክሩና የተከላካይ ክፍሉ ያለሽፋን ለጥቃት ሲጋለጥ

 

በተጨማሪም የማጥቃት ሂደት ላይ የሚሳተፉ የመስመር ተከላካዮቻችን መቼ ወደፊት መሄድ እንዳለባቸው በምን አጋጣሚ የአግድሞሽ ኳሶችን መጣል እንዳለባቸውና በምንዓይነት ጊዜና ክፍተት ከመስመር አማካዮች ጋር ባጭሩ ተጫውቶ ማለፍ እንዳለባቸው ማጤን ይገባቸዋል፡፡

 

3
ምስል 3፡ ብሩንዲዎች ወደፊት ተጠግቶ ከነበረው ነጂብ ሳኒ የነጠቁትን ኳስ ወደ ጐል ይዘው ሲሄዱ ወደ መከላከል በሚደረገው ሽግግር ላይ ሳላዲን በርጌቾና ጋቶች ፓኖም ከኳስ ኋላ የቀሩበት አጋጣሚ

 

የአማካይ መስመር

በእለቱ የተገኙት ጐሎች ምንጭ የቆሙ ኳሶች ነበሩ፡፡ የአማካይ ክፍላችን ለአጥቂዎቹ የመጨረሻ የግብ እድሎችን (በሳኦቶሜው ጨዋታ ላይ እንደታየው) በብዛት የመፍጠር ችግር ታይቶበታል፡፡ በእርግጥ የብሩንዲ ብሔራዊ ቡድን የተከላከለበት መንገድ ክፍተቶችን አብዝቶ የሰጠ አልነበረም፡፡አማካይ ክፍሉ በሁለቱ መስመሮች በበረከትና በአስቻለው አማካይነት እንዲሁም በመሀል በኤልያስ አማካይነት አጋጣሚዎችን የመፍጠር አካሄድ ነበረው፡፡ኤልያስ ማሞ ከአራቱ አማካዮች በነፃነት ብዙ የሜዳውን ክፍል መሸፈን የሚያስችል ኃላፊነት ነበረው፡፡ ከአጥቂዎች ጀርባ ያለው ቦታ ላይ በአብዛኛው ቢገኝና ኳሶችን ለአጥቂዎች ቢሰጥ እራሱም ወደ ግብ ቢሞክር ተመራጭ ይሆን ነበር፡፡ይህንንም በተወሰኑ አጋጣሚዎች ተግብሮታል፡፡ ውጤታማም ነበር፡፡ነገር ግን በበቂ ሁኔታ በዚያ ቦታ ላይ መገኘት አልቻለም፡፡ የዚህም ምክንያት ከሁለቱ የመሀል ተከላካዮች የሚነሱ ኳሶችን ለመቀበል ወደነሱ በሚቀርብባቸው አጋጣሚዎች ከአጥቂዎቹ ጀርባ የሚኖረውን ቦታ ለቆ መሄዱ ነው፡፡ለዚህም ከሱ ጀርባ የነበረው የጋቶች በማጥቃት ጨዋታዎች ጅማሮ ላይ ከተከላካዮቹ ኳስን ተቀብሎ በዙሪያው (በቀኙና በግራው ለሁለቱ የመስመር ተከላካዮች እንዲሁም ከፊቱ ለኤልያስ) የማሰራጨትን ሚና ለመወጣት በተገቢው ቦታ ላይ ያልተገኘባቸው አጋጣሚዎች መፈጠራቸው አንዱ ምክንያት ነው፡፡በዚህም የተነሳ የኤልያስ ማሞን የግብ አጋጣሚ የሚፈጥሩና የተጋጣሚን የመከላከል ቅርፅን ሊያዛቡ የሚችሉ እንቅስቃሴዎችን የመፍጠር ክህሎት ከዚህም በተሻለ በጨዋታው ልናይ የምንችልበት አጋጣሚ ሳይፈጠር ቀርቷል፡፡

4
ምስል 4፡ ጋቶች ፓኖም ነፃ ሆኖ በሜዳው አጋማሽ ላይ ሲገኝ ፣ኤልያስ ማሞ ወደ መሀል ተከላካዮቹ ቀርቦ ኳስን ለመቀበል ሲሞክር

 

5
ምስል 5፡ በምስሉ ላይ እንደሚታየው የብሩንዲ ተጨዋቾች ኳሱን ማቋረጥ የሚያስችል አቋቋም ይዘው እያለ በረከት እና ነጂብ በመስመር ተቀባብለው ለማለፍ የሞከሩበት ያልተሳካ አጋጣሚ

ሌላው የቡድኑ የማጥቃት አማራጭ የነበሩት ሁለቱ መስመሮች ነበሩ፡፡እነዚህ መስመሮች የመስመር አማካዮቹ በረከት እና አስቻለው ከኤልያስ ጋር እና ከበስተሁዋላቸው ከሚገኙት የመስመር አማካዮች ጋር በሚያደርጓቸው ቅብብሎሽ ወደፊት አልፈው ወደጐል በሚያሻሟቸው እንዲሁም ሁለቱ የፊት አጥቂዎች በተጋጣሚ የመሀልና የመስመር ተከላካዮች መሀል በሚፈጥሩት ክፍተት ተጠቅመው ወደ ተጋጣሚ የፍጹም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ በመግባት የሚጠቀሙባቸው ነበሩ፡፡ነገር ግን ከነዚህ ሁለት መስመሮች ከላይ በተጠቀሱት መንገዶች መገኘት የነበረባቸውን ያህል የማግባት እድሎች መፍጠር አልተቻለም፡፡ለዚህ በአብዛኛው እንደ ምክንያትነት የሚገለፀው የተጫዎቻችን ጊዜን እና ቦታን ያላማከሉ ቅብብሎቻቸውና ከመጠን ባለፈ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ኳስን ለመግፋት መሞከር ናቸው፡፡

 

6
ምስል 6 ፡ አስቻለው ግርማ በዙሪያው በብዛት በሚገኙ የብሩንዲ ተጨዋቶች ተከቦ ለማለፍ ሲሞክር እና ሲነጠቅ

 

በነዚህ ምክንያቶች ከበረከት እና አስቻለው የሚነሱ የማጥቃት አጋጣሚዎች አደጋ ከመፍጠራቸው በፊት በብሩንዲ ተከላካዮች በተደጋጋሚ ከሽፈዋል፡፡ሌላው ሁልጊዜም ከሚነሱት ችግሮች አንዱ የሆነው ከማጥቃት ወደ መከላከል የሚደረገው ሽግግር ነው፡፡በነዚህ ሁለት መስመሮች ለመፍጠር በሚሞከር የማጥቃት ጨዋታ መሀል በተሳሳቱ ቅብብሎሽ ኳስ በባላጋራ ተጨዋቾች ቁጥጥር ስር ስትወድቅ በፍጥነት ወደ መከላከል አቋቋም ከመመለስ ይልቅ በተበላሸው ኳስ መቆጨትና በመበሳጨት ያለምንም ተግባር ለተጋጣሚ ጊዜ መስጠት ወደፊት ከፍተኛ ዋጋ የሚያስከፍል አጉል ልምድ በመሆኑ ካሁኑ መወገድ ያለበት ነው፡፡

አጥቂዎች

ሁለቱ የፊት አጥቂዎች ምንም እንኳ በቂ የሆኑ የጐል እድሎችን ከአማካዮቹ ማግኘት ባይችሉም በተወሰኑ አጋጣሚዎች ወደመስመር በመውጣት ራሳቸው ይዘው ለመግባት ሙከራ አድርገዋል፡፡አልፎ አልፎ የተገኙትን እድሎችንም ወደ ጐልነት መቀየር ሲሳናቸው ቢታይም ከዚያ በላይ ግን እንደዚህ ዓይነት በመከላከል ላይ ያተኮረ ተጋጣሚ ለሙከራ እና ለቅብብል የሚሆን ክፍተትን ሳይሰጥ ሲቀር በምን ዓይነት አቋቋምና ቦታ አያያዝ ላይ በመሆን ቢያንስ አማካዮች ኳስ ይዘው መግባት የሚችሉበትን ክፍተት ቢፈጥሩ የተሻለ ነበር፡፡በሁለት አጥቂ የሚጫወት ቡድን የተጋጣሚን ተከላካዮች ሀሳብ ለመከፋፈል በአንድ አጥቂ ከሚጫወት ቡድን ይልቅ እድልን ያገኛል፡፡ይህን ማድረግ የሚቻለው ግን ሁለቱም አጥቂዎች እርስ በእርስ እንዲሁም ከመስመር እና ከአጥቂ አማካዮች ጋር በሚፈጥሩት ጥምረት ነው፡፡ብዙ በተንቀሳቀሱ ቁጥር እና ብዙ ኳሶችን በነኩ ቁጥር በተከላካዮቹ መሀል የሚገኙትን ክፍተቶች የማስፋት እድሎችን መፍጠር ይችላሉ፡፡

7
ምስል 7 ፡ የፍጹም ቅጣት ምት ባስገኘው አጋጣሚ ኤልያስ ለአስቻለው ያሾለካት ኳስ ላይ የራምኬ ሎክ እንቅስቃሴ በሁለቱ ተከላካዮች መሀል ያለው ርቀት እንዲሰፋ እና እሱን ለማጥበብ ሲሞክሩ በቀኝ በኩል ለአስቻለው የመሮጫ ቦታ ሲሰጠው ይታያል

 

በጥቅሉ ብሔራዊ ቡድኑ በሁለት አጋጣሚዎች ያሳየን ከሽንፈት በኋላ የነበረውን ጫና ሁሉ ተቋቁሞ በሜዳው ተጋጣሚዎችን ያሸነፈበት መንገድ የሚበረታታ ነው፡፡ይህን ዓይነቱን የአእምሮ ጥንካሬ በቀጣይ ላሉብን ሌሎች የማጣሪያ ጨዋታዎችም ይዞ መዝለቁ ወሳኝነት ይኖረዋል፡፡

እንዲሁም ጨዋታውን ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ በተመሳሳይ ፍጥነት እና ጉልበት ተጠቅሞ ማካሄዱ ለቡድኑ በተወሰነ መልኩ እርጋታን ከመስጠትም በላይ ወደ ጨዋታ መገባደድ ላይ ከሚኖሩ መዳከሞችና የትኩረት ስህተቶች ጠብቆታል፡፡

ሌላው ሊነሳ የሚገባው ጐሎቹ የተቆጠሩበት መንገድ ነው፡፡ በተለይ ከአጥቂዎቹ ጐሎችን ማግኘት ባልተቻለባቸው አጋጣሚዎች ከቆሙ ኳሶች በግንባር ተገጭተው የተቆጠሩት ጐሎች ቡድኑ ሁልጊዜ ከኋላ ተመስርተው በሚመጡ ኳሶች ላይ ብቻ ትኩረት አድርጐ አጋጣሚዎችን ከሚጠብቅ ይልቅ ከቆሙ ኳሶችም ጐሎችን ማግኘት እንደሚችል ያረጋገጡ ነበሩ፡፡

ሁሌም በሜዳ ላይ የሚፈለገውን ለማግኘት በተመሳሳይ መንገድ የሚጠቀምን ቡድን ለማቆም ለተጋጣሚዎች ቀለል ስለሚል እንደዚህ ዓይነት አማራጭ መንገዶችን መፍጠር መቻሉ ሊበረታታ ይገባዋል፡፡በቀጣይ ብሔራዊ ቡድኑ ያሉበትን ችግሮች ቀንሶ የተሻለ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ እንደሚያሳየን ተስፋ እናደርጋለን፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *