የአሰልጣኞች አስተያየት | ሲዳማ ቡና 0-0 ጅማ አባጅፋር

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ7ኛ ሳምንት ተስተካካይ መርሐ ግብር ዛሬ ሀዋሳ ላይ ሲዳማ ቡና ከጅማ አባጅፋር ያለ ግብ በአቻ ውጤት ካጠናቀቁበት ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ክለብ አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተውናል ፡፡

“የመጨረስ ችግር ታይቶብናል” ዘርዓይ ሙሉ ሲዳማ ቡና

ስለጨዋታው እና የመሣይ መውጣት

” መሳይ የወጣው ወደ ኃላ የተመለሰ ለማግኘት ከጅማ አጥቂ ጋር ሲገናኝ ተመትቶ ጣቱ የእብጠት ምልክት ስላሳየ ነው የወጣው። የሱ መውጣት ቅያሪዬን አበላሽቷል። የቡድኑን መንፈስ እና አጀማመራችንንም አበላሽቷል። ቢሆንም ለማስተካከል ሞክረናል። ዞሮ ዞሮ ኳሱን ለመቆጣጠር ሞክረናል። ተከላካይ ቀንሰን አማካይ አብዝተን ነበር ያስገባነው። ለማጥቃት ሞክረናል፤ ጨዋታውን ሙሉ ወደ ጎል ነው ስንሄድ የነበረው። ጅማዎች እድለኛ ናቸው። በዚህ አጋጣሚ የነሱን ግብ ጠባቂ ላደንቀው እፈልጋለሁ። ብዙ ኳሶች አድኖላቸዋል። ከዛ ውጭ ጅማ እንዴት ይጫወታል ብትለኝ እኔ አላውቅም፤ ከሜዳቸው ውጭ ስለሆነ እነሱ ማድረግ ያለባቸውን አድርገዋል። ብዙ ጊዜ ጎል ጋር ብንደርስም የመጨረስ ችግር ታይቶብናል። አጥቂዎቻችን ጋርም የነበረው ችግር ይሄ ነው። ”

የአዲስ ግደይ እንደወትሮው ያለመሆን

የጨዋታ መደራረብ ግልፅ ነው። ይህ ሜዳ ደግሞ ራሱን የቻለ አቅም ይፈልጋል። ከሶስት ቀን በኋላ ነው በድጋሚ የተጫወትነው። ይህ ደግሞ አንድ ተፅዕኖ ፈጥሮብናል። የኛ ተጫዋቾች ፈጣኖች ስለሆኑ ያላቸውን ያላቸውን ነገር ስለሚሰጡ ያንን ነገር ድካም አልለውም። አዲስም ጎል ለማግባት ያለው ጉጉት ነው እንጂ ሌላ ጊዜ ከሚያገባቸው እጅግ በተሻለ ጎል ጋር ደርሷል። ከዚህ ውጭ ምንም የታየኝ ነገር የለም። የኛ ችግር ተረጋግቶ የማስቆጠር ብቻ ነው።

“የጨዋታ መደራረብ ተፅዕኖ ፈጥሮብናል” ዩሱፍ ዓሊ – ጅማ አባጅፋር (ረዳት አሰልጣኝ)

ጥሩ ሲጫወቱ የነበሩት አስቻለው እና መስዑድ ስለመቀየራቸው

የኛ ተጫዋቾ አብዛኛዎቹ ኳስ ይዘው የሚጫወቱ ናቸው። በሜዳችን ባለፈው ስንጫወት ጥሩ አልነበርንም፤ ዛሬ ግን ሜዳው ተመችቷቸዋል።
በዛሬው ጨዋታ እንዳያችሁት በቀይ ካርድ ተጫዋች ወጥቶብን በጎዶሎ ነው የተጫወትነው። መስዑድን አስወጥተን ያስገባነው አማካይ ቢሆንም የመከላከል አቅምም ያለውን ነው። መጀመሪያ ኳስን የሚጫወቱ ተጫዋቾች ነበሩ ከሜዳው አኳያ በደንብ እንዲጫወቱም ነበር ያደረግነው። ቀይረን ስናስገባ ግን የመከላከልም ለማጥቃትም አስበን ነበር። ለምሳሌ መስዑድን ስታዩት ብዙ ጊዜ ኳሱን ይዞ ነው የሚጫወተው የመከላከል ባህሪ ብዙም የለውም። ጎዶሎ ስለሆንን ደግሞ ተከላክሎም አጥቅም የሚጫወት ተጫዋች ስለፈለግን አስቻለውንም መስዑድንም አውጥተናል።”

ሰለ ጨዋታ መደራረብ

“የጨዋታ መደራረብ እኛን ተፅዕኖ ውስጥ ከቶናል። በየሶስት ቀን ልዩነት ነው የምንጫወተው። እኛ አሁን ለሞሮኮው ጨዋታ ምንም እየተዘጋጀን አይደለም። በየሶስት ቀን የምንጫወተው ፕሪምየር ሊጉን ነው። ለዛ ደግሞ ክፍተት እንድናገኝ ለዝግጅት ጠይቀን ነበር። ከጨዋታ ወደ ጨዋታ ነው እየገባን ያለነው። ይህ ደግሞ ተፅዕኖ ፈጥሮብናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *