ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና ሽረን በማሸነፍ በመሪነቱ ቀጥሏል

ደካማ እንቅስቃሴ በታየበት የዛሬው የአዲስ አበባ ስታድየም የዘጠነኛ ሳምንት ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና በአቡበከር ነስሩ ብቸኛ የፍፁም ቅጣት ምት ጎል ስሐል ሽረን 1-0 ማሸነፍ ችሏል።

ኢትዮጵያ ቡና በሸገር ደርቢ ከተጠቀመበት ቡድኑ ጉዳት የገጠመው አማኑኤል ዮሃንስ እና ሳምሶን ጥላሁንን በማሳረፍ ዳንኤል ደምሴ እና ሱለይማን ሎክዋን ወደ መጀመሪያ አሰላለፍ አምጥቷል። ሽረዎች በበኩላቸው ከመቐለ ያለግብ ከተለያዩበት ጨዋታ ግብጠባቂው ሐፍቶም ቢሰጠኝን በሰንደይ ሮቲሚ ፤ መሀል ተከላካዩ ነፃነት ገብረመድህንን ከቅጣት በተመለሰው ዲሜጥሮስ ወልደስላሴ እንዲሁም የአጥቂ አማካዩ ልደቱ ለማን በኢብራሂማ ፎፋና በመተካት ወደ ሜዳ ገብተዋል።

በተመጣጣኝ እንቅስቃሴ የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ለረጅም ደቂቃዎች በፍጥነቱ ዝግ ያለ እና ጠንካራ ሙከራዎች የማይታዩበት ሆኖ ነበር የቀጠለው። ሳምንት በገባባት አኳኋን ሦስት የመሀል ተከላካዮችን ተጠቅሞ በ3-4-3 ጨዋታውን የጀመረው ኢትዮጵያ ቡና ተጋጣሚው ከራሱ አጋማሽ እምብዛም እንዳይወጣ ቢያደርግም የኳስ ቁጥጥሩ ግን ከመሀል ሲያልፍ አይታይም ነበር። ቡናዎች 8ኛው ደቂቃ ላይ አቡበከር ከቀኝ መስመር ባሻማው እና ተቀባይ ባልነበረውን ኳስ ብቻ ነበር በመጀመሪያዎቹ 15 ደቂቃዎች ወደ ሽረ ሳጥን ማስገባት የቻሉት። 19ኛው ደቂቃ ላይ አቡበከር ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ያልተጠቀመበት ኳስ ደግሞ ቡድኑ በተሻለ ሁኔታ የፈጠረው ግልፅ የማግባት አጋጣሚ ነበር። በአመዛኙ ግን የኢትዮጵያ ቡና የአማካይ ክፍል ቅብብሎች በሚፈለገው መጠን የተጋጣሚያቸውን የኋላ ክፍል ማስከፈት ተስኗቸው ቆይቷል።

መጠነኛ ብልጫ የተወሰደባቸው ሽረዎችም ወደ ቡና አጋማሽ ይገቡ የነበረው በተወሰኑ አጋጣሚዎች ብቻ ነበር። መሀል ላይ የሚያቋርጧቸው ኳሶችን ወደ ፊት ቢያሳልፉም ከቡና ሦስት ተከላካዮች ጋር በቅርብ ርቀት ይታዩ የነበሩት የቡድኑ ሁለት አጥቂዎች ተፅዕኖ አስጨናቂ መሆን አልቻለም። ሆኖም ሽረዎች ከተጋጣሚያቸው የተሻሉ አደገኛ የግብ አጋጣሚዎችን መፍጠር የቻሉ ሲሆን እነዚህ ዕድሎች የተገኙትም በኢትዮጵያ ቡና የሜዳ አጋማሽ ከሚነጠቁ ኳሶች ነበር። በተለይም 35ኛው ደቂቃ ላይ ከአህመድ ረሺድ በተቀማ ኳስ ሽረዎች ሦስት ለሦስት ሆነው ሳጥን ውስጥ ቢገቡም ኪዳኔ አሰፋ የሰጠውን ኳስ ኢብራሂማ ፎፋና ወደ ግብ ቢሞክርም ግብ ጠባቂው አድኖበታል። ከዚያ አስቀድሞ 22ኛው ደቂቃ ላይ ከመሀል ከተጣለ ረጅም ኳስ ፎፋና በግንባሩ ሲጨርፍለት ሚድ ፎፋና የሞከረው ኢላማውን የጠበቀ ሙከራም በእንግዶቹ በኩል ተጠቃሽ ነበር።

ከ35ኛው ደቂቃ በኃላ አሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስ ከሦስቱ ተከላካዮች መካከል ንታንቢን ወደ መሀል በማስገባት ወደ 4-2-3-1 አሰላለፍ መምጣታቸው ኢትዮጵያ ቡናን የተሻለ የመቀባበያ አማራጭ ሲፈጥርለት ታይቷል። የለውጡ ፍሬም ከደቂቃዎች በኋላ ዳንኤል ደሜ ለሱለይማን ሎክዋ ባደረሰው ረጅም ኳስ የታየ ነበር። ሎክዋ ኳሱን ወደ ውስጥ ለማሳለፍ ሲሞክር ክብሮም ብርሀነ በእጁ በመንካቱ የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል። የፍፁም ቅጣት ምቱን አቡበከር ነስሩ አስቆጥሮም ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል። የፍፁም ቅጣት ምቱ ከመመታቱ አስቀድሞ ውሳኔውን የተቃወሙት የሽረ ቡድን አባላት ተጫዋቾቻቸውን ወደ ሜዳው ጠርዝ መጥራታቸውን ተከትሎ ወደ ግቡ ለመመለስ ጊዜ የወሰደው ሰንደይ ሮቲሚ የማስጠንቀቂያ ካርድ ተመልክቷል።

ከእረፍት መልስ ጨዋታው ይበልጥ ማራኪነቱን አጥቶ አሰልቺ በሆነ መንገድ ተጀምሮ የተጠናቀቀ ነበር። በድጋሜ አሰላለፋቸውን በመቀየር ሚኪያስ እና አቡበከርን ከሎክዋ ግራ እና ቀኝ በማሰለፍ በ4-3-3 ወደ ሜዳ የተመለሱት ቡናዎች ሚኪያስ ወደተሰለፈበት የቀኝ መስመር አድልተው ለማጥቃት ጥረታቸውን ቢቀጥሉም መረጋጋት የማይታይበት ቅብብላቸው በተደጋጋሚ እየተቆራረጠ ውጤታማነታቸውን አውርዶታል። የቡድኑ ተጫዋቾች በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ወቅትም የሚወስኗቸው የተዛቡ ውሳኔዎች የኳስ ፍሰቱን ወደ ግብ ዕድልነት እንዳይቀየር እንቅፋት ሆኖ ታይቷል። 64ኛው ደቂቃ ላይ አቡበከር ነስሩ በግራ በኩል ወደ ውስጥ ገብቶ ያደረገው ሙከራም የተሻለ የሚባለው የቡድኑ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ነበር።

ልደቱ ለማ እና ሰለሞን ገብረመድህንን ካስገቡ በኋላ መሀል ላይ ከተጋጣሚያቸው የተሻለ መረጋጋት ይታይባቸው የነበሩት ሽረዎችም ወደ ግብ የደረሱት በጥቂት አጋጣሚ ነው። ጅላሉ እና ሰለሞን ከሳጥን ውስጥ ኄኖክ ካሳሁን ደግሞ ከርቀት ያደረጓቸው ሙከራዎች በዚህ ረገድ የሚጠቀሱ ነበሩ። ከረጅም ሳምንታት በኋላ ወደ ሜዳ የተነለሰው ሠለሞን በድጋሜ ተጎድቶ ከወጣ በኋላ ግን ቡድኑ የታየበት መነቃቃት እየተቀዛቀዘ ሄዷል። በዚህ ሰዓት ላይ በአምበሉ ኄኖክ ካሳሁን እና በአጥቂው ሚድ ፎፋና መሀል የተፈጠረው አለመግባባታም የጨዋታው ሌላ አነጋጋሪ አጋጣሚ ነበር። በጥቅሉ ሁለቱም ቡድኖች የማይረበሹ እና ወጥትነት ያላቸው ቅብብሎች እያደረጉ ጎል ላይ ከሚደርሱባቸው እንቅስቃሴዎች ይልቅ በመቀማማት እና በመቆራረጥ የተሞሉ ቅብብሎች የተበራከቱበት ሁለተኛ አጋማሽ ከባባድ ሙከራዎችን ሳያስመለክተን እና ተጨማሪ ግብም ሳይቆጠርበት ጨዋታው በኢትዮጵያ በና 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *