ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ወልዋሎ ዓ/ዩ ከ ፋሲል ከነማ

ከ9ኛ ሳምንት ጨዋታዎች መካከል ዛሬ በብቸኝነት በሚደረገውን እጅግ ተጠባቂው የወልዋሎ ዓ/ዩ እና ፋሲል ከነማ ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል። 

በሊጉ በርካታ ተስተካካይ ጨዋታዎች እንዲኖሩ ምክንያት የነበረው እና ተደጋጋሚ ውይይቶች እየተደረጉ ቢቆዩም መቼ ፈር ሊይዝ እንደሚችል ግራ ያጋባ የነበረው የአማራ እና ትግራይ ክለቦች ጉዳይ ዛሬ በዚህ ጨዋታ እንደሚፈታ ይጠበቃል። ፋሲል ከነማ ወደ መቐሌ ለመጓዝ ፍቃደኛ መሆኑን ማረጋገጫ ከሰጠ በኋላ ይህ ጨዋታ እንደሚደረግ ሲታወቅ ጀምሮ ጨዋታው ልዩ ትርጉም ተሰጥቶት ቆይቷል። በዛሬው የጨዋታ ቀንም በብቸኝነት በትግራይ ስታድየም ከ9፡00 ጀምሮ እንደሚከናወን ይጠበቃል። አምና የተፈጠሩት ችግሮች ከመከሰታቸው በፊት የሁለቱ ክልል ክለቦች በሜዳቸው ያስተናገዱት የመጀመሪያ እና ብቸኛ ጨዋታ ዓዲግራት ላይ የተደረገው የፋሲል እና ወልዋሎ ጨዋታ መሆኑ ደግሞ የተለየው የታሪክ አጋጣሚ ነው። 

እስካሁን ስምንቱንም የሊግ ጨዋታዎች ያደረጉት ወልዋሎዎች በ11 ነጥቦች ስምንተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ከኢትዮጵያ ቡና እና ጅማ አባ ጅፋር ካደረጓቸው የሜዳ ውጪ ጨዋታዎች አንድ ነጥብ አሳክተው ከተመለሱ በኋላም ነው ዛሬ ፋሲል ከነማን በሜዳቸው የሚያስተናግዱት። ከተጋጣሚያቸው አንፃር ሁለት ያላደርጓቸው ጨዋታዎች ያሉ ቢሆንም በእኩል ነጥብ በግብ ክፍያ በልጠው ስድስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ፋሲሎች በበኩላቸው ሳምንት ከደደቢት ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ መተላለፉ የሚታወስ ነው። ከዚያ አስቀድሞም ቡድኑ ወደ ድሬዳው አቅንቶ በ 1-0 ድል መመለስ ችሏል። 

በዛሬው ጨዋታ የወልዋሎ ዓ/ዩዎቹ ዳንኤል አድሓኖም ፣ ዋለልኝ ገብሬ ፣ ኤፍሬም ኃይለማርያም  እና ሮቤል አስራት በጉዳት ከጨዋታው ውጪ ሲሆኑ የሪችሞንድ ኦዶንጎ መሰለፍም አጠራጣሪ ሆኗል። ከዚህ ውጪ አስራት መገርሳ በስምንተኛው ሳምንት በተመለከተው የቀይ ካርድ ምክንያት ከጨዋታው ውጪ ነው። በፋሲል ከነማ በኩል አጥቂው  ፋሲል አስማማው በጉዳት እንዲሁም ዩጋዳዊው አማካይ ያስር ሙገርዋ በሀዘን ምክንያት ወደ ሀገሩ በመጎዙ የማይሰለፍ ተጫዋች ይሆናል።

ሁለቱም ቡድኖች የኳስ ቁጥጥር የበላይነት መያዝ ላይ ተመስርተው የሚጫወቱ በመሆናቸው ጨዋታው መሀል ላይ ብርቱ ፉክክር እንደሚደረግበት ይጠበቃል። ባለሜዳዎቹ ወልዋሎዎች ጥንቃቄን በሚመርጡበት ጊዜ ለመስመር አጥቂዎቻቸው የሚሰጡትን የመከላከል ኃላፊነት በመተው ወደ ፊት ገፍተው በአጥቂው ግራ እና ቀኝ እንዲሰለፉ እንደሚያደርጉ ሲጠበቅ በጉዳት እና ቅጣት የሳሳው የመሀል ክፍላቸው የበላይነት ከተወሰደበት ግን ተመሳሳይ መንገድ እንደሚከተሉ ይገመታል። መሀል ላይ ብልጫውን ለመውሰድ ዕድሉ ያላቸው ፋሲል ከነማዎች የሚያገኙትን የኳስ ቁጥጥር የበላይነት በአጫጭር ቅብብሎች  ከተጋጣሚያቸው የተከላካይ መስመር ጀርባ ለመግባት እንደሚጠቀሙበት ይጠበቃል። በዚህ ሂደትም ቡድኑ ከቀጥተኛ ጥቃት ይልቅ የመስመር አጥቂዎቹን ፍጥነት እንደሚጠቀም ሲጠበቅ ከነሱራፌል ዳኛቸው የሚነሱ ቀጥተኛ ኳሶችም ልዩነት ሊፈጥሩ የሚችሉበት አግባብ ይኖራል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ወልዋሎ ዓ/ዩ ወደ ሊጉ በገባበት ያሳለፍነው የውድድር ዓመት የመጀመሪያ ጨዋታ ዓዲግራት ላይ ተገናኝተው 2-2 ሲለያዩ በሁለተኛው ዙር አዲስ አበባ ላይ የተደረገው ጨዋታ ደግሞ በፋሲል ከነማ በ1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

– ወልዋሎ ዓ/ዩ ትግራይ ስታድየም ላይ እስካሁን ካደረጋቸው አራት ጨዋታዎች ውስጥ ሁለቱን ሲያሸንፍ በአንዱ የአቻ ውጤት በሌላኛው ደግሞ ሽንፈት ገጥሞታል። 

– ፋሲል ከነማ ዘንድሮ ሦስት ጊዜ ከሜዳው የወጣ ሲሆን ሁለቱን በድል አጠናቆ ሲመለስ በአንዱ ሽንፈት ገጥሞታል።

– ወልዋሎ ዓ/ዩ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ግብ አላስቆጠረም።

– ፋሲል ከነማ እስካሁን በሊጉ ካደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች በአንዱ ብቻ ግብ ሳያስቆጥር የወጣ ሲሆን ከመጀመሪያው ሳምንት በኋላም ሽንፈት አላገኘውም።

ዳኛ

– ባህር ዳር ከተማ ከሀዋሳ ከተማ እንዲሁም ድሬዳዋ ከተማ ከደቡብ ፖሊስ ያደረጋቸውን ጨዋታዎች በመምራት ስድስት የማስጠንቀቂያ ካርዶችን የመዘዘው ፌደራል ዳኛ አክሊሉ ድጋፌ በዚህ ጨዋታ ላይ በመሀል ዳኝነት ተመድቧል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ወልዋሎ ዓ.ዩ (4-3-3)

አብዱልዓዚዝ ኬይታ

እንየው ካሳሁን –  ደስታ ደሙ – ቢኒያም ሲራጅ – ብርሀኑ ቦጋለ

አማኑኤል ጎበና – ብርሀኑ አሻሞ – አፈወርቅ ኃይሉ

ፕሪንስ ሰቨሪንሆ – ሪችሞንድ ኦዶንጎ – ኤፍሬም አሻሞ

ፋሲል ከነማ (4-3-3)

ሚኬል ሳማኬ

ሰዒድ ሁሴን – ያሬድ ባየህ – ሙጂብ ቃሲም – አምሳሉ ጥላሁን

ሐብታሙ ተከስተ – ከድር ኩሊባሊ – ሱራፌል ዳኛቸው  

ሽመክት ጉግሳ – ኢዙ አዙካ – አብዱራህማን ሙባረክ

              

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *