የአሰልጣኞች አስተያየት | ኢትዮጵያ ቡና 1-0 ስሑል ሽረ

ዛሬ በአዲስ አበባ ስታድየም በብቸኝነት በተካሄደው የሊጉ 9ኛ ሳምንት ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ስሑል ሽረን አስተናግዶ 1-0 መርታት ችሏል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላም የቡድኖቹ አሰልጣኞች ይህንን ብለዋል።

” ዛሬ በጣም መጥፎ አቋም ነው ያሳየነው ” ዲዲዬ ጎሜስ – ኢትዮጵያ ቡና 

ስለጨዋታው

” ለኛ በጣም መጥፎ ጨዋታ ነበር። እውነቱን ለመናገር ምንም ያሻሻልነው ነገር የለም። በጥቂቱ ጨዋታውን ተቆጣጥረን ነበር። ነገር ግን በጣም ያዘንኩበት ጨዋታ ነው ፤ የደጋፊዎቻችንንም ስሜት እረዳለው። ነገር ግን ምንም እንኳን መጥፎ ጨዋታ ብናሳልፍም አሁንም አንደኛ ደረጃ ላይ መሆናችን ጥሩ ነገር ነው። ”

ስለጨዋታው ዕቅድ እና ስለተደረጉ ማስተካከያዎች

” ጨዋታውን አጥቅተን ለመጫወት በ3-4-3 ነበር የጀመርነው። ነገር ግን ቅብብሎቻችን በጣም መጥፎ ነበሩ። በተደጋጋሚ ኳሶችን እንነጠቅ ነበር። ይህ ያልተለመደ ነገር ነው ፤ በአብዛኛውም እንደዚህ በመጫወት አንታወቅም። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ አካባቢ ንታንቢን ወደ መሀል በማምጣት ለውጦችን አድርጊያለው ፤ ከዛ በኋላም ነበር መሪ የሆንነው። በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ ሚኪያስ እና አቡበከርን በመስመር አጥቂነት ተጠቅመናል። ሆኖም ዛሬ በጣም መጥፎ አቋም ነው ያሳየነው። በዚህ መንገድ መቀጠል የሌለብን በመሆኑም በቀጣዩ ጨዋታ ብዙ መሻሻል ይኖርብናል። በተለይ ደግሞ በማጥቃቱ በኩል። ከአስራት ፣ አማኑኤል እና ሳምሶን አለመኖር ጋር ተያይዞ ብንቸገርም ዛሬ በጣም መጥፎ አቋም ማሳየታችንን ግን አንክድም። ”

” ዳኛው ነው ያሸነፈን እንጂ ጨዋታው ከባድ አልነበረም። ” ዳንኤል ፀኃዬ – ስሐል ሽረ

” ውጤቱ ለኛ አይገባንም ፤ ዳኛው ነው ያሸነፈን እንጂ ጨዋታው ከባድ አልነበረም። ይዘነው በገባነው ስትራቴጂ እስከምንፈልገው ደቂቃ ድረስ ጠብቀን ወደ ማጥቃት ለመግባት ነበር ያሰብነው። ነገር ግን ዳኛው ከኳስ ጀርባ ሆኖ በወሰነው ውሳኔ ተሸንፈናል። በርግጥ ከዳኛ ጋርም ማሸነፍ ይጠበቅብናል ነገር ግን ተጫዋቾቼም ስሜታዊ ሆኑ ፤ ይህም ዋጋ አስከፍሎናል። ”

ስለፍፁም ቅጣት ምቱ

” ፍፁም ቅጣት ምት ቢሆን ኖሮ ረዳት ዳኛው ይዞር ነበር ፤ ምክንያቱም ፊት ለፊት የሚታየው ለሱ ነበር። ነገር ግን ዳኞቹ ራሱ አልተግባቡም። ዳኛው የሚታየው አቋቋም ላይ ሆኖ ቢሆን ኖሮ እኛም አንከራከርም ነበር። አንድን ቡድን ለመጥቀም አንድን ቡድን ለመጉዳት የተደረገ ስለሆነ በጣም ነው ያዘነው። ”

ስለሁለተኛው አጋማሽ

” በመከላከል ዞን ቆይተን በመልሶ ማጥቃት ለመሄድ ነበር ሀሳባችን። መስመሮቹን ለመጠቀምም አቅደን ነበር። ነገር ግን በመሀል ጎል ስናስተናግድ ነገሮች ተቀይረዋል። አንዳንዴ የገባውን ግብ የማትቀበለው ሲሆን ነገሮችን ለመተግበር ከባድ ይሆናል። ከእረፍት መልስም በምንፈልገው መጠን ወደፊት ባንሄድም ከግብ ጠባቂ ጋር ሁለት ሦስት ጊዜ ተገናኝተን ነበር ፤ ማስቆጠር አልቻልንም እንጂ ያንን ብንጠቀም አሸንፈን መውጣትም እንችል ነበር። ”

ፍፁም ቅጣት ምቱ ሊመታ ሲል ግብ ጠባቂው በቦታው ስላለመገኘቱ

” የጠራነው ልንመክረው ነው። በወቅቱ ተጫዋቾቹ አልተረጋጉም ፤ ሁሉም ወደ ዳኛው ነው የሮጡት። እስከመጨረሻው እየተከራከሩት ነበር ፤ እስካሁንም አልወጣላቸውም። ስለዚህ የካርድ ሰለባም እንዳንሆን ተጫዋቾችን ወደ ሜዳው ጠርዝ ጠርተን ለማረጋጋት ሞክረናል። “

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *