ከፍተኛ ሊግ ሐ | ሀዲያ ሆሳዕና መሪነቱን ሲያጠናክር ቤንች ማጂም አሸንፏል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሐ 6ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከአንዱ በቀር እሁድ ተከናውነው ሀዲያ ሆሳዕና እና ቤንች ማጂ ቡና አሸንፈዋል።

ወደ ነቀምት ያመራው ሀዲያ ሆሳዕና 1-0 አሸንፎ ተመልሷል። ከእረፍት መልስ በ48ኛው ደቂቃ በእንዲሪስ ሳፊ የሀዲያ ሆሳዕናን ብቸኛ ጎልን ማስቆጠር ሲችል ውጤቱን ተከትሎ ሀዲያ ሆሳዕና አንድ ጨዋታ ከሚቀረው አርባምንጭ ያለውን ልዩነት ወደ አራት ማስፋት ችሏል።

ቤንች ማጂ ቡና ሚዛን አማን ላይ ጅማ አባ ቡናን አስተናግዶ 3-1 አሸንፏል። ወንድምአገኝ ኪራ ሁለት ጎሎችን ሲያስቆጥር ኃይለየሱስ ኃይሉ ቀሪዋን የቤንች ማጂ ጎል ማስቆጠር የቻለ ተጫዋች ነው።

ቡታጅራ ላይ ከሁለት ተከታታይ ሳምንት በኋላ ወደ ጨዋታ የተመለሰው ቡታጅራ ከአርባምንጭ 3-3 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይቷል። በ33ኛው ደቂቃ ክንዴ አቡቹ ለቡታጅራ ቀዳሚውን ግብ ቢያስቆጥርም በ40ኛው ደቂቃ ላይ ስንታየው መንግስቱ አርባምንጭን አቻ አድርጓል። በ43ኛው ደቂቃ ሙሉቀን አሰፋ ቡታጅራ በድጋሚ መሪ አድርጎ ወደ እረፍት ያመሩ ሲሆን በ54ኛው ደቂቃ ላይ ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ሶስተኛ ጎል ሙሉቀን አሰፋ አስቆጥሮ የግብ ልዩነቱን ከፍ ማድረግ ችሏል። ሆኖም በ58ኛው ደቂቃ አለልኝ አዘነ እንዲሁም በ81ኛው ደቂቃ ላይ ፍቃዱ መኮንን ለአርባምንጭ ግብ አስቆጥረው ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ሻሸመኔ ላይ ሻሸመኔ ከተማ ከሺንሺቾ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ሲለያዩ ቦረና ላይ ነገሌ ቦረና ከቢሾፍቱ አውቶሞቲቪ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *