ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ሲዳማ ቡና ከ ኢትዮጵያ ቡና

ከአስረኛ ሳምንት ጨዋታዎች መካከል ሲዳማ ቡና እና ኢትዮጵያ ቡናን በሚያገናኘው ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ጉዳዮች ለማንሳት ወደናል።

አንደኛ እና ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ኢትዮጵያ ቡና እና ሲዳማ ቡና በሀዋሳው ሰው ሰራሽ ሜዳ  10፡00 ላይ ተጠባቂ ጨዋታ ያደርጋሉ። መቐለ ላይ የዓመቱ የመጀመሪያ ሽንፈት የገጠመው ሲዳማ ቡና ከሮድዋ ደርቢ ድል በኋላ መቀዛቀዝ ታይቶበታል። ከሳምንቱ ሽንፈት በፊትም በሜዳው ጅማ አባ ጅፋርን ያስተናገደበት ጨዋታ ያለግብ ነበር የተጠናቀቀው። የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ ቡና ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ከአዲስ አበባ ይወጣል። በነዚህ ጨዋታዎች ያሳካቸው አስር ነጥቦችም መሪነቱን ከሀዋሳ ተረክቦ በሰንጠረዡ አናት ላይ እንዲቆይ አስችለውታል። ቡድኖቹ ካሉበት ደረጃ አንፃር ጨዋታው በመሪነት ፉክክሩ ላይ ተፅዕኖ የመፍጠር አቅም ስላለው ከአስረኛ ሳምንት ጨዋታዎች መካከል ትልቅ ግምት የሚሰጠው ነው።

ሲዳማ ቡና በነገው ጨዋታ ግብ ጠባቂው መሳይ አያኖን በጉዳት ምክንያት የማያሰለፍ ሲሆን የኢትዮጵያ ቡናዎቹ አማኑኤል ዮሀንስ እና አስራት ቱንጆም ከጉዳት አላገገሙም። ከዚህ ውጪ የግራ መስመር ተከላካዩ ተካልኝ ደጀኔም በጋብቻ ስነ ስርዓቱ ምክንያት ወደ ሀዋሳ አልተጓዘም።

በጨዋታው ሲዳማ ቡና በሦስቱ የፊት መስመር ተሰላፊዎቹ በተለይም በአዲስ ግደይ አማካይነት የሚፈጥረው ጫና ለቡና የኋላ ክፍል ፈተና የመሆን ዕድሉ የሰፋ ነው። ቡድኑ የሚያገኛቸውን ኳሶች በፍጥነት ወደ መስመር አጥቂዎቹ በመላክ እንዲሁም ቡናዎች ከኋላ ኳስ ሲጀመሩ አፍኖ ለማስቀረት በመሞከር ላይ ተመስርቶ በማጥቃት ጨዋታውን እንደሚያከናውንም ይጠበቃል። ተለዋዋጭ ቅርፅ ይዞ ወደ ሜዳ ሲገባ የሚታየው የአሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜሱ ኢትዮጵያ ቡና ከአማኑኤል ጉዳት በኋላ አማካይ ክፍል ላይ የተሳኩ ቅብብሎችን መከወን እና ተጋጣሚን የሚያስጨንቅ የተደራጀ ጥቃት በመሰንዘር በኩል ተዳክሞ እየታየ ነው። ሆኖም ነገ እንደሚመርጠው ቅርፅ ቢወሰንም መሀል ላይ ብልጫ የመውሰድ ዕድል ሲኖረው የመስመር ተከላካዮቹን ወደ ፊት አስጠግቶ ለአጥቂዎቹ በማቅረብ አስፍቶ የሲዳማን የተከላካይ ክፍል ለማስከፈት እንደሚጥር ይገመታል። ከካሉሻ አልሀሰን የሚነሱ ተሻጋሪ ኳሶችም ለዚህ አካሄድ አጋዥ እንደሚሆኑ ሲጠበቅ አጋጣሚዎችን ከመፍጠር ባለፈ የተዳከመው የቡድኑ የአጨራረስ ብቃት ካልተፈታ ግን ነገም ከክፍት ጨዋታ ግቦችን ለማግኘት እንዲቸገር ሊያደርገው ይችላል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሲዳማ ቡና ወደ ፕሪምየር ሊጉ ካደገበት 2002 ወዲህ ለ18 ጊዜያት ተገናኝተዋል፡፡ ሲዳማ ቡና 7 ጨዋታዎች በማሸነፍ የበላነቱን ሲወስድ ኢትዮጵያ ቡና 6 ጊዜ አሸንፏል፡፡ በ5 አጋጣሚዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡ ሲዳማ ቡና 21 ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ 22 ግቦችን አስቆጥረዋል።

– በ2008 ይርጋለም ላይ 0-0 የተጠናቀቀው ጨዋታ በሁለቱ የእርስ በዕርስ ግንኙነት ታሪክ ብቸኛው ያለ ግብ የተጠናቀቀ ጨዋታ ነው፡፡

– ሲዳማ ቡና ሀዋሳ ላይ ካደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች ሦስቱን አሸንፎ በሁለቱ ነጥብ ተጋርቷል።

– ኢትዮጵያ ቡና እስካሁን በሦስት ጨዋታዎች ከሜዳው የወጣ ሲሆን አራት ነጥቦችን አሳክቶ ተመልሷል።

ዳኛ

– ኢንተርናሻል ዳኛ አማኑኤል ኃይለሥላሴ ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት ለመምራት ተመድቧል። አርቢትሩ በሦስት ጨዋታዎች አስራሁለት የቢጫ ካርዶች እና አንድ የፍፁም ቅጣት ምት ሰጥቷል። የፍፁም ቅጣት ምቱ የውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ ሲሆን በኢትዮጵያ ቡና እና ድሬዳዋ ከተማ የአንደኛ ሳምንት ጨዋታ ላይ የተሰጠ ነበር።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሲዳማ ቡና (4-3-3)

ፍቅሩ ወዴሳ

ሰንደይ ሙቱኩ – ፈቱዲን ጀማል – ሚሊዮን ሰለሞን – ግሩም አሰፋ

ዳዊት ተፈራ – ዮሴፍ ዮሃንስ – ወንድሜነህ ዓይናለም

ፀጋዬ ባልቻ – ሀብታሙ ገዛኸኝ – አዲስ ግደይ

ኢትዮጵያ ቡና (4-4-2 ዳይመንድ)

ዋቴንጋ ኢስማ

አህመድ ረሺድ – ተመስገን ካስትሮ – ክሪዝስቶም ንታምቢ – እያሱ ታምሩ

ዳንኤል ደምሴ

ካሉሻ አልሀሰን – ሳምሶን ጥላሁን

ሚኪያስ መኮንን

ሱለይማን ሎክዋ – አቡበከር ነስሩ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *