ሪፖርት | ቅዱስ ጊዮርጊስ በግብ ተንበሽብሾ ወደ ሠንጠረዡ አናት ተጠግቷል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አስረኛ ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ መከላከያን ገጥሞ 5-1 በማሸነፍ ወደ ሠንጠረዡ አናት ተጠግቷል።

መከላከያ በሳምንቱ አጋማሽ በኢትዮጵያ ዋንጫ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከረታበት ስብስቡ አማኑኤል ተሾመ እና በኃይሉ ግርማን በዳዊት እስጢፋኖስ እና ፍቃዱ ዓለሙ ምትክ በመጀመሪያ አሰላለፉ አካቶ ሲቀርብ የአምስት ተጫዋቾችን ለውጥ ያደረገው ቅዱስ ጊዮርጊስ በአንፃሩ ግብጠባቂ ለዓለም ብርሃን፣ ፍሬዘር ካሳ፣ አብዱልከሪም መሐመድ፣ አቡበከር ሳኒ እና አሜ መሐመድን በማሳረፍ ፓትሪክ ማታሲ፣ ሳላዲን በርጌቾ፣ ኄኖክ አዱኛ፣ ናትናኤል ዘለቀ እና ሳላዲን ሰዒድ ጨዋታውን አስጀምሯል።

የኢትዮጵያ ዋንጫ ሽንፈታቸው ቁጭት ውስጥ የከተታቸው የሚመስሉት ፈረሰኞቹ በፍፁም የማሸነፍ ፍላጎት ነበር የዛሬውን ጨዋታ የጀመሩት። ለአጥቂዎቹ ሳላዲን ሰዒድ እና ለጌታነህ ከበደ በሚጣሉ ኳሶች የመከላከያን የግብ ክልል ሲፈትሹ ቆይቶው ፈረሰኞቹ በ16ኛው ደቂቃ ከሳጥን ውጭ በግራ መስመር ለእጅ ውርወራው ለቀረበ መስመር አካባቢ የተሰጠውን ቅጣት ምት ለማሻማት በሚመስል መልኩ ሳላዲን ሰዒድ አክርሮ የመታው ኳስ ማንም ሳይነካው ግብ ጠባቂውን ይድነቃቸው ኪዳኔን በማለፍ የመጀመርያው ጎል ተቆጥሯል።

ተጭነው ሲጫወቱ የነበሩት ጊዮርጊሶች ከዚህ ጨዋታ ሙሉ ሦስት ነጥብ እንደፈለጉ በሚያሳይ ሁኔታ ያለ እረፍት በተደጋጋሚ ወደ ጎል በመድረስ ለመከላከያ ተከላካዮች ፈተና ሆኖባቸው ነበር። ከጎሉ መቆጠር ሁለት ደቂቃ በኋላም በኃይሉ አሰፋ በጥሩ ሁኔታ አሾልኮ ለአጥቂው ጌታነህ ከበደ የሰጠውን ኳስ አዙሮ መሬት ለመሬት አክርሮ ቢመታውም ለጥቂት በብረቱ ጠርዝ ወጥቶበታል። ብዙም ሳይቆይ በ25ኛው ደቂቃ ታደለ መንገሻ በግሩም ዕይታ ለጌታነህ ከበደ የጣለለት ኳስ የግብ ጠባቂው የይድነቃቸው ኪዳኔ መውጣትን ተከትሎ ጌታነህ በግንባሩ ጨርፎ የቅዱስ ጊዮርጊስን ጎል ወደ ሁለት ከፍ አድርጓል። ጎሏ ለጌታነህ ከበደ በቅዱስ ጊዮርጊስ ማልያ የመጀመርያው ጎል ሆና ተመዝግባለች።

በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ በጨዋታው እንቅስቃሴ የተዋጡት መከላከያዎች የቅዱስ ጊዮርጊስን ፈጣን እንቅስቃሴ ቆሞ ከመመልከት ውጭ ጀ ጨዋታው ሊመልሳቸው የሚችል እንቅስቃሴ ማድረግ አልቻሉም። ከጌታነህ ጎል ከሁለት ደቂቃ በኋላ ሙሉዓለም መስፍን ከማዕዘን የተሻገረን በተከላካዮች ተደርቦ እግሩ ላይ የገባችን ኳስ አክርሮ ቢመታበትም በዛሬው ጨዋታ ስራ የበዛበት የመከላከያው ግብጠባቂ ይድነቃቸው ኪዳኔ እንደምንም አውጥቶበታል። መከላከያዎች መሀል ሜዳ ላይ በተገደበ የኳስ ቅብብል ብቻ ወደፊት በማይሄደው አጨዋወታቸው ራሳቸውን ጫና ውስጥ እየከተቱ በሚነጠቁት ኳሶች የግብ ዕድል ሲፈጠርባቸው የተስተዋለ ሲሆን ለዚህ ማሳያ 32ኛው ደቂቃ ፈረሰኞቹ በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ጎል ደርሰው ሳላዲን ሰዒድ ለጌታነህ ከበደ አሳልፎለት ጌታነህ አስቆጠረ ሲባል አዲስ ተስፋዬን ለማለፍ ሲያስብ ረዝሞበት ነፃ አቋቋም ላይ ላለው ለታደለ መንገሻ አቀብሎት የግቡን መረብ ታካ የወጣችው ኳስ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ሦስተኛ ጎል ሆና ለመመዝገብ የተቃረበች አጋጣሚ ነበረች።

ከ30 ኛው ደቂቃ በኋላ መከላከያዎች በአንፃራዊነት ወደ ጎል መቅረብ የቻሉ ሲሆን ምንተስኖት ከበደ ከማዕዘን የተሻገረው ኳስ ተደርቦ ሲመጣ አክርሮ በመምታት የሞከረው የመከላከያ የመጀመርያው ለጎል የቀረበ ሙከራ ሆኗል። ብዙም ሳይቆይ በጨዋታው ለመከላከያ ብቸኛ ጎል ሆና የተመዘገበች አጋጣሚ 36ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት የተሻገረውን በኃይሉ አሰፋ ጨርፎ በራሱ ጎል ላይ የተቆጠረችው ሆናለች። ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር ይጥሩ የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች 41ኛው ደቂቃ ኄኖክ አዱኛ ከመሐል ሜዳ አርዝሞ የጣለለትን ሳላዲን ሰዒድ ኳሱን ወደፊት በመግፋት ከይድነቃቸው ኪዳኔ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ቺፕ አድርጎ ለማስቆጠር ሲሞክር ይድነቃቸው እንደምንም ጨርፎ ያወጣበት ሌላ ጎል መሆን የሚችል አጋጣሚ ሆኖ ነበር።

ከእረፍት መልስ መከላከያዎች የተጨዋች ለውጥ በማድረግ ተለውጠው የገቡ ቢመስልም ምንም የእንቅስቃሴ መሻሻል ያላሳዩ በአንፃሩ ጊዮርጊሶች ጨዋታውን ቶሎ ለመጨረስ በማሰብ ተጭነው መጫወታቸውን ቀጥለው በ54ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት የተሻገረውን ሳላዲን ሰዒድ በግንባሩ በግሩም ሁኔታ ገጭቶ የግቡ አግዳሚን ለትሞ ሲመለስ ሙሉዓለም መስፍን በደረቱ አብረዶ እና ተረጋግቶ በመከላከያ ተከላካዮች እግር ስር በማሾለክ ሦስተኛ ጎል ለቅዱስ ጊዮርጊስ አስቆጥሯል። ሙሉዓለም መስፍን ኳሷን በደረቱ አብርዶ አምስት ከሃምሳ ውስጥ ተረጋግቶ ጎል ሲያስቆጥር የመከላከያ ተከላካዮች ቆሞ ከመመልከት ውጭ የመከላከል ሚናቸውን በአግባቡ አለመወጣታቸው ምንያህል ቡድኑ በዛሬው ጨዋታ በመከላከሉ ረገድ ደካማ እንደነበር ማሳያ ነው።

ፈረሰኞቹ ተጨማሪ ጎል ፍለጋ በከፍተኛ ተነሳሽነት ቀጥለው 59ኛው ደቂቃ ሳላዲን ሰዒድ ከጌታነህ የተጣለለትን ኳስ ከይድነቃቸው ኪዳኔ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ቀለል አድርጎ ጎል አስቆጠረ ሲባል አክርሮ በመምታት ወደ ሰማይ የሰደዳት ኳስ የጊዮርጊስን የጎል መጠን ከፍ ማድረግ የሚችል አጋጣሚ ነበር። 65ኛው ደቂቃ ላይ ሳላዲን ሰዒድ በጥሩ ሁኔታ ያቀበለውን ተከላካይ ሰንጣቂ ኳስ ጌታነህ ከበደ በሚታወቅበት የአጨራረስ ብቃቱ ለቡድኑ አራተኛ ለራሱ ሁለተኛ ጎል ማስቆጠር ችሏል።

ከእረፍት መልስ መከላከያዎች ከክፍት የጨዋታ እንቅስቃሴ ግልፅ የማግባት አጋጣሚ መፍጠር የቻሉት ዘግየነው ነበር። በ80ኛው ደቂቃ መሐል ሜዳ ላይ የተሰጠውን ቅጣት ምት ጊዮርጊሶች በተዘናጉበት ቅፅበት ኳሱን አስጀምረው በቀኝ መስመር ዳዊት ማሞ ለአጥቂው ፍቃዱ ዓለሙ ቢያቀብለውም ጎል ለማስቆጠር ነፃ አቋቋም ላይ የነበረው ፍቃዱ ኳሷ በግሩ መሀል ሾልካ ያለፈችው የምታስቆጭ ብቸኛ ሙከራ ነበረች።

ወደ ጨዋታው መጠናቀቂያ ናትናኤል ዘለቀን ቀይሮ የገባውና ከተስፋ ቡድን ያደገው ሳሙኤል ተስፋዬ 85ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር ኳሱን እየገፋ በመሄድ መሬት ለመሬት አክሮ በመምታት ለፈረሰኞቹ አምስተኛ ለእርሱ ደግሞ በሊግ ጨዋታ በቅዱስ ጊዮርጊስ ማልያ የመጀመርያው ጎል አስቆጥሯል። ጨዋታው በቅዱስ ጊዮርጊስ ፍፁም የበላይነት 5-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። በውጤቱ መሰረት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ9 ጨዋታ ነጥቡን 15 በማድረስ ወደ ሦስተኛ ደረጃ ከፍ ሲል በሁለት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች 10 ጎሎችን ያስተናገደው መከላከያ 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *