የዲላው አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ በፌዴሬሽኑ እውቅና ተሰጣቸው

በከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ ዲላ ላይ በመጀመርያው ሳምንት ዲላ ከተማ ከ ወላይታ ሶዶ ከተማ ተጫውተው ያለ ጎል በተጠናቀቀው ጨዋታ በኢትዮጵያ እግርኳስ ባልተለመደ መልኩ በመሐል ዳኛው የፀደቀ ግብ በዲላው አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ጥቆማ አማካኝነት መሻሩ የሚታወስ ነው።

በጨዋታው 62ኛው ደቂቃ ላይ ዲላዎች በቀኝ በወላይታ ሶዶ የግብ ክልል ጠርዝ ላይ ካገኙት የቅጣት ምት የተሻማውን ኳስ የዲላ ከተማው የመሐል ተከላካይ ዝናው ዘላለም በግንባሩ ገጭቶ ወደ ግብ የላከውን ኳስ የዕለቱ ዳኛ አፈወርቅ አድማሱ ከረዳቱ ጋር በመነጋገር ግብ ነው በማለት አፅድቀዋል። ሆኖም ተጫዋቹ በግምባሩ የገጨው ኳስ ከመረብ ያረፈ ቢመስልም መረቡ የተቀደደ በመሆኑ ከጀርባ በኩል የመረቡን ማሰርያ ገመድ መትቶ ሾልኮ የገባ መሆኑን የግብ አስቆጣሪው ዲላ ከተማ አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ በማረጋገጣቸው ወደ አራተኛ ዳኛው አብርሃም ኮይራ በመጠጋት ኳሷ ግብ እንዳልሆነ ገልፀዋል። የእለቱ ኮሚሽነርም ዳኞቹን በመጥራት ካወያዩ በኃላ በስተመጨረሻም የአሰልጣኙን ጥቆማ በመቀበል ግቡ ተሽሮ በመልስ ምት እንዲቀጥል ተደርጎ ጨዋታውም 0-0 በሆነ ውጤት ተጠናቆ ነበር።

ይህ የአሰልጣኙ ተግባር በወቅቱ መነጋገርያ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽንም በዛሬው ዕለት ዲላ ከተማ ከ ነጌሌ አርሲ ባደረጉት የ8ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ላይ በመገኘት ለአሰልጣኙ በጎ ተግባር እውቅና ሰጥቷል። የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ጂራ፣ የከፍተኛ ሊግ ዋና ሰብሳቢ ኢብራሂም አህመድ፣ የከፍተኛ ሊግ ውድድር ኃላፊ ጌታቸው አበበ፣ የደቡብ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፅህፈት ቤት ኃላፊ ወልደሚካኤል መስቀሌ፣ የከተማው ከንቲባ ትግሉ በቀለ፣ የዞኑ አስተዳዳሪ ገዙ አሰፋ እና ሌሎች እንግዶች በተገኙበት ከዛሬው ጨዋታ መጀመር በፊት የምስጋና ሽልማት ተከናውኗል። ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ንግግር ካደረጉ በኋላ ሽልማቱን ለአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ያበረከቱ ሲሆን የዲላ ስፖርት ቤተሰብም ላሳየው ስፖርታዊ ጨዋነት ምስጋና አቅርበዋል። በመቀጠል የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ገዙ አሰፋ የምስጋና ንግግር በማድረግ ለአሰልጣኙ እና ለተጫዋቹ የአምስት ሺ ብር ሽልማት አበርክተዋል።

አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ከሽልማቱ በኋላ ባደረጉት ንግግር እግርኳስ ፍትሀዊነት እንደሚፈልግ ገልፀዋል። “እግር ኳስ ፍትሀዊነትን ይፈልጋል። እኔም ይህን ነው ያደረኩት። ታዲያ እኛ ለምን እንክዳለን? ሲቀጥል ደግሞ ነገ ይህ ጉዳይ እኔ ላይ ቢከሰትና ብንሸነፍስ ብዬ ማሰብ መቻል አለብኝ። የዲላ ህዝብ ፍትሐዊ እግር ኳስን ፈላጊ ነው። እኔም በዲላ ኳስን ስጫወት ማሸነፍ የሚቻለው በፍትሐዊ መንገድ ነው የሚለው በውስጤ ስላለ ያደረኩት ነው። ተጫዋቾቼም ይህን እንዲያምኑ ነው የምሰራው። የኢትዮጽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ይህን የምስጋና ሽልማት ማድረጉ ለኔ ትልቅ ደስታ ፈጥሮብኛል። እኔ ያደረኩት እግር ኳስ የሚፈልገውን ነው። ይህን ተመልክቶ ፌዴሬሽኑ እዚህ ድረስ በመምጣቱ ደስታ ተሰምቶኛል።”

በመቀጠል ንግግር ያደረጉት ኢሳይያስ ጂራ “በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ይህ ነገር እንደተፈጠረ ስሰማ የእውነት በጣም ነው የደነቀኝ። እውነትም አሁንም እግርኳሳችንን ለማሳደግ የቆሙ እና እየለፉ ያሉ ሰዎች እንዳሉ በግልፅ የሚሳይ ነው። ዓለም ላይ እግር ኳስ የሚታወቅበት ትልቁ ምልክት የሰላም ተምሳሌት መሆን መቻሉ ነው። የዲላ ዋና አሰልጣኝ የተገበሩት ይህን ነው። ከዚህ ጋር አብሮ መመስገን ያለበት የዲላ አመራር እና ደጋፊ ነው። ለእውነት እንደቆሙ ያሳያል። ዛሬ ላይ የኢትዮጽያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዲላ ላይ ተገኝቶ ይህንን ማድረግ የፈለገው እግር ኳሱን በእውነት ለሚመሩት አካላቶች ምስጋና ያሻቸዋል የሚል ፅኑ እምነት ስላለን ጭምር ነው። ፌዴሬሽኑ በስፖርታዊ ጨዋነት ላይ አጥብቆ እየሰራ ይገኛል፤ ይህንን ስራ ማሳካት የምንችለው ደግሞ እንደዚህ አይነት ድርጊት የሚፈፅም ማህብረስብ ማግኘት ስንችል ነው። አሰልጣኝ ገብረክርስቶስም በድርጊታቸው ቡድናቸው ሁለት ነጥብ ቢያጣም ትልቅ ክብር የሚያስገኝ ተግባር ፈፅመዋል። ለዚህም ተግባራቸው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምስጋናውን ዛሬ ላይ በዲላ ከተማ ተገኝቶ ማስተላለፍ ችሏል። የዲላ ከተማ ደጋፊ ይህን ጨዋነቱን ለቀጣይ ጊዚያት በተግባር በማሳየት እንዲቆይ ስል መልዕክቴን አስተላልፋለሁ፤” ብለዋል።

ዛሬ ከስነ-ስርዓቱ በኋላ በዲላ ከተማ እና ነጌሌ አርሲ መካከል የተደረገው ጨዋታ በእንግዳው ቡድን 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *