-ሶስት ተጨማሪ ተጫዋቾች ከአዲስ አበባው ፍልሚያ ውጪ ሆነዋል
በ2018ቱ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የኢትዮጵያ አቻውን የሚገጥመው የኮንጎ ብሔራዊ ቡድን ወሳኝ ተጫዋቾች ባጋጠማቸው ጉዳት ከደርሶ መልሱ ጨዋታ ውጪ ሆነዋል። ለፈረንሳዩ አንጀርስ የሚጫወተው እና በመስከረም ወር በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያው ጊኒ ቢሳው ላይ አራት ግቦችን ማስቆጠር የቻለው ፍሬቦሪ ዶሬ ባጋጠመው የእግር ስብራት አስቀድሞ በጨዋታው እንደማይሰለፍ የታወቀ ሲሆን አሠልጣኝ ክላውድ ሌሮይ ጥሪ ካደረጉላቸው 21 ተጫዋቾች 3ቱን በጉዳት እንዳጡ የሚወጡ መረጃዎች ጠቁመዋል።
በፈረንሳይ ሊግ 1 ለሬሚስ የሚጫወተው ፕሪንስ ኦኒያንጉዌ ትከሻው ላይ ባጋጠመው ጉዳት ምክንያት ከብሔራዊ ቡድኑ የተገለለ ሲሆን የአንጀርሱ ተከላካይ አርኖልድ ቡካ ሞውቱ በብሽሽት ጉዳት ጨዋታው እንደሚያመልጠው ተነግሯል። ወሳኙ አጥቂ ቲዬቪ ቢፎውማም በቁርጭምጭሚት ጉዳት ከክላውድ ሌሮይ ስብስብ ውጪ ሆኗል።
የላ ሊጋው ክለብ ኢስፓኞል ንብረት የሆነው እና በውሰት ለግራናዳ እየተጫወተ የሚገኘው ቲዬቪ ቢፎውማ ክለቡ በላሊጋው በራዮ ቫዬካኖ 3-1 በተሸነፈበት ጨዋታ ቁርጭምጭሚቱ ላይ መጠነኛ ጉዳት ያጋጠመው በመሆኑ አዲስ አበባ ላይ ለሚደረገው የመጀመሪያ ጨዋታ እንደማይደርስ እውን ሆኗል። ተጫዋቹ ከጉዳቱ በፍጥነት ማገገም ከቻለ ግን ለብራዛቪሉ የመልስ ጨዋታ የሚሰለፍ ይሆናል። ቢፎውማ ለፈረንሳይ ወጣት ቡድኖች የተጫወተ ሲሆን በ2014 ለኮንጎ መጫወት ከወሰነ በኋላ በተሰለፈባቸው 14 ጨዋታዎች 8 ግቦች ማስቆጠር የቻለ ወሳኝ አጥቂ ነው።
ኮንጎ ዋሊያዎቹን የፊታችን ቅዳሜ አዲስ አበባ ላይ የምትገጥም ሲሆን የመልሱን ጨዋታ ደግሞ ከ3 ቀን በኋላ በብራዛቪል ታስተናግዳለች።
ፎቶ – ቲዬቪ ቢፎውማ
© Soccer Ethiopia