– የምድብ ጨዋታዎች በአዲስ አበባ፣ ባህርዳር እና ሐዋሳ ስታዲየሞች ይደረጋሉ
ከህዳር 11 እስከ 26 ድረስ በኢትዮጵያ አዘጋጅነት የሚደረገው የ2015ቱ የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ዋንጫ የምድብ ድልድል ዛሬ ናይሮቢ በሚገኘው የሴካፋ ዋና መስሪያ ቤት ወጥቷል። ውድድሩ በ11 የሴካፋ አባል ሃገራት መሀል የሚደረግ ሲሆን የማላዊ ብሔራዊ ቡድን በተጋባዥነት ይሳተፋል።
በተለያዩ የሚድያ አካላት ከዚህ በፊት የተዘገበው የምድብ ድልድል የተዛባ እንደሆነ እና ውድድሩም ዛሬ የወጣውን መርሃ-ግብር ተከትሎ እንደሚካሄድ ኬንያዊው የሴካፋ ዋና ፀሃፊ ኒኮላስ ሙሶንዬ አስታውቀዋል። ዋና ፀሃፊው አክለውም በርካታ የአፍሪካ ሃገራት በውድድሩ የመሳተፍ ፍላጎት እንደነበራቸው የገለፁ ሲሆን በይፋ ጥያቄ ያቀረበው ግን የማላዊ ፌዴሬሽን ብቻ እንደነበር ተናግረዋል።
ውድድሩ ቅዳሜ ህዳር 11 ብሩንዲ ከዛንዚባር በአዲስ አበባ ስታዲየም በሚያደርጉት ጨዋታ የሚጀመር ሲሆን በዕለቱ አስተናጋጅ ሃገር ኢትዮጵያ ከሩዋንዳ ጋር የመጀመሪያ ጨዋታዋን ታደርጋለች። ከሰኞ ህዳር 13 ጀምሮ የሚደረጉ የምድብ ጨዋታዎች በሙሉ በባህርዳር እና ሐዋሳ ስታዲየሞች የሚደረጉ ይሆናል።
በ2013 ውድድሩን አዘጋጅታ ዋንጫውን ያነሳችው ኬንያ የወቅቱ የሴካፋ ሻምፒዮን ነች። ዩጋንዳ ውድድሩን 13 ጊዜ በማሸነፍ የምትመራ ሲሆን ኬንያ በ5 ዋንጫ፣ ኢትዮጵያ ደግሞ 4 ጊዜ ሻምፒዮን በመሆን ይከተላሉ።
የምድብ ድልድሉ ይህንን ይመስላል
ምድብ 1 – ኢትዮጵያ – ሩዋንዳ – ታንዛንያ – ሶማልያ
ምድብ 2 – ኬንያ – ዩጋንዳ – ቡሩንዲ – ዛንዚባር
ምድብ 3 – ሱዳን – ማላዊ – ደቡብ ሱዳን – ጅቡቲ