ከፍተኛ ሊግ ለ | ወልቂጤ ከተማ የምድቡን መሪነት አጠናክሯል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ዘጠነኛ ሳምንት የምድብ ለ ጨዋታዎች እሁድ ሲከናወኑ ወልቂጤ ከተማ፣ ኢትዮጽያ መድን፣ ነገሌ አርሲ፣ ናሽናል ሴሜንት እና ወላይታ ሶዶ አሸንፈው ሶስት ነጥብ ማግኘት ችለዋል። ሀላባ ከተማ በሰፊ ጎል ሲሸነፍ የዲላ መጥፎ የውድድር ዘመን ጉዞም ቀጥሏል።

አዲስ አበባ ከተማ 1-1 ኢኮስኮ

(በዳንኤል መስፍን)

አሜድላ ሜዳ ረፋድ 4:00 ላይ በተደረገው በዚህ ጨዋታ በመጀመርያው የጎል ሙከራ ነበር አዲስ አበባዎች የጎል ማስቆጠር የቻሉት። በ6ኛው ደቂቃ ከመስመር የተሻገረውን ኳስ ሳዲቅ ሴቾ አጥብቆ ቢመታውም ግብ ጠባቂው አስግድ ታምሬ ሲመልሰው ኢብሳ በፍቃዱ አግኝቶ አዲስ አበባዎችን መሪ ማድረግ ቻለ። ጎሉ ከመቆጠሩ በፊት አዲስ አበባዎች በተሻለ መንቀሳቀስ ቢችሉም ጎሉን ካስቆጠሩ በኋላ እየተቀዛቀዙ መጥተው በኢኮስኮዎች ብልጫ እንዲወሰድባቸው ሆኗል። 

በዳኝነቱ በኩል ተጫዋቾች አላስፈላጊ አጨዋወት እንዲጫወቱ መፍቀዳቸው የጨዋታውን ውበት ሲቀንሰውም ተስተውሏል። ኢኮስኮዎች ጎል ለማስቆጠር ከአዲስ አበባዎች በተሻለ ሁኔታ ጫና በፈጠሩበት አጋጣሚ የቀድሞ የፋሲል ከነማ ተስፈኛ አጥቂ የነበረው ሄኖክ አወቀ ኢኮስኮን አቻ የምታደርግ ጎል በ21ኛው ደቂቃ አስቆጥሯል። በተደጋጋሚ ዳኛው የሚሰሩት ስህተት ጨዋታው እየተቆራረጠ አሰልቺ ሆኖ ቀጥሎ 34ኛው ደቂቃ ኢኮስኮዎች ግልፅ አጋጣሚ አግኝተው ሄኖክ አወቀ ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። 

ከእረፍት መልስ የረባ እንቅስቃሴም ሆነ የጎል ሙከራዎች በቅጡ ያልተመለከትንበት ሲሆን ያልተመጠኑ ኳሶች በሁለቱም ቡድኖች በኩል ወደ ፊት እየተጣሉ መድረሻቸው ሳይታወቅ ይባክኑ ነበር። ከጨዋታው እንቅስቃሴ ይልቅ  የዕለቱ ዳኛ የሚሰሩትን ስህተት ተከትሎ ተጫዋቾች ዳኛውን በመክበብ ያደርጉት የነበረው ወከባ የጨዋታው አንድ አካል ይመስል ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ግልፅ የሆነ የግብ ዕድል መፍጠር የቻሉት አንድ አንድ ጊዜ ብቻ ነው። 75ኛው ደቂቃ አዲስ አበባዎች ከሳጥን ውጭ የተሰጠው ቅጣት ምት ምንያምር ዼጥሮስ መትቶት የግቡ አግዳሚ የመለሰበት፤ እንዲሁም 83ኛው ደቂቃ በኢኮስኮ በኩል ጊዮን መላኩ ከማዕዘን የተሻማውን በግራ እግሩ አጠንክሮ በጥሩ ሁኔታ መትቶ ለጥቂት ወደ ውጭ የወጣበት ተጠቃሽ የጎል ሙከራዎች ሆነው አልፈዋል። ጨዋታውም በዚሁ ውጤት 1 -1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

ወልቂጤ ከተማ 1-0 ሀምበሪቾ

(በአምሀ ተስፋዬ)

ወልቂጤ ላይ በ9:00 የተደረገው ጨዋታ ከመጀመሩ በፊት የወልቂጤ ቡድን አመራሮች ከዚህ ተጫዋቻቸው ለነበረው አሁን ላይ በሀምበሪቾ ለሚጫወተው ሚካኤል ወልደሩፋኤል ስጦታ ያበረከቱ ሲሆን በኢትዮጽያ ብሔራዊ መዝሙር ነበር ጨዋታው የተጀመረው።

ከፍተኛ ጥንቃቄ የተሞላበት እንዲሁም የአየር ላይ ኳሶች የበዛበት በነበረው ጨዋታ በ2ኛው ደቂቃ አህመድ ሁሴን ባደረገው የግብ ሙከራ የጀመሩት ወልቂጤዎች ጎል ማስቆጠር የቻሉትም ገና በጊዜ ነበር። በ6ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት ብስራት ገበየሁ ወደግብ ያሻማውን ኳስ አህመድ ሁሴን በግንባሩ በመግጨት ወደግብነት ለውጦታል። በግቡ ይበልጥ የተነቃቁት ወልቂጤዎች በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ቶሎ ቶሎ በመድረስ ጫና ሲፍጥሩ ተስተውሏል። በ15ኛው ደቂቃ አህመድ ሁሴን በድጋሚ በግንባሩ በመግጨት የግቡ አግዳሚ ታካ የወጣችበት አጋጣሚ ሌላው ተጠቃሽ ሙከራ ነበር።

ከግቡ መቆጠር በኋላ በቀላሉ መረጋጋት ያልቻሉት ሀምበሪቾዎች ረዘም ላለ ደቂቃ ወደፊት በመጓዝ አደጋ መፍጠር ሳይችሉ የቀሩ ሲሆን በ32ኛው እና 37ኛው ደቂቃዎች ላይ ፈጣኑ አጥቂ ዘካርያስ ፍቅሬ በግንባሩ በመግጨት የሞከራቸው እንዲሁም በ41ኛው ደቂቃ ላይ መቆያ አልታየ ሞክሮ ወደ ውጪ የወጣበት ኳስ ተጠቃሽ ናቸው። በወልቂጤ በኩልም በ27ኛው ደቂቃ ከመሀል ክፍል በረጅሙ የተሻገረረትን ኳስ አህመድ ሁሴን ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ በግቡ አናት ሲወጣበት 34ኛው ደቂቃ የሀምበሪቾ ግብ ጠባቂ ኳስ ለመያዝ ቀድሞ ሲወጣ የወልቂጤው ቀኝ ተከታካይ ቀድሞ ደርሶ በመቀማት ያሻገረው ኳስ በተከላካዮች ርብርብ ተመልሷል። የመስመር ላይ ኳሶችን መጫወት ምርጫው ያደረገው ባለሜዳው ቡድን በ45ኛው ደቂቃም በተመሳሳይ አጋጣሚ ተመስገን ደረሰ ያገኘው እድል ልዩነቱን ማስፋት የሚችልበት ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ተመጣጣኝ እና የሚቆራረጥ እንቅስቃሴ አሳይተዋል። ሀምበሪቾዎች ከገቡበት አለመረጋጋት በመውጣት የኋላ ክፍላቸውን ሲያጠናክሩ በጨውታ እንቅስቃሴም ተሽለው ነበር። ዘካሪያስ ፍቅሬ በ51ኛው ደቂቃ አክርሮ የመታው ኳስ በግቡ አናት የሂደችበት አጋጣሚ በሀምበሪቾ በኩል የሁለተኛው አጋማሽ ተጠቃሽ ሙከራ ነበረች። ከዚህች ሙከራ በኋላ ተጨማሪ የጎል አጋጣሚዎችን ለመመልከት ረጅም ጊዜ የወሰደ ሲሆን በ84ኛው ደቂቃ ሀምበሪቾ አቻ ሊያደርገው የሚችለውን እድል አግኝተው ነበር፤ ሚካኤል ወልደሩፋኤል ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ የመለሰበት እንዲሁም የተመለሰውን ኳስ ወንድሜነህ አክርሮ ቢመታውም ቤሊንጋ አድኖበታል። ጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ የወልቂጤው አጥቂ አህመድ ሁሴን 5:50 ውስጥ ላይ የተገኘውን የግብ አጋጣሚ ሳይጠቀምበት ቀርቶ ጨውታው በወልቂጤ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። በዛሬው ጨዋታ ላይ የወልቂጤ ደጋፊ ማኅበር በስፖርታዊ ጨዋነት ዙሪያ በስታዲየሙ በሞንታርቦ የታገዘ ትምህርት ሲሰጥም ተስተውሏል።

ሌሎች ጨዋታዎች

(በአምሀ ተስፋዬ)

መድን ሜዳ ላይ ኢትዮጽያ መድን ከዲላ ያደረገውን ጨዋታ 3-0 በማሸነፍ ወልቂጤን መከተሉን ቀጥሏል። 17ኛው ደቂቃ ላይ በሂደር ሙስጣፋ አማካይነት በተቆጠረ ግብ መሪ ሆነው ወደ እረፍት ያመሩ ሲሆን አብዱለጢፍ ሙራድ በ65ኛው ደቂቃ እንዲሁም ሳሙኤል በለጠ በተጨማሪ ደቂቃ ላይ ባገቡት ግቦች 3-0 ማሸነፍ ችለዋል።

አርሲ ነገሌ ላይ ነገሌ አርሲ ከድሬዳዋ ፖሊስ ያደረጉት ጨዋታ አብዲሳ ጀማል በ76ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ጎል በባለሜዳው አሸናፊነት ተጠናቋል። በዘንድሮ ዓመት ያደገው ነገሌ አርሴ የምድቡ ክስተት መሆኑንም ቀጥሏል።

ኦሜድላ ሜዳ ላይ በ9:00 የካ ክፍለ ከተማ ከናሽናል ሲሚንት ባደረጉት ጨዋታ እንግዳው ቡድን ናሽናል 3-1 ማሸነፍ ችሏል። በመጀመሪያው አጋማሽ በተቆጠሩት ግቦች በተጠናቀቀው ጨዋታ በግብ ቀዳሚ መሆን የቻሉት ናሽናሎች ነበሩ። በ15ኛው ደቂቃ ላይ አድነው ተመስገን አስቆጥረው መሪ መሆን ሲችሉ የካዎች ንጉስ ጌታሁን በ25ኛው ደቂቃ አቻ አድርጓቸዋል። አቤል ግርማ በ32ኛው እንዲሁም ኤርሚያስ ቴወዎድሮስ በ38ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠሯቸው ጎሎች ለናሽናል ከሜዳ ውጪ ድልን አስጨብጠዋል።

በሌላ የምድቡ ጨዋታ ሶዶ ላይ ወላይታ ሶዶ ሀላባን ባልተጠበቀ መልኩ 4-0 በሆነ በሰፊ ጎል ማሸነፍ ችሏል። ለወላይታ ሶዶ ዳግም ማቴዋስ በ26ኛው እና በ37ኛው ደቂቃ ሁለት ጎሎችን ሲያስቆጥር ፉዓድ አህመድ በ54 ደቂቃ በፍፁም ቅጣት ምት እንዲሁም በ75ኛው ደቂቃ ብሩክ አማኑኤል ቀሪዎቹን ጎሎች ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *