አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ብሔራዊ ቡድኑን ለማጠናከር እንቅስቃሴ ስለመጀመራቸው ይናገራሉ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ በቀጣይ ለብሔራዊ ቡድኑ ግብዓት የሚሆኑ ስራዎችን ለመስራት ማሰባቸውን በተለይ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ በ2019 በግብፅ በሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ በተደረጉ የማጣርያ ጨዋታዎች ላይ ውጤታማ ያልሆነ ጉዞዋን ያጠናቀቀች ሲሆን በቀጣይ የኦሊምፒክ አንደኛ ዙር የማጣርያ ጨዋታዎች በመጋቢት ወር ከማሊ ጋር ይጠብቃታል። በዓመቱ መጨረሻ ደግሞ የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ጉዞዋን ትጀምራለች። ለቀጣይ ውድድሮች የሚሆን ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን ለመፍጠር እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ የገለፁት አሰልጣኝ አብርሀም በቅርቡ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ተዘጋጅቶ በነበረው የኤሽያ ዋንጫ ላይ በቀድሞው ቡድናቸው የመን ብሔራዊ ቡድን ጋባዥነት ጨዋታዎችን ተመልክተው ወደ ሀገር ውስጥ የተመለሱ ሲሆን በቅርቡ ወደ አውሮፓ ሀገራት እንደሚያመሩ ይናገራሉ። 

“በቅርቡ ለሁለት ጉዳዮች ከሀገር ውጪ ለመጓዝ ማረጋገጫውን እየጠበኩ ነው። አንደኛው የምሄድበት ምክንያት በውጪ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾችን ለኦሊምፒክ እና ለዋናው ብሔራዊ ቡድን በሚሆን መልኩ አይቶ መመልመል ነው። በጣሊያን፣ ሲዊድን፣ እንግሊዝ እና የመሳሰሉት ሀገራት በመሄድ ለብሔራዊ ቡድን የሚሆኑትን መምረጥ ነው። ይህን የማደርገው በራሴ ነው። ይህ ደግሞ ሀገር ውስጥ ያሉ ተጫዋቾችን ያነቃቃል።” ያሉት አሰልጣኝ አብርሀም አክለውም በውጪ ሀገር ስላሉት ተጫዋቾች የሚመጡበትን ቅደም ተከተል በዚህ መልኩ አብራርተዋል።

” አፍሪካ ዋንጫ ውስጥ ገባን አልገባን አይደለም ቁም ነገሩ። ለለውጥ የተለየን ነገር መስራት ይኖርብናል። እስካሁን የሀገር ውስጥ ተጫዋቾችን ተመልክተናል። መጀመሪያ በሰጠሁት ጋዜጣዊ መግለጫ መሠረት የሀገር ውስጥን ካየን በኋላ ወደ ውጪው ዞር ብለን እናያለን ብለን ነበር። የውጪዎቹን ደግሞ ወደዚህ እያመጣን ማባከን አንፈልግም። አስራ አምስት ተጫዋች የትኬት፣ የቪዛ፣ የሆቴል እና ሌሎች  ወጪ አውጥቶ ከማምጣት እኔ ሄጄ ባያቸው እና ጥራት ያላቸውን ብመርጥ ይሻላል ከሚል አንፃር ነው። ሌሎች ያደጉ ሀገሮችም የሚያደርጉት እንደዚህ ነው። የሚጠቅመን ከሆነ ግን ጥቅሙ ለሀገር ስለሆነ ወጪያቸው ተሸፍኖ እናመጣለን።” 

አሰልጣኝ አብርሀም የልምድ ልውውጥ ወደ አውሮፓ የሚያቀኑበት ሁለተኛ ምክንያት ገልፀዋል። ለዚህም ጉዟቸውን ወደ እንደግሊዝ ማድረግን መርጠዋል። “ሁለተኛ የምሄድበት ጉዳይ ደግሞ ከእንግሊዝ እግር ኳስ ማኅበር የቴክኒክ ባለሙያዎች ጋር ልምድ ልውውጥ ለማድረግ ነው። ከነሱ ጋር በነበረኝ ግንኙነት አማካኝነት ባቀረብኩት ጥያቄ የተገኘ ዕድል ነው። ኢትዮጵያ ልምድ ከሚያስፈልጋቸው ሀገሮች አንዷ ናት። ለምሳሌ የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ጋሬዝ ሳውዝጌት የመረጠው አጨዋወት እና እየተከተለ ያለው የተጫዋች ምርጫ ላይ ከነ ጓርዲዮላ እና ላውድሩፕ ጋር ያለው ግንኙነት ምን ያህል ጠቅሞታል የሚለውን ለማየት ነው። ለንደን ላይ በተገናኘንበት ወቅት ልምድ ለመለዋወጥ ዝግጁ እንደሆነ ነግሮኝ ስለነበር እሱን መሠረት አድርገን ነው የምጓዘው።” ብለዋል።

ወደ ብሔራዊ ቡድኑ አዳዲስ ተጫዋቾችን ለማምጣት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እና የከፍተኛ ሊግ ጨዋታዎችን ከረዳቶቻቸው ሙሉጌታ ምህረት፣ ፋሲል ተካልኝ እና ውብሸት ደሳለኝ ጋር በመሆን በተለያዩ ከተሞች በመዟዟር እየተመለከቱ እንደሆነ የገለፁት አሰልጣኝ አብርሀም ከአውሮፓ ጉዟቸው በተጨማሪ ከቀድሞ የብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች እና የፕሪምየር ሊግ አሰልጣኞች ጋር ለመወያየት ማቀዳቸውን ገልፀዋል።

“ነገ ወይም ከነገ ወዲያ አንድ ስብሰባ አለኝ። ከአሜሪካ፣ እንግሊዝ እና ከሚኖሩበት ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ ለእረፍት የመጡ የቀድሞው የብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች አሉ። በየጊዜው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ውጤት ያሳስበናል፤ ይቆጨናል ይላሉ። ሁሉንም ባይሆን የተወሰኑትን ጠርቼ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጠንካራ እና ደካማ ጎን ምንድን ነው ብዬ ላወያያቸው ነው። ያለፉበትም ስለሆነ ፊት ለፊት እንነጋገራለን። እነሱ ምን ማድረግ እንዳለብን ሊነግሩን ይችላሉ። ከነሱ የምናገኘው ግብረ-መልስ ብሔራዊ ቡድናችንን ያጠነክራል። ከነሱ በመቀጠል ደግሞ የፕሪምየር ሊግ አሰልጣኞችን በመጥራት እንወያያለን። ይሄ ደግሞ መለመድ አለበት። ያኔ እግር ኳሱ እየጠራ እና እያደገ እያደገ የሚመጣው” ሲሉ ሀሳባቸውን አጠቃለዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *