አንዳንድ ነጥቦች በመቐለ 70 እንደርታ እና መከላከያ ጨዋታ ዙርያ

ቅዳሜ ከተደረጉት ጨዋታዎች አንዱ የነበረውና በመቐለ 5-2 አሸናፊነት በተጠናቀቀው ጨዋታ ዙርያ የሚከተሉትን ሶስት ነጥቦች ለማንሳት ወደናል።

በጨዋታው መቐለዎች ባለፉት ሶስት በሜዳቸው  ያደረጓቸው ጨዋታዎች የተጠቁሙበትን 4-4-2 (መሃሉ ጠባብ) ሲጠቀሙ እንግዶቹ መከላከያዎች ደግሞ በመጀመርያው አጋማሽ 4-2-3-1 መርጠው ወደ ሜዳ ሲገቡ ሁለተኛው አጋማሽ ወደ ተለመደው 4-4-2 ድያመንድ ተመልሰዋል። በመጀመርያው አጋማሽ ከተፈጥሯዊ ቦታው በተለየ ከሶስቱ አማካዮች በአንዱ ጠርዝ የተሰለፈው ተመስገን ገብረፃዲቅ በመጀመርያ አጋማሽ የነበረው አማካይ የመጫወቻ ቦታ (Average position) ከብቸኛ አጥቂው ምንይሉ ወንድሙ ቅርብ ቦታ ላይ ነበር።

በጨዋታው በርካታ ትኩረት የሚስቡ ታክቲካዊ ጉዳዮች ቢኖሩም መከላከያዎች በሁለቱ አጋማሾች የነበራቸው አቀራረብ፤ የአማኑኤል ገ/ሚካኤል እና የያሬድ ከበደ ጥምረት እንዲሁም የመከላከያ የመከላከል አደረጃጀትን በዋነኝነት በመምረጥ በአጭሩ ተመልክቻቸዋለሁ።

፨ የመከላከያ የጨዋታ አቀራረብ 

በጨዋታው 4-2-3-1 መርጠው ወደ ሜዳ የገቡት መከላከያዎች በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ፍፁም ብልጫ ቢኖራቸውም ጨዋታውን በተቆጣጠሩባቸው ደቂቃዎች የፈጠሯቸው የግብ ዕድሎች ሁለት ብቻ ነበሩ። በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ወደ መቐለ ሳጥን በዝተው በመጠጋት በማያቋርጥ እንቅስቃሴ ባለሜዳውን ቡድን መጫን ችለው የነበሩት መከላከያዎች እንቅስቃሴያቸው የመቐለን ተከላካዮች ከኳስ ምስረታ ( build-up ) ያገደ እና ለቀጥተኛ ኳስ ያስገደደ ነበር። ሆኖም እንቅስቃሴው ከመጀመርያዎቹ ሃያ ደቂቃዎች ያለፈ አልነበረም።

ግብ ካስተናገዱ በኋላ በተገላቢጦች በተጋጣሚ ቡድን ጫና ውስጥ የገቡት መከላከያዎች በቴክኒኩ ረገድ የላቁ የአማካይ ክፍል ተጫዋቾች ቢይዙም ጨዋታውን መቆጣጠር አልቻሉም፤ በጨዋታው ቶሎ ማንሰራራት የቻሉት መቐለዎች የተቃራኒ ቡድን አማካዮች ከኳስ ጋር በቂ ጊዜ እና ቦታ እንዳያገኙ ጫና በመፍጠሩ ረገድ የተሻሉ ነበሩ።

ሌላው በመከላከያ በኩል የሚጠቀሰው ድክመት በብዛት የኳስ አቅጣጫን ተከትሎ እና አጥቦ ሲከላከል የነበረውን ተጋጣሚ ቡድን በተቃራኒ አቅጣጫ የሚፈጥረውን ክፍተት ለመጠቀም አንድም ጊዜ ካሱን ከአንዱ አቅጣጫ ወደ አንዱ አቅጣጫ ቀይረው ለማጥቃት የሞከሩበት አጋጣሚ አልነበረም (በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ ) ።

የመጀመርያው አጋማሽ ጨዋታው በጀመረበት ቅኝት መቀጠል ያልቻሉት መከላከያዎች ምንም እንኳ ቡድኑ እንደ ቡድን ጥሩ ባይሆኑም የመቐለን የመስመር አጨዋወት ለመመከት የተከሉት አጨዋወት ጥሩ ነበር፤ በዚህ ምክንያትም መቐለዎች በመጀመርያው አጋማሽ የተለመደው እና ለተጋጣሚ ቡድን ፈታኝ የሆነው ፈጣን የመስመር ሽግግራቸው ማሳካት የቻሉባቸው አጋጣሚዎች ጥቂት ነበሩ። ከዚ ውጭ መከላከያዎች በሁለቱም የሜዳ ክፍሎች የነበራቸው መመጣጠን ሌላው ጥሩ ጎን ነው ፤ ቡድኑ ከሜዳ ውጭ እንደመጫወቱ አፈግፍጎ ለመጫወት የፈለገበት ሁኔታም አልነበረም።

በሁለተኛው አጋማሽ አማኑኤል ተሾመ በዳዊት ማሞ ተክተው ወደተለመደው 4-4-2 ድያመንድ የተመለሱት መከላከያዎች በተወሰነ መልኩ ማሻሻያዎች ቢያሳዩም ፎርሜሽኑን በመተግበር ደረጃ ብዙ ስህተቶች ተስተውሎባቸዋል። አጨዋወቱ በመሃል ሜዳ ላይ ወደ ጎን ወደ መስመሩ ተለጥጦ ለመጫወት የሚፈቅድ ባለመሆኑ በሁለቱም አማካዮቹ የጎንዮሽ ያለው ሰፊ ቦታ በመስመር ተከላካዮች እንዲሸፈን የግድ ይላል፤ ይህ ካልሆነ ግን ያንን ሰፊ ቦታ ለተጋጣሚ ቡድን ጥቅም ነው የሚውለው። በዚህ ጨዋታ የሆነውም ይህንኑ ነው፤ ምንም እንኳ ባለሜዳው መቐለ ይህንን ቦታ ከመጠቀም ይልቅ ከተከላካይ ጀርባ በሚጣሉ ረጃጅም ኳሶች ለማጥቃት ቢሞክርም። በባለሜዳው ቡድን በሁለቱም መስመር የተሰጠውን ሰፊ ቦታ ለመጠቀም የተደረገ ጥረት እምብዛም አልነበረም።

ሌላው መከላከያዎች  ከማጥቃት ወደ መከላከል ሲያደርጉት የነበረው ሽግግር ቶሎ ወደ መከላከል ቅርፃቸው የመያዝ ችግር ይስተዋልባቸው ነበር።

፨ የአማኑኤል እና የያሬድ ጥምረት

በጨዋታው በመቐለዎች በኩል ከነበሩት ጠንካራ ጎኖች አንዱ የነዚህ ሁለት ተጫዋቾች ጥምረት ነው። ያለፉትን ሶስት ዓመታት በተከታታይ የመቐለን የአጥቂ ክፍል የመሩት እነዚህ ተጫዋቾች በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ የነበራቸው ተግባቦት እጅግ ጥሩ ነበር።

በገብረመድኅን ኃይሌ አጨዋወት የቡድኑ ዋነኛ የማጥቃት መሳርያ የሆኑት እነዚህ ሁለት ተጫዋቾች ከኳስ ውጭ ያላቸው እንቅስቃሴ እና ከተከላካይ ጀርባ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ለተጋጣሚ ቡድን ፈታኝ ነበር። በጨዋታው አማኑኤል አራት ግብ ሲያስቆጥር ያሬድ ደሞ አንድ ግብ አግብቶ ለሁለት ፍፁም ቅጣት ምት መገኘት ምክንያት ነበር።

፨ የመከላከያ የመከላከል አደረጃጀት 

በሁለተኛው አጋማሽ ከታዩት ትኩረት ሳቢ ጉዳዮች አንዱ መከላከያዎች የተከላካይ ክፍላቸው በእጅጉ ወደ መሃል ሜዳ አስጠግተው መጫወታቸው ነው። መከላከያዎች አጨዋወቱን መምረጣቸው ምንም የማያጠያይቅ ጥሩ ጎን ቢሆንም አተገባበሩ ላይ የታዩት ጉልህ ስህተቶች ግን የጨዋታውን መልክ የቀየረ ነበር።

አሰልጣኝ ስዩም ከበደ ከጨዋታው በኋላ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር በነበራቸው አጭር ቆይታ እንደገለፁት እየተመሩ የተከላካይ ክፍላቸውን ለግብ ጠባቂያቸው አስጠግተው ቢጫወቱ ጨዋታውን ለመቆጣጠር እንደሚቸገሩ እና በአማካይ እና አጥቂ ክፍል ያለውን ክፍተት ለመመጠን ይህን ማድረግ እንዳስፈለገ የገለፁበት መንገድ ትክክል ቢሆንም የተጋጣሚን ቡድን ብቃት እና የራሳቸው ተከላካዮችን ፍጥነት ከግምት ያስገባ አልነበረም።

የመከላከያ ሁለቱ የመሃል ተከላካዮች ከጀርባቸው ያለው ቦታ ለመሸፈን የነበራቸው ንቃት እና አካል ብቃት ከተጋጣሚ አጥቂዎች ፍጥነት ጋር ሲተያይ በእጅጉ ደካማ ነበር። ከዚህ ውጭ መከላከያዎች ተከላካይ ክፍላቸው ወደ መሃል ሜዳ አስጠግተው ( high-line) ለመከላከል የሚመርጡ ቡድኖች አብዛኛው ጊዜ የሚተገብሩትን ግብ ጠባቂን ከተከላካይ ጀርባ ያለው ቦታ እየወጣ የመሸፈን (swipper-kepper) ማድረግም አልቻሉም።

መቐለዎችም ከላይ የተጠቀሱት ስህተቶችን ተጠቅመው በቁጥር በርካታ ዕድሎች ፈጥረዋል። በተለይም አማኑኤል ገብረሚካኤል ያስቆጠራት ግብ እና በይድነቃቸው ኪዳኔ ድንቅ ብቃት ጎል ከመሆን የተረፈችው ኳስ በዛ መንገድ የመጡ ነበሩ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *