ሚካኤል አርዓያ ከዳኝነት ሙያ ራሱን አገለለ


በሚወስናቸው ውሳኔዎች እንዲሁም በተለያዩ እግርኳሳዊ ስብሰባዎች ላይ ፊት ለፊት በግልፅ በሚያደርጋቸው ንግግሮቹ የስፖርት ቤተሰቡ ትኩረት ሆኖ የቆየው ፌዴራል ዳኛ ሚካኤል አርዓያ ራሱን ከዳኝነት ሙያ ማግለሉን ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግሯል።

በኢትዮጵያ እግርኳስ ፈታኙ ሙያ በሆነው ዳኝነት ላይ ከ20 ዓመት በላይ መቆየት ችሏል። በሜዳ ላይ በሚወስዳቸው አወዛጋቢ ውሳኔዎች እንዲሁም በሚያሳያቸው አካላዊ እንቅስቃሴዎቹ አንዳንዴ ፈገግታን ይጭራሉ። በኢትዮጵያ ዳኞች ማኅበር ውስጥ በምክትል ሰብሳቢነት በሰራበት ዓመታት የኢትዮጵያ ዳኝነት ሙያ እንዲከበር በመታገል ትልቅ አስተዋፆኦም ማበርከት ችሏል። በተለይ በተለያዩ የእግርኳስ ስብሰባዎች ላይ በግልፅ ችግሮች እንዲታረሙ አስተያየት በመስጠት እና ፈገግ በሚያደርጉ ንግግሮቹ ይታወቃል። ተጫዋቾች ከቡድን አመራሮች እንዲሁም ከደጋፊዎች ጋር አይረሴ የሆኑ 20 ዓመታትን አሳልፏል።

ኢንተርናሽናል ዳኛ የመሆን ከፍተኛ ፍላጎት ቢኖረውም ይህን ማሳካት ባለመቻሉ ይቆጭ እንጂ በዳኝነት ሙያው ደስተኛ መሆኑን የሚናገረው ፌደራል ዳኛ ሚካኤል አርዓያ ራሱን ከዳኝነት ሙያ በክብር ማግለሉን ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግሯል። “ከ20 ዓመት በላይ በዚህ ሙያ አገልግያለው። ሁልግዜ በዳኝነቱ አትቀጥልም፤ የሆነ ጊዜ ላይ ማቆምህ አይቀርም። በዳኝነት በቆየሁባቸው ያለፉት ዓመታት በጣም ደስተኛ ነኝ። በእነዚህ ሁሉ ዓመታት አንድ ቀን ሳልቀጣ፤ ክለቦች፣ ተጫዋቾች እና ደጋፊዎች አክብረውኝ እኔም ህጉን ተከትዬ ያለ ምንም ሀሜት አገልግያለው። አሁን ራሴን ከዳኝነት አገለልኩ እንጂ ከሙያው አልርቅም። ነገ ኮሚሽነር ሆኜ በሙያዬ እግርኳሱን በቅንነት አገለግላለው። በዳኝነት ዘመኔ እንደነበረኝ ጉዞ ሁሉ በሀቅነት፣ በግልፅ እና እውነትን ይዤ እሰራለው። እስከዛሬ በነበረኝ ቆይታ ደስተኛ ነኝ። እዚህ ለመድረሴ ብዙ አስተዋፆኦ ያደረጉልኝ አባቶቼ ባለሙያዎችን አመሰግናለው። ተጫዋቾች፣ ባለሙያዎች፣ ደጋፊዎች እና ሚዲያውን አመሰግናለው። ባልሰደብ እና ባልተች ኖሮ ራሴን እያስተካከልኩ አልሄድም ነበር። በአጠቃላይ ከሁሉም ዘንድ ጥሩ ፍቅር አግኝቼበታለው። በዳኝነት ዘመኔ ቀረ ብዬ የምለው ነገር ባይኖርም ኢንተርናሽናል ዳኛ ደረጃ መድረስ ህልሜ አለመሳከሰቱ ትንሽ ያስከፋኛል። ያው ፈጣሪ የፈቀደው ነው የሚሆነው። በአጠቃላይ ደስተኛ ሆኜ ነው ዳኝነትን ያቆምኩት። ” ብሏል።

ከፌደራል ዳኛ ሚኬኤል አርአያ ጋር አስገራሚ የሆኑ የዳኝነት ጉዞዎቹ ፣ ፈገግ የሚያደርጉ ገጠመኞቹ እና ሌሎች ዘርዘር ያሉ ቆይታዎቹን በቀጣይ ይዘን የምንቀርብ መሆኑን ከወዲሁ መግለፅ እንወዳለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *