ደቡብ ፖሊስ አዲስ ዋና አሰልጣኝ ሾመ

ደካማ የውድድር ዓመት አጀማመር ያሳየው እና ከቀናት በፊት ዋና አሰልጣኙን ከኃላፊነት ያነሳው ደቡብ ፖሊስ ከዲላ ከተማ ጋር የተለያዩት አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራን በዋና አሰልጣኝነት ቀጠረ፡፡

የ2010 የከፍተኛ ሊግ ቻምፒዮን በመሆን ከስምንት ዓመታት በኋላ ወደ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዳግም ያደገው ደቡብ ፖሊስ ለዚህ ተሳትፎው እንዲበቃ ካደረጉት አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ ጋር በመለያየት የቀድሞው አሰልጣኙን ዘላለም ሺፈራውን በአንድ ዓመት የውል ኮንትራት ቢያመጣም ከውጤት ማጣት ጋር ተያይዞ በስምምነት ከተለያየ በኃላ የቀድሞውን የክለቡ ተጫዋች አላዛር መለሰን እስከውድድር ዓመቱ መጨረሻ ድረስ በጊዜያዊ ዋና አሰልጣኝነት መቅጠሩ ይታወሳል። አላዛር ቡድኑን እየመራ ባደረገው የመጀመርያ ጨዋታው ከሜዳው ውጪ ኢትዮጵያ ቡናን 2-1 በመርታት መልካም አጀማመር ቢያደርግም ቆይታው ሳይዘልቅ ወደ ረዳት አሰልጣኝነት ዝቅ በማለት በሌላ አሰልጣኝ ተተክቷል፡፡ አዲሱ አሰልጣኝ በዲላ ከተማ ረዘም ያለ ቆይታ የነበራቸው አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ናቸው።

አሰልጣኙ በቅርቡ የከፍተኛ ሊግ ጅማሮ ዲላ ከተማ በሜዳው ከ ሶዶ ከተማ ባደረጉት ጨዋታ በዳኛው አማካኝነት በስህተት የፀደቀችውን ግብ እንዲሻር ጥቆማ በመስጠታቸው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ሽልማት በወሩ መጀመርያ ሽልማት የተበረከተላቸው ሲሆን ይህ ተግባራቸውም አድናቆት አስገኝቶላቸዋል። ሆኖም ዲላ ከተማ ዘንድሮ እያስመዘገበ በሚገኘው ደካማ ውጤት ምክንያት ተቃውሞዎችም በመበርታታቸው ከክለቡ ከቀናት በፊት ከተለያዩ በኃላ ነው ወደ ደቡብ ፖሊስ በአንድ ዓመት የውል ስምምነት ያመሩት፡፡ አሰልጣኙ ከነገ ጀምሮ ወደ ልምምድ የሚገቡ ሲሆን ቀሪውን የአንደኛ ዙር የመጨረሻ ጨዋታ በአላዛር ከተመራ በኋላ ሁለተኛውን ዙር በአዲሱ አሰልጣኝ የሚቀጥል ይሆናል። ካለበት ደረጃ የተሻለን ነገር ይዞ እንዲያጠናቅቅ እንደሚሰሩም አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡

አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ከ1970ዎቹ አንስቶ በተለይ በዲላ ከተማ የተጫዋችነት ዘመናቸውን ያሳለፉ ሲሆን ለደቡብ ክልል እንዲሁም በቀድሞ አጠራር ለሲዳማ ክፍል ሀገር በአማካይ ስፍራ ላይ በአምበልነትም ጭምር የእግር ኳስ ህይወትን አሳልፈዋል። ከ90ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ ደግሞ ወደ አሰልጣኝነት ሙያ ውስጥ በመግባት በተለይ በታዳጊዎች ላይ በመስራት የጀመሩት አሰልጣኙ  ለረጅም አመታት ከአንደኛ ሊግ አንስቶ እስከ አሁኑ የከፍተኛ ሊግ ውድድር ድረስ በዲላ ከተማ የዋና አሰልጣኝነት ቦታ ላይ ነበሩ፡፡ በመሐል ለአንድ ዓመት ካልመሩበት ውጪም በርካታውን የአሰልጣኝነት ህይወታቸውን በዚሁ የትውልድ ቦታቸው ክለብ አሳልፈዋል። የቅዱስ ጊዮርጊሶቹ ጌታነህ ከበደ እና አስቻለው ታመነን እንዲሁም ሌሎች ስመ-ጥር ተጫዋቾችን ለኢትዮጵያ እግር ኳስም አበርክተዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *