ሶከር መፅሀፍት | ኢንቨርቲንግ ዘ ፒራሚድ (ምዕራፍ ሶስት – ክፍል 4)

በእንግሊዛዊው የእግርኳስ ጸኃፊ ጆናታን ዊልሰን ደራሲነት በ2008 ለንባብ የበቃው Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics ን በሶከር ኢትዮጵያ በተከታታይ ክፍሎች እያቀረብንላችሁ እንገኛለን፡፡ በዛሬው መሠናዶም የምዕራፍ ሦስትን 4ኛ ክፍል እነሆ ብለናል፡፡

|| ያለፈውን ሳምንት ለማንበብ ይህን ይጫኑ LINK

ኸርበርት ቻፕማን (ካለፈው ሳምንት የቀጠለ…)

በኸርበርት ቻፕማኑ አርሰናል አንደኛው ለሌላኛው የተነሳሽነት እገዛ እያደረገ ድል መቋደስና እና ዘመናዊ ገጽታን መላበስ ተደጋጋፊ ሆነው ዘለቁ፡፡ ከመሰረቱ የወግ አጥባቂነት ባህሪ የተጠናወተው የሀገሪቱ እግርኳስ ማኅበር በተጫዋቾች መለያ ላይ ቁጥሮችን ለማስፈር እንዲሁም በትልልቅ የፓውዛ መብራቶች በመታገዝ ጨዋታዎችን በምሽት ለማከናወን የሚደረጉ ጥረቶችን አገደ፡፡ ሆኖም ግን ሌሎች ለእግርኳሱ መዘመን ጉልህ ድርሻ የሚኖራቸው የፈጠራ ግንኝቶች ጥቅም ላይ እንዲውሉ ተደረገ፡፡ የመድፈኞቹ ጥቁር ጋምባሌ በነጭና ሰማያዊ ቀለም ተተካ፤ በሃይብሪ ስታዲየም ውስጥ ግዙፍ የሰዓት መቁጠሪያ ምሰሶ ተተከለ፤ በጊሌስፒ ጎዳና የሚገኘው የምድር ውስጥ-ለውስጥ ባቡር ጣቢያ በክለቡ መጠሪያ እንዲሰየም ተወሰነ፤ ሙሉ በሙሉ ቀይ የነበረው የክለቡ መለያም ከርቀት በቀላሉ ሊለይ እንዲችል ታስቦ ነጭ እጅጌ ተሰፋለት፡፡

ምናልባትም ከሁሉ የሚገርመው የሚከተለው ሳይሆን አይቀርም፦ በየሳምንቱ ዓርብ ከሚካሄደው የልምምድ መርሐ-ግብር በኋላ ቻፕማን ተጫዋቾቹን በማግኔት በሚሰራ የታክቲክ ማስተማሪያ ሰሌዳ (Magnetic Tactic Board) ዙሪያ ይሰበስባል፤ ካለፈው ጨዋታ ጋር የተያያዙ ህጸጾችን እየነቀሰ ያወጣል፤ ከቀጣዩ ተጋጣሚ አንጻር እርማት ለሚሹ ጉዳዮችም መፍትሄ ያበጃል፤ ተጫዋቾቹ እስከሚረዱት ድረስም ሳይታክት ማብራሪያ ይሰጣል፡፡ በሃደርስፊልድ ሳለ ተጫዋቾች በሜዳ ላይ ለሚጠበቅባቸው ተገቢ የቦታ አያያዝ የራሳቸውን ሃላፊነት እንዲወስዱ በማበረታታት ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ በአርሰናል ደግሞ በየሳምንቱ የሚካሄድ፣ በረቂቅና ዝርዝር ታክቲካዊ አጀንዳዎች ላይ የሚያተኩር ውይይትና ጠለቅ ያለ ትንታኔ እንዲለመድ አደረገ፡፡ በወቅቱ <ዴይሊ ሜይል> ጋዜጣ ላይ የወጣ አንድ ጽሁፍ ” ያረጀና ያፈጀውን ተለምዷዊ ባህል ወደ ጎን ትቶ ለጨዋታዎች የማሸነፊያ ቀመር በመቅረጽ ረገድ  ቀዳሚው አሰልጣኝ ነው፡፡” ሲል አስነበበ፡፡

የአሰልጣኙ ትጋት መና አልቀረም፤ ልፋቱ ፍሬ አፈርቶ አርሰናሎች በ1931 እና 1933 የሊጉን ዋንጫ አሸነፉ፡፡ በ1932 ደግሞ በእግርኳስ ማኅበሩ ዋንጫ ፍጻሜ ደርሰው ከፍተኛ ውዝግብ የፈጠረ አከራካሪ ግብ ተቆጥሮባቸው ተረቱ፡፡ የዚያን ጊዜውን የክለቡ ዘላቂ ብቃት በማስመልከት ብሪያን ግላንቪል “ለማሽን የቀረበ ስልነት የተጎናጸፉ!” ሲል አወድሷቸዋል፡፡ ከመከላከል ወደ ማጥቃት በሚያደርጉት ፈጣን ሽግግር እና ወጥ በሆነው የአጨዋወት ዘይቤያቸው ላይ በሃይብሪ ስታዲየም ዙሪያ የተሰራው የ1920ዎቹና የ1930ዎቹ ታዋቂ የኪነ ህንጻ ንድፍ አስደማሚ ውበት ይታይ ነበር፡፡ የስዊዝ-ፈረንሳዊ ጥምር ዜግነት ባለቤት፣ ስመጥር የህንጻ ንድፍ ጥበበኛ፣ ሰዓሊና ጸሃፊ የነበረው ለ-ኮቡዚዬን ‘ ቤት- ሰዎች ለመኖሪያነት የሚገለገሉበት ማሽን ነው፡፡’ የሚለውን ትርጓሜ እንደ ማጣቀሻ ከወሰድን እጅግ በዘመነው እግርኳስ ‘ማሽን’ የሚለው ቃል አውዳዊ ፍቺ የተለየ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

በተመሳሳይ ዝነኛው ፖርቶሪኮ-አሜሪካዊ ገጣሚና የህክምና ባለሙያ ዊሊያም ካርሎስ ዊሊያምስ በኪነጥበብ ውስጥ ሰርፆ የነበረው ዘመናዊ አስተሳሰብ ላይ የታዘበውን  ሲያወጋ ‘ማሽን’ የሚለውን ቃል የመፈክር ያህል እንደተጠቀመ እንረዳለን፡፡ ለአብነት ያህልም ግጥም ምን ማለት እንደሆነ ለማብራራት ይህንኑ ቃል አጭር ትንታኔ ለመስጠት መርጦታል፡፡ “ግጥም እንደ ሌሎች ማሽኖች አስፈላጊ ያልሆኑ ትርፍ ክፍሎች ላይኖሩት የሚችል ከቃላት የሚገነባ ማሽን ነው፡፡” የቻፕማን አርሰናል ደግሞ ዘመኑን አመላካች መስታወት ነበር፡፡ ጆይ ስለ አጨዋወት ስልታቸው ሲናገር ” ሃያኛው መቶ ክፍለ-ዘመን ላይ ነበርን፤ እጥር-ምጥን ያሉ ቅብብሎችን ያካተተ፣ ቀልብን ሰቅዞ የሚይዝ፣ ውብ፣ የተጫዋቾችን ጉልበት የሚቆጥብ እንዲሁም ተጋጣሚዎችን ድባቅ የሚመታ አቀራረብ ተገበርን፡፡” ይላል፡፡

ምናልባት ይህ እግርኳሳዊ ልህቀት ብዙ የሚያስገርም ላይሆን ይችላል፡፡ ምንም ይሁን ምን ቻፕማን ከ1870ው የፎርስተር <ትምህርት ለሁሉም!> መርህ የመጀመሪያዎቹ ተጠቃሚዎች መሃል መገኘት ችሏል፡፡ በወቅቱ ይህ አዋጅ በእንግሊዝ እና ዌልስ የሚገኙ እድሜያቸው ከአምስት ዓመት እስከ አስራ ሁለት ዓመት የደረሱ  ህፃናት የትምህርት ገበታቸው ላይ እንዲገኙ ያስገድድ ነበር፡፡ በዚህ መሰረት ከአርባ ዓመታት በኋላ እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸው የሰራተኛው መደብ አባላት በአንደኛው የዓለም ጦርነት መጀመር ምክንያት የተፈጠረውን የአስተዳደራዊ ስራ ክፍት ቦታዎች ለመሙላት አስችሏል፡፡ በእርግጥ በእነዚህ የኃላፊነት ስፍራ የተሰጣቸው ሰዎች ዘንድ የታዋቂው አሜሪካዊ ባለቅኔና ሃያሲ እዝራ ፖንድ “አዲስ አድርገው!” አይነት አዕምሮዓዊ ትዕዛዝ በጆሮአቸው አያቃጭል፤ በጭንቅላታቸው አይመላለስ ይሆናል፡፡ ሆኖም በባህላዊ አሰራር ተሸብበው ከቆዩት ቀደምት ትውልዶች በላቀ እነዚህ የአመራር ክፍሎች ለፈጠራና አዳዲስ ግኝቶች ይበልጥ በራቸውን ክፍት የማድረግ አዝማሚያ አሳይተዋል፡፡ ቻፕማንም ከኖቲንግሃምሻየር ማዕድን ማከማቻ አካባቢ የተገኘውን ዘመናዊና ባለ ምጡቅ አዕምሮ ደራሲ ዴቪድ ኸርበርት ላውረንስን ያስታውሰናል፡፡

በቻፕማን የእግርኳስ አጨዋወት ዘይቤ  ጥርጣሬ ከገባቸው ሰዎች መካከል ምናልባትም ከሁሉ በተሻለ ብልህ የነበረው ካሩዘርስ ከ1933 የውድድር ዘመን ማብቂያ በኋላ በ<ዴይሊ ሜይል> ጋዜጣ ላይ የግል አስተያየቱን ሰጠ፡፡ “ሌሎች ክለቦች የአርሰናልን የጨዋታ ስልት ለመኮረጅ ከተለሙ እኔ እንደማስበው ተምሳሌት አድርገው የሚነሱበት ቡድን እድለኛ አያደርጋቸውም፡፡ አሁን ያለው አንድ አርሰናል ብቻ ነው፤ ሌላ ለማሰብ እቸገራለሁ፡፡ የትኛውም ቡድን በዚህ ዘይቤ ለመጫወት የሚችሉና ተመሳሳይ አስተሳሰብን የሚያራምዱ ተጫዋቾች የሉትም፡፡” አለ፡፡

በእርግጥ የቻፕማንን አጨዋወት መሰረታዊ ሐሳብ ባልተሟላ ሁኔታም ቢሆን ተጫዋቾች ተረድተውታል፡፡ ይህ መጠነኛ ግንዛቤ በ1931 እንግሊዝ በወዳጅነት ጨዋታ ስኮትላንድን ለመግጠም ስትዘጋጅ የሃገሪቱ ብሄራዊ ቡድን ቴክኒክ ኮሚቴ ሮበርትስን ሲመርጥ ገሃድ ወጣ፡፡ ተጫዋቹ ለሃገሩ የተጠራ የመጀመሪያው ብቸኛ የመሃል ተከላካይ ሲሆን ሁለቱ የመስመር ተከላካዮች ፍሬድ ጉዳልና ኧርኒ ብሌንኪሶፕ ግን ለW-M ፎርሜሽን እንግዳ ነበሩ፡፡ በዚህም ምክንያት “ስኮትላንዳውያኑ በሜዳው ላይ የተፈጠሩት ክፍተቶች ተመችቷቸው በጥሩ ብቃት 2-0 አሸነፉ!” ሲል ሌቪ ማኒንግ በ<ዴይሊ ስኬች> ጋዜጣ ላይ በሰራው ዘገባ የእንግሊዞችን ታክቲካዊ ድክመት አጋለጠ፡፡

በስኮትላንድ የጨዋታ ዘይቤን በሚመለከት የሚነሱ አስተያየቶች በሁለት ጎራዎች የተከፈሉ ነበሩ፡፡ አንደኛው “ይበልጥ ዘመናዊ የሆነው አቀራረብ በተሻለ ውጤታማ ያደርጋል፡፡” የሚል ይዘት ሲኖረው ሁለተኛው ደግሞ በ<ቅብብሎች ላይ የተመሰረተውን እግርኳስ የሙጥኝ ያለው ክፍል> ነበር፡፡ እንደ ሽመና ንድፍ በአጭሩ ተቆላልፈው የሚደረጉ ቅብብሎች ላይ ያመዘነው አጨዋወት ለመጨረሻ ጊዜ አስደናቂ ሆኖ የታየው መጋቢት 31-1928 ሁሌም <የዌምብሌይ ምትሃተኞች> ተብለው ሲታወሱ የሚኖሩትን ተጫዋቾች ያካተተውን ስብስብ የያዘው የስኮትላንድ ቡድን በአሌክስ ጃክሰን-ሶስት እና አሌክስ ጄምስ-ሁለት ግቦች ታግዞ እንግሊዞችን 5-1 ሲያሸንፍ ነበር፡፡ <ኢቭኒንግ ኒውስ> በተሰኘ ጋዜጣ ላይ የድህረ ጨዋታ ዘገባ ያቀረበው ሳንዲ አዳምሰን የጃክሰንን የመጀመሪያ ጎል ” ባለተሰጥዖ ተጫዋቾች ብቻ በተካኑት ዘዴ፣ እጅጉን በሰለጠነና ጠመዝማዛ በሆነ ቴክኒካዊ ስልት ተጋጣሚውን እያለፈ ያስቆጠራት ግብ በአይነቷ ለየት ያለች እንደሆነች ለመጪው ትውልድ ልናትት ይገባናል!” ሲል አወደሳት፡፡ ” የአይጥና ድመት መሯሯጥ በሚመስለው ጨዋታ እንግዶቹ ፈነጠዙ፡፡ ኳሱ ከስኮትላንዳውያኑ ተጫዋቾች እግር-እግር በፍጥነት ይንሸራሸራል፤ እንግሊዛውያኑ ደግሞ በተረበሸ መንፈስ ውስጥ ሆነው ግራ ተጋቡ፤ ረዘም ላሉ ደቂቃዎች እንዲሁ እንደተደነጋገሩ በሜዳቸው በሰፊ የጎል ልዩነት ተሸነፉ፡፡ የሚገርመው የስኮትላንዶቹ ተጫዋቾች ጥልፍልፍ ባለው ተከታታይ የመቀባባል ዘይቤያቸው (Weaving-Pattern) ታግዘው በሚያደርጉት አንዲት ንጥል የማጥቃት ቅጽበት ውስጥ እንግሊዞቹ ኳሱን ሳይነኩ እነርሱ ግን ቢያንስ አስራ አንድ የተሳኩ ቅብብሎችን ያደርጉ ነበር፡፡ እንዲያውም በአንድ አጋጣሚ በዚሁ የማጥቃት  እንቅስቃሴ የመጣን ኳስ የስኮትላንዱ አጥቂ ቲም ደን ከግቡ አግዳሚ በላይ አርቆ በመስደድ አምክኖታል፡፡” ሲልም እንግዶቹ ላሳዩት የጨዋታ አቀራረብ ሙገሳውን ቸረ፡፡

<ግላስኮው ሄራልድ> የተሰኘው ጋዜጣ  በጨዋታው ዙሪያ በሰራው ዘገባ ” የእንግዳው ቡድን ስኬት በቀላሉ ከሚተገበረው፣ ማራኪነቱ እምብዛም ከሆነውና ፍጥነትን መሰረታዊ ግብዓት አድርጎ ከሚቃኘው የእንግሊዞች እግርኳስ ስልት ይልቅ ክህሎት፣ ሳይንስና ቴክኒካዊ ተሰጥዖ ላይ ያተኮረው የስኮትላንዳውያኑ አጨዋወት ዘዴ አሁንም ቢሆን በሃገሪቱ ውስጥ በብዛት ተስፋፍቶ እንዳለ ዋነኛ ማሳያ ነው፡፡” ሲል ለዘብ ያለ ትዝብቱን አሰፈረ፡፡ በረግረጋማው ሜዳ የመስመር አማካዮቹ ጂሚ ጊብሰንና ጂሚ ማኩላን እንዲሁም ሁለቱ ከመስመር የሚነሱ አጥቂዎች ደንና ጄምስ የባላንጣን አቅም የሚያስከነዳ አስገራሚ ጥምረት አሳዩ፡፡ በእርግጥ ጨዋታው የተካሄደው በአለም ዓቀፍ የቤት ውስጥ ሻምፒዮና ሲሆን በጥሎ ማለፍ መልክ የሚከናወን እና ከተለያዩ የእንጨት አይነቶች ተቀርጾ የሚሰራ ማንኪያ መሳይ የዋንጫ ሽልማት ያለው ብዙም ትኩረት የማይቸረው ውድድር ላይ ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ በቶርናመንቱ  የስኮትላንዳውያኑ የአጨዋወት ስልት አዋጭነት ረዘም ያለ ርቀት አልተጓዘም፤ በሰሜን አየርላንድ 1-0 ሽንፈት እና በዌልስ 2-2 አቻ ውጤት ተገታ፡፡

ከስኮትላንድ ብሄራዊ ቡድን አስራ አንድ የመጀመሪያ ተሰላፊዎች መካከል ስምንቱ በእንግሊዝ መጫወታቸው ዋጋው ላቅ ያለ ነበር፡፡ ተጫዋቾቹ ቀድሞም ቢሆን የተሳኩ ቅብብሎችን የማድረግ ችሎታቸው እንዳለ ሆኖ የእንግሊዝ እግርኳስ ተጠቃሽ አዎንታዊ ጎን የሆነውን ከፍተኛ ፍጥነት እንዲላበሱ አግዟቸዋል፡፡ ሁኔታው ከአጨዋወት ዘይቤ አንጻር ሲቃኝ ጥቂቶች እንደሚሉት ኋላ-ቀር ተብሎ የሚደመደም አይደለም፡፡ በጨዋታው የመሃል ተከላካይ-አማካዩ ቶም ብራድሾው የመከላከል ሚና ተሰጠው፤ዲክሲ ዲንን እየተከታተለ በቁጥጥሩ ስር እንዲያውለውም ታዘዘ፡፡ ብራድሾው ይህን ኃላፊነት ሲወጣ አጠቃላይ የቡድኑ መዋቅራዊ ስርዓት (System) ሙሉበሙሉ የW-M ፎርሜሽንን የማይከተል አቀራረብ ይይዛል፤ ከመደበኛው 2-3-5 ትግበራም የራቀ ቅርጽ ይኖረው ነበር፡፡

በክለቦች ጨዋታ ላይ የW-M ፎርሜሽን ተደራሽነት ወጥ አልነበረም፡፡ የቀድሞው የሬንጀርስ ተጫዋች ጆርጅ ብራውን በ1930ዎቹ ገደማ በሬንጀርስ-ሴልቲክ ምርጥ አስራ አንድ እና በኸርትስ-ዊብስ ምርጥ አስራ አንድ ስብስቦች መካከል የተደረገውን የእርዳታ ገቢ ማሰባሰቢያ ግጥሚያ ያስታውሳል፡፡ ” በጨዋታው ዴቭ ሜይክጆን የቀኝ መስመር አማካይ ሆነ፤ እኔ ለግራ መስመር አማካይነቱ ተመረጥኩ፤ የሴልቲኩ ጂሚ ማክስቴይ ደግሞ የመሃል ተከላካይ አማካይነት ሚና ተሰጠው፡፡ በዚህ ሁኔታ እየተጫወትን በመጀመሪያው አጋማሽ ነገሮች በመልካም ሁኔታ አልሄድልን አሉ፤ 1-0 እየተመራንም እረፍት ወጣን፡፡ በመልበሻ ክፍል ውስጥ ሜይክጆን ማክስቴይን አወያየው፤ ‘ አንተ ወደ ፊት ገፍተህ በመጫወትህ የተነሳ ቡድናችን በአብዛኛው ጥቃት እየደረሰበት የሚገኘው በመሃለኛው የሜዳ ክፍል ነው፡፡ ከኋላ በጄሚ ሲምፕሰን አማካኝነት ጥሩ ከተንቀሳቀስን የመስመር ተከላካዮቻችን ይበልጥ ነጻ ይሆናሉ፡፡’ አለው፡፡ ማክስቴይም ይህን ዘዴ ለመሞከር ያለማቅማማት ተስማማ፤ እኛም በቀላሉ አሸናፊ ሆነን ወጣን፡፡ ከዚያ በኋላ ማክስቴይ ለሴልቲክ በዚያ ሚና መጫወቱን ቀጠለ፡፡ እንደ አርሰናሉ ጃክ በትለር ሁሉ ማክስቴይም ተፈጥሮአዊ ተከላካይ አልነበረም፡፡ ስለዚህ ሴልቲኮች በዚህ ተነሳስተው ቆሞ የሚከላከለውን (Stopper) ዊሊ ሊዮን ከኩዊንስ ፓርክ ካስፈረሙ በኋላ ዘጠኝ አመታት ያለ ድል ያደረጉት ጉዞ ተገታ፡፡

ይሁን እንጂ የሴልቲክ ውጤታማ ውሳኔ ስር የሰደደ የታክቲክ አስተሳሰብ ችግር ይዞ ከተፍ አለ፡፡ ጥሩ የማጥቃት ተጫዋች ከመሆን በተሻለ መከላከል ላይ የሚያተኩር የበቃ የመሃል-ተከላካይ አማካይ መሆን ይቀላል፡፡ በቻፕማን አማካኝነት የተጠናው እና ፈጠራ ላይ የሚያተኩረውን ቀመር በሌሎች ቡድኖች ዘንድ  ተግባራዊ ለማድረግ አዳጋች ሆነ፡፡ በቀላሉ የማይረበሽና የተረጋጋው ኸርቢ ሮበርትስ አይነቶቹ ተከላካዮች በብዛት ቢገኙም ከመሃል አጥቂ ግራና ቀኝ የሚጫወቱት ሌሎቹ የፊት መስመር አጥቂዎች (Inside-Forwards) ሚና የያዘውን አሌክስ ጄምስ ችሎታ የታደሉ ተመሳሳይ ተጫዋቾች እንደሚፈለገው ለማግኘት አስቸጋሪ ሆነ፡፡ ጂሚ ሆጋን ሲመሰክርም ” ሌሎች ክለቦች የቻፕማንን ዘዴ በቀጥታ ሊተገብሩ ሻቱ፤ ሆኖም ግን ብቁ ተጫዋቾችን አልያዙም ነበር፡፡ እንደኔ ድርጊቱ የእንግሊዝን እግርኳስ ከማውደም የዘለለ ፋይዳ አላሳየም፡፡ ውጤቱም መከላከል ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጠው፣ ረጅምና ጠንካራ ቅብብሎችም እውቅና እንዲያገኙ ከማድረግ አልፎ ተራማጅነትና ዝመና የሚታይበት አጨዋወትን ያስቀረ ሆነ፡፡ በዚህ አይነቱ መንገድ ተጫዋቾቻችን ኳሱን የመቆጣጠር፣ የመያዝና እግራቸው ስር የማቆየት ፍላጎት አጡ፡፡” አለ፡፡

በእርግጥ የዚህ ውድቀት ጥንስስ ችግሮች የ<ጨዋታ ውጭ> ህግ ከመቀየሩ በፊት የጀመሩ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ቻፕማን ለለውጡ ተግባራዊ ምላሽ መስጠት ሲጀምር በትኩረት የመታየት አጋጣሚ አገኙ፡፡ ግላንቪል እንደገለጸው “ሶስተኛውን ተከላካይ በማካተት የሚደረገው ጨዋታ ቀደም ሲል በእግርኳስ አቀራረብ ይታይ የነበረውን ድክመት የሚያጠናክርና የሚያባብስ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በአሰልጣኞች እና ተጫዋቾች ዘንድ አዕምሯዊ ስንፍናን ያሰርጻል፡፡” በእውነቱ አዲስ ስልት ለመፍጠር ከመታገል ይልቅ በቀጥታ ለፊት መስመር ተሰላፊዎች በረጅሙ የሚጠለዙ ቅብብሎች ላይ ክችች ማለት ያን ያህል ከባድ አይሆንም፡፡ ቻፕማን በተለመደው አቋሙ እንደጸና ቆየ፡፡ ” ዘወትር በሌሎች ክለቦች እየተኮረጀ የሚገኘው የእኛ አጨዋወት ስርዓት ለትችት የተጋለጠ ሆኗል፡፡ አልፎአልፎ ለውይይት የሚበቃበት ሁኔታም አለ፡፡” ሲል ለሁጎ ሜይዝል ቅሬታውን አወያየው፡፡ ” ሜዳ ላይ ያለው አንድ ኳስ ብቻ ነው፡፡ይህቺን ኳስ ደግሞ በሆነ ቅጽበት በቁጥጥሩ ስር ሊያደርጋት የሚችለው አንድ ተጫዋች ብቻ ነው፡፡ በተመሳሳዩ ሰዓት ሌሎቹ ሃያ አንድ ተጫዋቾች ስልና ንቁ ተከታታይ ይሆናሉ፡፡ ስለዚህ ታዳሚው ኳሱን ስለያዘው ተጫዋች ፍጥነት፣ ስሜት፣ ችሎታና አቀራረብ ያስባል፡፡ እንግዲህ የቀረው ሰዎች በእኛ ስልት ላይ የወደዱትን እንዲያስቡ ማድረግ ነው፡፡ በእርግጠኝነት ከተጫዋቾቻችን ግላዊ ችሎታ ጋር ተስማሚ ዘይቤ ስለመሆኑ በአግባቡ ልናሳያቸው ችለናል፡፡ ይህም እኛን ከድል ወደ ድል እያሻገረን ይገኛል፡፡ ስለዚህ ለምን የምናሸንፍበትን ስርዓት መቀየር ያስፈልገናል?” ሲልም መሞገቻ ሃሳቡን አወጋው፡፡

ቻፕማን ከአንደኛው የተጫዋቾች ትውልድ ወደ ሌላኛው በሚደረገው ሽግግር ላይ የሚፈጠሩ ችግሮችን መቋቋም አልተጠበቀበትም፡፡ በጥር 1-1934 ክለቡ ከበሪ ጋር ባደረገው ጨዋታ ብርድ አገኘው፡፡ እርሱ ግን በማግስቱ ቀጣዩን ተጋጣሚ ሼፊልድ ዌንስዴይን ለመገምገም  ወደ በሪ ለማቅናት ወሰነ፡፡ ወደ ለንደን ሲመለስ ከፍተኛ ትኩሳት ነበረበት፡፡ ሆኖም ግን የክለቡ ዶክተሮችን ምክር ችላ ብሎ የተቀያሪ ቡድኑ ጨዋታ ላይ ለመታደም ወደ ጊድፎርድ አመራ፡፡ ወደ ቤቱ ሲመለስ በሳምባ ምች ተጠቅቶ አልጋ ላይ ወደቀ፡፡ዳግመኛ አላገገመም፡፡ ሃምሳ ስድስተኛ የልደት በዓሉን ሊያከብር አስራ አምስት ቀን ሲቀረው ጥር 6 ቀን 1934 አሸለበ፡፡

አርሰናል በቀጣዩ አመት የሊጉን ድል ተቀዳጀ፡፡ በተከታታይ ለሶስተኛ ጊዜም አሸናፊ ሆነ፡፡ ቻፕማን ካለፈ ከጥቂት ወራት በኋላ እግርኳሳዊ ሃሳቦቹ የተከተቡባቸው ጽሁፎቹ ለህትመት በቁ፡፡ ቻፕማን በጽሁፎቹ በቡድኖች መካከል በታየው ደካማ የመፎካከር አቅም ያለፉት እነዚያ ጊዜያት እንደሚያስቆጩት ይገልጻል፡፡ ” ከአሁን በኋላ የቡድኖች አላማ ጥሩ እግርኳስ ለማሳየት መጫወት መሆን የለበትም፡፡ በየትኛውም ዘዴ ግቦችን ማግኘትና ነጥቦችን መሰብሰብ ይገባቸዋል፡፡ የብቃታቸውም ልክ በደረጃ ሰንጠረዡ  ላይ በሚኖራቸው ቦታ ሊዳኝ ይችላል፡፡” ሲል ይሞግታል፡፡

እንግዲህ ይህ ሁሉ አስረጅ ማረጋገጫ የማይሻ እውነታ ይመስላል፡፡ ቻፕማን የእግርኳስ ጨዋታ ተቀዳሚ አላማ ማሸነፍ መሆኑ ምክንያታዊ እንደሆነ ቢያምንም አማተራዊ አዝማሚያ የሚያመዝንበት የእግርኳስ አጨዋወት በሰፊው እየናኘ ለመምጣቱ ማሳያም ይሆናል፡፡ ቻፕማን ሁኔታውን ሲያብራራው ” ከሰላሳ ዓመት በፊት ተጫዋቾች የግል ክህሎታቸውን በመጠቀም በጨዋታው ጥበብና ውበትን የማሳየት ሙሉ ነጻነት ነበራቸው፡፡ አሁን ግን ለአጨዋወት ስርዓት/System/ የራሳቸውን ድርሻ ማበርከት ይጠበቅባቸዋል፡፡” ይላል፡፡ ከዚህ ሁሉ በኋላ የማሸነፍ አላማ አከራካሪነት መፍትሄ ተበጀለት፡፡ የተጫዋቾች ተናጠላዊ ተሰጥዖ ከአንድ ቡድን አጠቃላይ መዋቅራዊ ጥንካሬ ጋር መሳ ለመሳ የሚሄድ ጉዳይ እንደሆነ ታመነበት፤ ስለዚህም በእግርኳስ ጨዋታ ታክቲክ ያለው ዋጋ እውቅና ተቸረው፡፡

ይቀጥላል...


ስለ ደራሲው 

ጆናታን ዊልሰን ዝነኛ እንግሊዛዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ሲሆን በተለያዩ ጋዜጦች፣ መጽሄቶች እና ድረገጾች ላይ ታክቲካዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው የእግርኳስ ትንታኔዎችን የሚያቀርብ ጉምቱ ጸኃፊ ነው፡፡  ባለፉት አስራ ሁለት ዓመታትም የሚከተሉትን ዘጠኝ መጻህፍት ለህትመት አብቅቷል፡፡

Behind The Curtain: Travels in Eastern European Football (2006)

Sunderland: A Club Transformed (2007)

Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics (2008)

The Anatomy of England (2010)

Brian Clough: Nobody Ever Says Thank You: The Biography (2011)

The Outsider: A History of the Goalkeeper (2012)

The Anatomy of Liverpool (2013)

Angels With Dirty Faces: The Footballing History of Argentina (2016)

The Barcelona Legacy: Guardiola, Mourinho and the Fight For Football’s Soul (2018)


ቀደምት ምዕራፎች
መቅድም LINK
ምዕራፍ 1 – ክፍል አንድ LINK
ምዕራፍ 1 – ክፍል ሁለት LINK
ምዕራፍ 1 – ክፍል ሶስት LINK
ምዕራፍ 1 – ክፍል አራት LINK
ምዕራፍ 2 – ክፍል አንድ LINK
ምዕራፍ 2 – ክፍል ሁለት LINK
ምዕራፍ 2 – ክፍል ሶስት LINK
ምዕራፍ 2 – ክፍል አራት LINK
ምዕራፍ 3 – ክፍል አንድ
LINK
ምዕራፍ 3 – ክፍል ሁለት
LINK
ምዕራፍ 3 – ክፍል ሦስት LINK

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *