ደደቢት የሶስት የውጪ ተጫዋቾች ዝውውር አጠናቀቀ

ባሳለፍነው ሳምንት አዲስ አሰልጣኝ የቀጠሩት ደደቢቶች ሁለት አዳዲስ ተጫዋቾችን ሲያመጣ የቀድሞ ተጫዋቹንም መልሶ አስፈርሟል።

በውጤት ቀውስ የሚገኘው ደደቢት ከገባበት የውጤት ማጣት ለመውጣት እየተንቀሳቀሰ ሲሆን ባለፈው ሳምንት ዳንኤል ፀሐዬ አዲስ አሰልጣኝ አድርጎ ሲሾም አሁን ደግሞ ጋናዊ የቀድሞ የመቐለ 70 እንደርታ አጥቂ ኑሁ ፉሴይኒ፣ የቀድሞ ተጫዋቻቸው ኢኳቶርያል ጊንያዊው ሮበን ኦባማ እንዲሁም ናይጀርያዊው ተከላካይ አንቶንዮ አቡዋላን አስፈርመዋል።

ባለፈው ዓመት አጋማሽ የሊባኖሱ ክለብ ሸባብ አል ሳህል ለቆ ከመቐለ ጋር የተሳካ የውድድር ዓመት ያሳለፈው የ29 ዓመቱ ጋናዊ አጥቂ ኑሁ ፉሴይኒ ከስድስት ወራት ቆይታ በኋላ ወደ ኢትዮጽያ የሚመለስ ይሆናል። ባለፈው ዓመት መቐለ ለዋንጫ ባደረገው ፉክክር ቁልፍ ቦታ ከነበራቸው ተጫዋቾች አንዱ የነበረው ይህ ተጫዋች በየእግር ኳስ ህይወቱን በሞልዶቫው ሸሪፍ ትሪስፖል ጨምሮ ለአሻንቲ ጎልድ እና ኒው ኢዲብያሴ አሳልፏል።
ተጫዋቹ ከዚ በተጨማሪ በ2015 በአሰልጣኝ አብርሃም ግራንት ጥሪ ተደርጎለት ለጋና ብሄራዊ ቡድን ሁለት ጨዋታዎች ማድረግ ችሏል።

ተጫዋቹ ከሁለት ቀን በፊት ለሲዳማ ቡና ከፈረመው ታናሽ ወንድሙ ፉሴይኒ አልሃሰን ጋር በስድስት ክለቦች አብሮ ተዘዋውሮ በመጫወት አስገራሚ ታሪክ ያለው ሲሆን በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ወንድማማች የውጪ ዜጎች በተመሳሳይ ጊዜ በመሳተፍ አዲስ ታሪክ ያስመዘግባሉ።

ሌላው ለደደቢት ፊርማው ያኖረው ኢኳቶርያል ጊንያዊው ሮበን ኦባማ ነው። የአጥቂ አማካይ እና አጥቂ ሆኖ መጫወት የሚችለው ኦባማ ከአንድ ዓመት በፊት የሰማያዊዎቹን ማልያ ለብሶ የተጫወተ ሲሆን በድጋሚ ወደ ኢትዮጵያ የሚመልሰውን ዝውውር ፈፅሟል። በሃገሩ ክለብ አትሌቲኮ ማላቦ፣ ፓንተርስ እና አትሌቲኮ ሴሙ የተጫወተው ይህ ተጫዋች በ2012 የሃገሩ ሊግ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በመሆንም ሲሸለም በ2015 ሀገሩ ባዘጋጀችው የአፍሪካ ዋንጫም ተሳትፏል።

ሶስተኛው የሰማያዊዎቹ ፈራሚ የሆነው አንጋፋው ናይጀርያዊ ተከላካይ አንቶንይ አባውላ ሆኗል። ተጫዋቹ ከዚህ በፊት ለኒጀር ቶርናዶስ፣ ኦሽን ቦይስ እና ካኖ ፒለርስ እንዲሁም ለዛምቢያው ሉሳካ ዳይናሞስ የተጫወተ ሲሆን በ2008 ከኦሽን ቦይን እንዲሁም 2013 ከካኖ ፒለርስ ጋር የናይጀርያ ሊግ ዋንጫን አሸንፏል።

ከሰንጠረዡ ግርጌ ተላቀው በሊጉ ለመትረፍ በሁለተኛው ዙር ብዙ ስራ የሚጠብቃቸው ሰማያዊዎቹ በቀጣይ ጊዚያትም የሀገር ውስጥ የዝውውር መስኮት በመጠቀም ተጨማሪ ተጫዋቾች እንደሚያዘዋውሩ ይጠበቃል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *