የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ሰሞኑን ሲያነጋግር በሰነበተው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ከአፍሪካ ዋንጫ ማጠርያ ውጪ መሆን ዙርያ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ ጥፋተኛ ተብለው ውሳኔ የተላለፈባቸው ግለሰቦችንም ይፋ አድርጓል፡፡
በዚህም መሰረት የስራ አስፈፃሚ አባል የሆኑት አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ ቀጥተኛ ተጠያቂ ተገርገው ከስራቸው ታግደዋል፡፡ የአይቲ ክፍል ኃላፊዋ ዘውድነሽ ይርዳው እና የጽህፈት ቤት ኃላፊው አቶ ዘርይሁን ቢያድግልኝም ከስራቸው እንዲሰናበቱ ተወስኗል፡፡
ረጅም ሰአት በፈጀው የዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ጁነይዲ ባሻ ፣ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ አበበ ገላጋይ ፣ አሊሚራህ መሃመድ ፣ ልኡልሰገድ በጋሻው እና ቾል ቤል (ኢ/ር) የሰጡትን መግለጫ እና ከጋዜጠኞች ለቀረቡት ጥያቄዎች የሰጡትን ምላሽ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
‹‹ … ወደ ዝርዝር ሲገባ ግን ጥፋቱ የጅምላ አይደለም፡፡ አንዱ ላጠፋው ሁሉም ሊባረር አይገባም ›› አቶ ጁነይዲ ባሻ
የካይሮ ጉዞ
‹‹ የካፍ ሃላፊዎች ለአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ ኪንሳሻ ስለነበሩ ወደ ግብጽ የሄድኩት እሁድ ማታ ነው፡፡ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሰዎችን ለማግኘት ሙከራ ተደርጓል፡፡ ኢሳ ሃያቱን በፀሃፊው በኩል ለማናገር ሞክሬያለው፡፡ የሚቀየር ነገር እንደሌለ ቢናገሩም የነገሩን አሳሳቢነት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስለገለፀ በቅድመ ሁነታ ልንገባ የምንችልበት እድል አልተሟጠጠም፡፡ ብዙ ኃገሮች ከማጣርያው ስለሚወጡ የትኛው ሃገር ሊገባ ይችላል የትኛው ሊወጣ ይችላል የሚለውን አሰስመንት እየሰራን ነው፡፡ አሁን ላይ ያለው ሁኔታ ይህንን ይመስላል፡፡
‹‹ አንዴ ከሆነ በኋላ ለውጥ አይመጣም ብለን ቁጭ አላልንም፡፡ ሙከራ ማድረግ አለብን፡፡ ቁጭ ብለን ማየት የለብንም፡፡ ነገሮችን ለማስተካከል ጥረት አድርገናል፡፡ ካይሮ ባንሄድ ኖሮ ጥረት አልተደረገም እንባል ነበር፡፡ ስንሄድ ደግሞ በስልክ መጨረስ ይቻል ነበር እየተባልን ነው፡፡ ››
ትኩረት ስለመስጠት
‹‹ የሴቶች ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ መሳተፍ የአመቱ እቅዳችን ውስጥ ነበር፡፡ ወጪውን አስቀምጠንና አፅድቀን ተንቀሳቅሰናል፡፡ በመጀመርያ እቅዶቹን ማን እንደሚሰራ እና ወጪውን አሰልተንም ተቀምጧል፡፡
‹‹ ትኩረት አልተሰጠውም በሚባለው ነገር አልስማማም፡፡ ሚድያው አልዘገበውም እንጂ ከ17 አመት በታች ሴቶች ውድድር ላይ ገብተናል፡፡ በሴቶች እግርኳስ ላይ እየሰራን ነው፡፡
‹‹ የተለያዩ ስልጠናዎች እንዲኖሩ አድርገናል፡፡ ከ20 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን በሚሄድበት ሃገር ትኩረት ሰጥተን ተከታትለናል፡፡ ለሴት አሰልጣኞች ኃላፊነት እየተሰጠን ነው፡፡ ይህ ስህተት በሴቶች ላይ ስላጋጠመ ወደ ፆታዊ ጉዳይ ማምራት የለበትም፡፡ ››
የአቶ ዮሴፍ ቅጣት እና በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ አለመገኘት
‹‹ አቶ ዮሴፍ እዚህ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ያልመጣው በራሱ ውሳኔ ነው፡፡ እገዳ ነው እንጂ የጣልነበት አላባረርነንም፡፡ የማባረር ስልጣን ያለውም ጠቅላላ ጉባኤው ነው፡፡
‹‹ ጥፋተኞች ላይ እርምጃ መውሰድ የትም ቦታ ያለ ህግ ነው፡፡ ጥፋተኛ እርምጃ ይወሰድበታል፡፡ ግን ይሄ በቂ አይደለም፡፡ ሲስተሙ ላይ ያለውን ነገር ለማስተካከል ጥረት እናደርጋለን፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግን የግለሰቦች ጥፋት እንደ ሲስተም ችግር ተደርጎ የሚወሰድበት ሁኔታ አለ፡፡
‹‹ አንዳንድ ክለቦች ማብራርያ ስጡ ብለዋል፡፡ ማብራርያውን አዘጋጅተን ስለጨረስን እንሰጣለን፡፡ ጠቅላላ ጉባኤ ጥሩ የተባለው ግን የምንጠራው ጥሩ ስለተባልን ሳይሆን በህጉ መሰረት ነው፡፡
‹‹ ማኔጅመንት የራሱ ፕሪንሲፕል አለው፡፡ በጋራ ለሚሰራ ስራ በጋራ ተጠያቂ ይኾናል፡፡ የጋራ ተጠያቂነት አለብን፡፡ ያ ባይሆን ኖሮ የሚመለከተው ብቻ መግለጫ እንዲሰጥ እናደርግ ነበር፡፡ ወደ ዝርዝር ሲገባ ግን ጥፋቱ የጅምላ አይደለም፡፡ አንዱ ላጠፋው ሁሉም ሊባረር አይገባም፡፡ ››
የመግለጫ መዘግየት
‹‹ ልክ ነው ዘግይተናል፡፡ ነገር ግን የዘገየነው ለማጣራት እና ዝርዝር ነገሮችን ለመሰብሰብ ነው፡፡ ለህዝቡ ላለመግለፅ አስበን አይደለም መግለጫ ያልሰጠነው፡፡ ››
‹‹ እርምጃው አንዱን ወንጅሎ አንዱን ነፃ ለማድረግ የታሰበ አይደለም›› አቶ አበበ ገላጋይ
‹‹ ይህንን ውሳኔ ስንወስን እያንዳንዷን ችግር አይተን ነው፡፡ በደፈናው ጋዜጣዊ መግለጫ ብንሰጥ መረጃ የለንም ነበር፡፡ ዮሴፍ ካይሮ የተላከው ለሌላ ሳይሆን ለሴቶች ጉዳይ ነው፡፡ አጀንዳ ነበር አጀንዳው ምን ይላል? ስብሰባው ላይ ምን ነበር? የተመዘገቡ ሃገሮች ዝርዝር ተመልክተህ ነበር? ብለን ሰንጠይቅ የሰጠን ምላሽ አጥጋቢ አይደለም፡፡
‹‹ እዚህ ቦታ የወርቅ ማእድን የለም፡፡ የመስራት ፍላጎት ነው የሰባሰበን፡፡ አንዱን ወንጅሎ አንዱን ነፃ ለማድረግ የታሰበ አይደለም፡፡ እርምጃው የተወሰደው በግልፅ በሚታይ ነገር ነው፡፡ የሄደው ለሴቶች እግርኳስ ጉዳይ እስከሆነ ድረስ ስራውን መስራት ነበረበት፡፡ ››
‹‹ ጠቅላላ ጉባኤ ደንብ እና ስርአት አለው፡፡ ጠቅላላ ጉባኤ ለመጥራት 2/3ኛው አባል መጠየቅ ይኖርበታል፡፡ ሌላው የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ካመነበት መጥራት ይቻላል፡፡ ››
‹‹ እንደ ስራ አስፈፃሚ ይቅርታ መጠየቅ ይኖርብናል ›› ቾል ቤል
‹‹ እንደ እግርኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈፃሚ ይቅርታ መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ ውድቀት እንደሆነ በሚገባ ገምግመን አይተናል፡፡ ››
‹‹ በመጀመርያ ፕሮፌሽናል ብንሆን ጥሩ ነው፡፡ የሰፈር ወሬ ባይወራ ጥሩ ነው፡፡ ዮሴፍን ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳትመጣ አላልነውም፡፡ ዮሴፍ ከውሳኔው በኋላ የናንተ አካል ስላልሆንኩ አልመጣም ነው ያለው፡፡ እንዳይመጣ የከለከለው የለም፡፡ ዮሴፍ ላይ እንዳትወስኑ የሚለንም የለም፡፡ ይህን እንድናደርግ የምንተዳደርበት ህግ እና ደንብ አለ፡፡ ››