አዳማ ከተማ አምረላህ ደልታታን አስፈረመ

ከቀናት በፊት በክረምቱ ካስፈረማቸው ሶስት ተጫዋቾች ጋር የተለያየው አዳማ ከተማ የማጥቃት አማራጩን ለማስፋት ፈጣኑ የመስመር ተጫዋቾች አምረላህ ደልታታን አስፈርሟል፡፡

በስልጤ ወራቤ የተጫዋችነት ህይወቱን የጀመረው አምረላ ወደ ሀድያ ሆሳዕና በ2007 አምርቶ ክለቡ ወደ ፕሪምየር ሊግ ካደገበት ጊዜ ጀምሮ ለሶስት ዓመታት ቆይታን ካደረገ በኃላ በ2010 ወደ ወላይታ ድቻ በሁለት ዓመታት ውል አምርቶ የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳታፊ በነበረው ወላይታ ድቻ መልካም የሚባል የውድድር ዓመትን አሳልፏል። ሆኖም በ2011 ከአሰልጣኝ ዘነበ ፍሰሀ ጋር በግል ጉዳዮች ባለመስማማት ክለቡን ለቆ ያለፉትን አራት ወራት ያለ ክለብ ከቆየ በኋላ ነው አዳማ ከተማን የተቀላቀለው። ተጫዋቹ የአንድ ዓመት ከስድስት ወራት የውል ስምምነት ከአዳማ ጋር መፈፀሙን ክለቡ በተለይ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጿል፡፡

አዳማ በሁለተኛው ዙር ራሱን አጠናክሮ ለመቅረብ ከአምረላህ ውጪ ባሳለፍነው ሳምንት ብሩክ ቃልቦሬን ማስፈረሙ የሚታወስ ሲሆን በቀጣዮቹ ቀናት አዳዲስ የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቾች ለማምጣት ጥረት እያደረገ እንደሆነም ታውቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *