ሴቶች ጥሎማለፍ | ንግድ ባንክ ወደ ሩብ ፍፃሜ አልፏል

የኢትዮጵያ ሴቶች ጥሎ ማለፍ ጨዋታ ዛሬ መደረግ ሲጀምር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኢትዮ ኤሌትሪክን በረሂማ ዘርጋው ጎሎች 2-1 በማሸነፍ ወደ ሩብ ፍፃሜ ዙር ማለፉን አረጋግጧል።

ቀዝቀዝ ባለ እንቅስቃሴ እና ንግድ ባንኮች በፈጠሩት የጎል ዕድል በጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በ6ኛው ደቂቃ በጥሩ ቅብብል ወደ ፊት በመግባት ረሂማ ዘርጋው የሞከረችው ኳስ የግቡ አግዳሚ መልሶባታል። ተመጣጣኝ የሆነ እንቅስቃሴ በመሀል ሜዳ ላይ የተገደበ የኳስ ፍሰት ብንመለከትም ተጨማሪ የግብ ዕድሎችን ለመመልከት 23ኛው ደቂቃዎችን መጠበቅ አስፈልጓል። 29ኛው ደቂቃ የንግድ ባንኳ አማካይ ህይወት ደንጊሶ ከቅጣት ምት አክርራ የመታችውን ግብጠባቂዋ ገነት አንተነህ በቀላሉ ይዛዋለች።

ለውድድሩ የሰጡት ግምት አነስተኛ መሆኑን ተከትሎ በሁለቱም ቡድኖች በኩል በአዕምሮ እና ፍላጎት ረገድ ያደረጉት ዝግጅት አነስተኛ መሆን ተደጋጋሚ የሆኑ የግብ ዕድሎችን እንዳንመለከት አድርጎናል። ያም ቢሆን 32ኛው ደቂቃ የኢትዮ ኤሌትሪኮች ከሳጥን ውጭ ከተሰጠው ቅጣት ምት ልማደኛዋ የመስመር አጥቂ መሳይ ተመስገን የመታችውን ጠንካራ ኳስ የንግድ ባንኳ ግብጠባቂ ንግስቲ ማዕዛ መቆጣጠር አቅቷት የተፋችውን ቤቴልሔም አያሌው አግኝታ ወደ ጎልነት በመቀየር ኢትዮ ኤሌክትሪክን ቀዳሚ ማድረግ ቻለች።


ከጎሉ ብዙም ሳይቆይ ጨዋታውን ከአምስት ደቂቃ በላይ እንዲቋረት ያደረገ ጉዳት ተከስቷል። ሁለቱ የንግድ ባንክ ተከላካዮች ዘቢብ ኃይለሥላሴ እና ገነሜ ወርቁ እርስ በእርስ በመጋጨታቸው በተፈጠረው ጉዳት ገነሜ ወርቁ ሜዳ ላይ በተደረገላት ህክምና ወደ ጨዋታ ስትመለስ ዘቢብ ጭንቅላቷ ላይ የመፈንከት አደጋ ደርሶባት የነበረ በመሆኑ ለተጨማሪ ህክምና ወደ ቤተዛታ ሆስፒታል አምርታለች። ወደ እረፍት መውጫ መዳረሻ ላይም በ44ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር ትግስት ዘውዴ ያሻገረችውን ረሂማ ዘርጋው በግንባሯ በግጨት ንግድ ባንኮችን አቻ ማድረግ ችላለች።


ከእረፍት መልስ በ50ኛው ደቂቃ የኢትዮ ኤሌትሪኳ ግብጠባቂ ገነት አንተነህ የሰራችውን ቀላል ስህተት ተከትሎ ረሂማ ዘርጋው ቀላል ኳስን ወደ ጎልነት በመቀየር ንግድ ባንክን መሪ ማድረግ ችላለች። ጎሉ ከተቆጠረባቸው በኃላ በተሻለ መንቀሳቀስ ቢችሉም የውድድር ዓመቱ መሰረታዊ ክፍተታቸው የጎል ዕድሎችን መፍጠር ዛሬም ተስተውሏል። በኤሌክትሪክ በኩል በጠንካራ ምቷ ንግድ ባንክን ስታስጨንቅ የዋለችው መሳይ ተመስገን ከየትኛው የሜዳ ክፍል የምታገኘውን ኳስ አክርራ በመታች ቁጥር የንግድ ባንክ ግብጠባቂ ንግስቲ ስትተፋው ገነሜ ወርቁ እና ጥሩአንቺ መንገሻ ኳሱን ከግብ ክልሉ ባያርቁት ኖሮ ጎሎችን ማስቆጠር በቻሉ ነበር። አልፎ አልፎም ቢሆን ወደ ጎል የሚደርሱት ንግድ ባንኮች ጎል አያስቆጥሩ እንጂ በብርቱካን ገብረክርስቶስ እና ረሂማ ዘርጋው ተጨማሪ ጎሎችን ለመፍጠር ጥረት ያደርጉ ነበር። ጨዋታውም ተጨማሪ ጎሎች ሳይቆጠርበት በንግድ ባንክ 2 -1 አሸናፊነት ተጠናቋል።


ንግድ ባንክ በድሉ በመታገዝ ወደ ወደ ቀጣይ ዙር ሲያልፍ በሩብ ፍፃሜው ከአርባምንጭ ከተማ ጋር ይጫወታል።

የውድድሩ ሁለተኛ ዙር ጨዋታዎች ነገ ሲቀጥሉ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና አዲስ አበባ ራሳቸውን ከውድድሩ በማግለላቸው ተጋጣሚዎቻቸው ጥረት እና አርባምንጭ ወደ ቀጣዩ ዙር አልፈዋል።

የውድድሩ መርሐ ግብር

አንደኛ ዙር


ማክሰኞ የካቲት 12 ቀን 2011


9:00
መቐለ 70 እንደርታ ከ አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከ

ረቡዕ የካቲት 13 ቀን 2011


9:00
ቂርቆስ ከ ንፋስ ስልክ

ሐሙስ የካቲት 14 ቀን 2011


9:00
ልደታ ክ/ከ ከ ሻሸመኔ ከተማ

* ቦሌ ከፋሲል የሚያደርጉት ጨዋታ በፋሲል አለመካፈል ምክንያት ቦሌ ወደ ሁለተኛ ዙር በቀጥታ አልፏል።

ሁለተኛ ዙር

ቅዳሜ የካቲት 9 ቀን 2011

ኢት/ንግድ ባንክ 2-1 ኢትዮ ኤሌክትሪክ

እሁድ የካቲት 10 ቀን 2011

8:00
መከላከያ ከ አዳማ ከተማ

9:00
ጥሩነሽ ዲባባ ከ ሀዋሳ ከተማ

10:00
ድሬዳዋ ከተማ ከ ጌዴኦ ዲላ

ወደፊት ቀናቸው የሚገለፅ

– ቂርቆስ/ንፋስ ስልክ ከ ልደታ/ሻሸመኔ
– መቐለ/አቃቂ ከ ቦሌ

* ቅዱስ ጊዮርጊስ እና አዲስ አበባ ከተማ ባለመሳተፋቸው ምክንያት ጥረት እና አርባምንጭ ወደ ሩብ ፍፃሜ አልፈዋል


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *