የፀጋዬ ኪዳነማርያም የልቀቁኝ ጥያቄ ተቀባይነት አገኘ

ወልዋሎን በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ከወራጅነት ስጋት እንዲላቀቅ ማድረግ ከቻሉ በኃላ ዘንድሮ አዲስ የአንድ ዓመት ኮንትራትን ተፈራርመው የነበሩት አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም የልቀቁኝ ጥያቄያቸው ተቀባይነት በማግኘቱ ተለያይተዋል፡፡

ወልዋሎን በ2010 የውድድር ዘመን ከአርባምንጭ ከተማ ጋር ከተለያዩ በኃላ በዓመቱ አጋማሽ አርባምንጭ ከተማን በመልቀቅ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲን የተቀላቀሉት አሰልጣኝ ፀጋዬ በዚህ ዓመት እንዲሟሉ ሲጠይቋቸው የነበሩ የደሞዝ መዘግየት፣ ትጥቅ አቅርቦት እና የመሳሰሉ ጥያቄዎች ሳይሟሉ በመቅረታቸው ነበር ከሳምንታት በፊት የልቀቁኝ ጥያቄን ያቀረቡት። የክለቡ የበላይ አካላትም በአሰልጣኙን ጥያቄ ላይ ተነጋግሮ የመልቀቂያ ሀሳባቸውን ተቀብሎ  ከውሳኔ ላይ በመድረሱ የስድስት ወራት ኮንትራት እየቀራቸው ዛሬ በስምምነት መለያየታቸውን አሰልጣኝ ጸጋዬ ኪዳነማርያም ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡

የቀድሞው የትራንስ ኢትዮጵያ፣ ሐረር ቢራ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ ንግድ ባንክ እና አርባምንጭ አሰልጣኝ የነበሩት አሰልጣኙ ወደ ሌላ የፕሪምየር ሊግ ክለብ ለማቅናት እየተነጋገሩ መሆኑን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡ ወልዋሎ አዲግራት በአንፃሩ አዲስ አሰልጣኝ በዚህ ሳምንት ያመጣል ተብሎም ይጠበቃል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *